በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት  ሥላሴ ካቴድራል  ቅዳሜ ነሐሴ ፯ እና ፰/፳፻፰ ዓ.ም. ማዕዶት ዘቤተ ጉባኤ ወገዳማት በሚል መጠሪያ የተደረገው ታላቅ የዐውደ ርእይ መርሐ ግብር የታቀደለትን ዓላማ በተገቢው መልኩ አስተላልፎ ተጠናቋል።

ከኢትዮጵያ ውጪ ለመጀመርያ ጊዜ የታየው ይኽ ዐውደ ርእይ በሚኒሶታ በሚገኙት የማኅበረ ቅዱሳን ቅርንጫፍ አዘጋጅነት ነው። ከፍተኛ ወጪ ተደርጎለት በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለሕዝብ የቀረበው ይኽ ዐውደ ርእይ ቅዳሜ ነሐሴ ፯/፳፻፰ ዓ.ም. ከሥርዓተ ቅዳሴ ፍጻሜ በኋላ በታላቅ ድምቀት የተከፈተው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት  ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ በክቡር መልአከ አርያም ቆሞስ አባ ኃይለሚካኤል ጸሎት ነው። ሙሉ ሐተታ በቀረበበት እና በቂ ገለጻ በተደረገበት በስምንት ክፍሎች ከትዕይንት ፩ እስከ ትዕይንት ፰ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አብነት ት/ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አብነት ት/ቤቶች አስተዋፅኦ፣ በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች የተከሰቱት ችግሮች ያስከተሉት ጉዳት፣ በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ችግር ለመቅረፍ በማኅበረ ቅዱሳን የተወሰዱ መፍትሔዎች፣ በማኅበረ ቅዱሳን የተከናወኑ ሥራዎችና የተገኙ ለውጦች እና ወደፊት መደረግ ያለበት በሚሉ ርእሶች ተመድቦ የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ በቅድሚያ የታየው ለደብሩ ካህናትና ዲያቆናት ሲሆን በመቀጠልም በሁለቱም ቀናት በብዙ መቶዎች ለሚቆጠሩ ምእመናን ነው። ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አብነት ት/ቤቶች በቂ ግንዛቤ ያስጨበጠው ዐውደ ርእይ በመላው ታዳሚዎች በኩል ትምህርት ሰጪ መሆኑ ታምኖበታል።

 

ማኀበረ ቅዱሳን የሚኒያፖሊስ ንዑስ ማዕከል