በሥነ ፍጥረት ታሪክ ቀደምትነት ያለውና በመጀመርያ የተመሠረተው ቤተሰብ መሆኑ በማያወላውል መንገዱ ተገልጽዋል። አዳምና ሔዋን ልጆች አፍርተው የመሠረቱት ያ የመጀመርያው ቤተሰብ ለቀሪው እና እስካሁን ለደረሰው የቤተሰብ መስፋፋት መነሻ ሆኖ ዓለም ሁሉ የዚህ ምሥረታ ተካፋይ ሆኖ እየተጋባና እየተዋለደ ቤተሰብ አፍርቶ ይኖራል። ቤተሰብ የቤተ ክርስቲያናችን መሠረት ነው በማለት የምንናገረው ከዚህ በመነሳት መሆኑም አጠያያቂ አይደለም። ቤተ ክርስቲያንም ቤተሰብ ፍጹም ጤነኛና ደስተኛ በሃይማኖትም የጸና ይሆን ዘንድ ዘወትር ያለማቋረጥ ታስተምራለች። ቤተሰብ በመልካም አኗኗር ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቆ በምግባር በሥርዓት የሚኖር ከሆነ ለተተኪው ትውልድ መልካም መንገድ አዘጋጅቶ ማለፍ ስለሚቻለው እግዚአብሔርን አክብረው የሚኖሩ የቤተሰብ አባላት እንዲኖሩ ትደግፋለች፤ ትሻለችም። አባትና እናት ለልጆቻቸው ልጆችም ለቤተሰባቸው የየድርሻቸውን በማድረግ አንድነቱን ያጎለብታሉ። መልካም ቤተሰብ ይኖር ዘንድ ኃላፊነቱ በቤተሰብ ውስጥ ያሉ አባላት ሁሉ ቢሆንም በይበልጥ ግን የባልና ሚስት ይሆናል። ምክንያቱም ልጆቻቸውን በማስተማር ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉት እነርሱ ናቸውና። በእርግጥ በአዳምና በሔዋን ቤተሰብ ውስጥ ወንድሙን የሚገድል ቃኤል፤ በቅዱስ ዳዊት ቤተሰብ ውስጥ አባቱን ለመግደል የተነሳ አቤሴሎም፤ በይስሐቅ ቤተሰብ በወንድሙ ላይ የተነሳ ኤሳው፤ በያዕቆብ ቤተሰብ ወንድማቸው ላይ በአመፃ ተነስተው ዮሴፍን በሃያ ብር የሸጡ ወንድሞች፤ በኖኅ ቤተሰብ መካከል የአባቱን ራቁት ከመሸፈን ይልቅ በአባቱ የሳቀ ወንድሞቹም አብረው እንዲስቁ ያነሳሳ ካም እና በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ተመሳሳይ የሆኑ ሁኔታዎች እንዳሉ ቢታወቅም። ሆኖም ግን ደጋግ ቤተሰቦችን ማፍራት የሚቻለው ከፈቃደ እግዚአብሔር ባሻገር ዘወትር በፈሪሐ እግዚአብሔርና በጸሎት የተደገፈ ሕይወት መኖር ሲቻል ነው።
ይኼን ያህል በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ስላሉ እናቶችና አባቶች፣ ወንድሞችና እኅቶች እንዲሁም ልጆች ካወራን እዚህ በምንኖርበት የአሜሪካን ምድር ላይ በአዲስ መጤነት ወይም በዕንግድነት መጥተው ለሚኖሩ ሰዎች የኑሮ ውጣ ውረድ ምን ያህል ከባድ እና አስቸጋሪ መሆኑን በሚገባ እናውቃለን። ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ባሻገር አብዛኛው ጊዜያቸውን በትምህርት ቤት ስለሚያሳልፉ የተለያዩ ሁኔታዎችን ለምደውና ተገንዝበው ይመጣሉ። ጠቃሚውን እንደ ጥቅሙ ለመውሰድ እንደምንሞክረው የማይጠቅመውን ደግሞ ጎጂ መሆኑን አውቀን ዕለት ከዕለት ክትትል በማድረግ የቤተሰብን ሕይወት በጥሩ ሁኔታ ለመምራት ይቻላል። የቤተሰብ ኃላፊነት ወይም ደግሞ ቤተሰብን መምራት ማለት በቤት ውስጥ ያለውን ሕይወት ብቻ በጥሩ ሁኔታ መምራት ሳይሆን በትምህርት ቤት፣ በሥራ፣ በማኅበራዊ ኑሮ፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በመዝናኛ ቦታዎችና በሌሎችም አካባቢዎች ምን ማድረግ እንደሚገባ አስቀድሞ ሁኔታዎችን ማመቻቸትም ነው። ጠንካራ ቤተሰብ ጠንካራ አገርን መፍጠር ይችላል። ለዚህ ሁሉ ዓይነተኛው መሠረት በእግዚአብሔር በማመን ቃሉንና ትምህርቱን ተቀብሎ በንግግር ሳይሆን በተግባር መተርጎም ሲቻል ነው። ባልና ሚስት አንድ አካል መሆናቸውን አውቀው ከተሳሰቡ በግልጽ ስለ ሁሉም ነገር መነጋገር ከቻሉ ኑሮአቸው የተቃና ይሆናል። ቤተሰብ እርስ በርስ የሚነጋገሩበት በቂ ጊዜ ሊኖራቸው ይገባል። አሁን ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነውና ባልና ሚስት ከልጆቻቸው ጋር የሚነጋገሩበትን ሁኔታ ካላመቻቹ በእጃቸው ላይ ሊያጫውታቸው የሚችል የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ስላሉ በቤተሰብ መካከል ያለው ቅርርብ
የበለጠ እየተለያየ ይመጣል። ተነጋግሮ መግባባት የማይችል ቤተሰብ ተነጋግረው ሊግባቡ የሚችሉ ልጆችን ለማፍራት ይቸገራል። ስለሆነም በቂ ጊዜ በመስጠት ቤተሰብን መምራት ከሁሉ የበለጠ ዋጋ አለው። እናትና አባት የልጆቻቸውን ጓደኞች በአግባቡ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ጠቢቡ ሰሎሞን በምሳሌው "ብረት ብረትን ይስለዋል፤ ሰውም ባልንጀራውን ይስለዋል" ይለናልና። ስለዚህም የቤተሰብ ኃላፊነት ከማብላትና ከማጠጣት፣ ከማልበስና ከማስተማር፣ ከመንከባከብና ከማዝናናት የበለጠ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።
ወላጆች በሥራቸው ላይ የተለያዩ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥማቸው ልጆችም በትምህርታቸው ላይ ተመሳሳይ ችግሮች ይገጥሟቸዋልና ትምህርት እንዴት ነበር? ምን አደረጋችሁ? በማለት በቁጣ ሳይሆን በፍቅር መመርመር ያስፈልጋል። ግልጽነት ካለበት ቤተሰብ ለችግር መፍትሔ የሚሆን ነገር ስለሚገኝ የዕለት ውሎን መነጋገር ጤናማ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስም “ልጆች ሆይ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ። ወላጆችም “ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጧቸው” ኤፌ. ፪፡፮ በማለት ያስተምረናል። ወላጆች ስለራሳቸውና ስለ ልጆቻቸው ሥጋዊና መንፈሳዊ ሁኔታ በተመለከተ ፍላጎታቸውንና ግዴታቸውን ማሟላት አለባቸው። የቤተሰብ መንፈሳዊ ፍላጎት ከሁሉም በላይ መሆን አለበት። የምናደርገውና የምናቅደው ነገር ሁሉ ኃጢአት የሌለበትና የእግዚአብሔርን ቃል ያከበረ መሆን ይገባዋል። ልጆቻችንንም የዚህን ቃል ነገር በቃልና በተግባር ማስተማር አለብን። አብሮ በመጸለይና የሃይማኖትን ጉዳይ አብሮ ከቤተሰብ ጋር በመወያየት ጤናማ ቤተሰብን ማፍራት ይቻላል። ልጆች ከቤተሰቦቻቸው መልካም ነገርን ካዩ መልካም ሰዎች ሆነው ያድጋሉ። ሃይማኖትን የጠበቁ ወላጆች ሃይማኖተኛ ሰው ከቤታቸው ያፈራሉ። በልጆች ፊት መጥፎ ነገርን ማድረግ በፍጹም ተገቢ አይደለም። ልጆች ከወላጆቻቸው የሚያዩትን ነገር እውነት ነው ብለው ስለሚቀበሉት መልካምነታችንን እንጂ መጥፎነታችንን በእነርሱ ፊት ልናንጸባርቅ አይገባም። በመነጋገር የማይፈታ ምንም ነገር የለምና ቤተሰብ እርስ በርሱ በመወያየት መልካም ዜጋ ማፍራት ይጠበቅበታል። ቤተሰቦቻቸውን ያከበሩ ልጆች አገራቸውንና ሕዝባቸውን ያከብራሉ። በመሆኑም ጤናማ ቤተሰብን ለማፍራት ሁላችን ክፉን በመልካም ማሸነፍ ይኖርብናል እንጂ በክፉ መሸነፍ አይኖርብንም።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።
አብርሃም ሰሎሞን