፬ኛው ዓመታዊ የቅድስት ሥላሴ የ፭ሺ ሜትር ርምጃና ሩጫ ውድድር ሥነ-ሥርዓት በአማረና በልዩ ሁኔታ ባለፈው ሐምሌ ፱/፳፻፰ ዓ.ም. (July 16, 2016) ተከብሯል። ዕለቱ እጅግ በጣም በሚያስደስት የሜኔሶታ ፀሐይ ታጅቦ ባለ ቢጫ ቀለም ትጥቃቸውን በለበሱ ተሳታፊዎች ደምቆ ነበር የዋለው።
፬ኛውን የ፭ሺ ሜትር ሩጫ/ርምጃ ካለፉት ዓመታት ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር የተመዝጋቢው ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር መጨመሩ ሲሆን ወደ 780 የሚሆኑ ተመዝግበው በመስኩ ላይ ከ570 በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ነበሩ።
ከሩጫ/ርምጃው ጎን ለጎን ሁሉም ተሳታፊዎች የተለያዩ የስፖርትና የአካል እንቅስቃሴዎች፣ የቡድን ጨዋታዎችና ባሕላዊ ጨዋታዎችን በመጫወት አሳልፈዋል። ከጨዋታውና ከስፖርቱ ጋር ተያይዞ የርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤተሰቦች የተለያዩ ዓይነት የምግብ ሽያጭና ለስላሳ መጠጦችን ሲያቀርቡ ተስተዉለዋል። እዚህ ላይ ሳልጠቅስ የማላልፈውና ኩራቴ እንዲጨምር ካደረገው ነገር አንዱ በምግብ ዝግጅት፣ በጽዳት እና በማስተባበር ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩት ብዙኃኑ ዶክተሮች፣ ኢንጅነሮች፣ ፕሮፌሰሮችና የተለያዩ ማዕረግ ያላቸው ቤተሰቦች መሆናቸው ነው። ይኸንን ማየት ልብ የሚማርክ ከመሆኑም በላይ ምንኛ ከበረከቱ ለመሳተፍ የሚሹና አርአያ የሚሆኑ የክርስቶስ ፍቅር ያላቸው አያሌ ወንድሞችና እኅቶች መኖራቸውን ተረድቻለሁ።
በሌላ እይታ ደግሞ ሲታይ ይህ የ፭ሺ ሜትር ሩጫ ዝግጅት ከጤና ጠቀሜታ ሌላ የቤተሰብ ፍቅርን መግለጫ፣ ልጅ ከቤተሰቡ ጋር በፍቅር የሚሮጥበት፣ ተነፋፍቀው የቆዩ ወዳጅ ዘመዶች መገናኛ፣ ከተለያየ አቅጣጫ መጥተው ግን ለአንድ አላማ የሚገናኙብት ልዩ እና ተናፋቂ ዓመታዊ ዝግጅት መሆኑ ነው። በመጨረሻም አባታችን ቆሞስ አባ ኃይለሚካኤል ለአሸናፊዎች የዋንጫ ሽልማት ካበረከቱ በኋላ ዝግጅቱን በጸሎት ዘግተዋል። ለዚህ ትልቅ መሰባሰብ ምክንያት ለሆኑት ለሁሉም ተሳታፊዎች፤ ለእርዳታ ለተመዘገቡ እና በተለያየ ምክንያት ሩጫ ላይ ላልተገኙ እንዲሁም ለድጋፍ ሰጪ ድርጅቶችና ግለስቦች በሙሉ ከ፭ሺ ሜትር አዘጋጆች ልባዊ ምስጋና ቀርቧል። ውጤታማና ስኬታማ የነበረው ውድድር የብዙዎች ድጋፍ አስተዋጽዖ ነው።
ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ለሚቀጥለው አምስተኛ ዙር የ፭ሺ ሜትር ሩጫ/ርምጃ በሰላም ያድርሰን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን!
በወ/ት ዘመናይ ዘሪሁን