ጾምሰ ተከልአተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ በውስተ ሕግ እንዘ ይትኤዘዝ ለዘሐገጎ ለሥርየተ አበሳ ወብዝኃ ዕሴት ፈቀደ ኪያሁ ከመ ያድክም ኃይለ ፍትወት ወትትአዘዝ ለነፍስ ነባቢት። (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲ ወ ፭ቱ ቁጥር ፭፻፺፬) ይኽም ማለት ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው። በደሉን ለማስተስረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወድዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ።

 ሕግ እንደሚያስረዳን ቅዱስ መጽሐፍ እንደገለጸልን ጊዜ ወስኖ ወቅት ለይቶ አዋጅ አውጆ መጾም እንደሚገባ በዚህም በረከት እንዳለው ሊያስተምረን ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ብሎ ተናግሯል፦

አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ ቁጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ። የሚመለስና የሚጸጸት እንደ ሆነ፥ ለአምላካችሁም ለእግዚአብሔር የእህልና የመጠጥ ቁርባን የሚሆነውን በረከት የሚያተርፍ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥ ሕዝቡንም አከማቹ፥ ማኅበሩንም ቀድሱ፥ ሽማግሌዎቹንም ሰብስቡ፥ ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ፤ ሙሽራው ከእልፍኙ፥ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ። ኢዩ ፪፥፲፪-፲፮

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንኑ የጌታችንን፣ የነቢያትንና የሐዋርያትን ቃል መሠረት በማድረግ በአዋጅ ከደነገገቻቸው አጽዋማት አንዱ ጾመ ነቢያት (ጾመ ስብከት) (ጾመ ልደት) ተብሎ የሚጠራው ነው። የዚህ ጾም መሠረት ነቢያት አስቀድመው ስለ ጌታ መወለድ ሱባኤ የቆጠሩበት በመቁጠር ጾም የጾሙበትን በማሰብ የምንጾመው ታላቅ መታሰቢያ ነው። ስለዚህም ምሥጢር ዳንኤል በትንቢት ቃሉ ይኽን አስተምሮናል፦

ዓመፃን ይጨርስ፥ ኃጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሯል። ስለዚህ እወቅ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች። ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም፤ የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሯል።

እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ ያደርጋል፤ በሱባዔውም እኵሌታ መሥዋዕቱንና ቍርባኑን ያስቀራል፤ በርኵሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል፤ እስከ ተቈረጠውም ፍጻሜ ድረስ መቅሠፍት በአጥፊው ላይ ይፈስሳል። ዳን ፱፥፳፬-፳፯

በዚህም መሠረት ነቢያት የሆኑ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሚልክያስና ሌሎችም የጌታን ልደት አስቀድመው በትንቢት ሲገልጹ በጾም፣ በጸሎትና በሱባኤ ነበር። በአጽዋማትና በዓላት ቀኖናችን መሠረት እነርሱ ተስፋ አድርገው ድኅነቱን ለማየት፣ ቃሉን ለመስማት በትንቢት ተስፋ ያ,ደረጉትን እኛ እንድናየው እንድንሰማው ስለፈቀደልን ተስፋህን ለመፈጸም፣ ማዳንህን ለማየት፣ ቃልህን ለመስማት ያበቃኸን አምላካችን የልደትህ በረከት ተካፋዮች አድርገን፤ ደስም እናሰኝህ ዘንድ መላእክት በምድር ሰላም ለሰውም እርቅ ሆነ ብለው እንዳመሰገኑህ እኛንም የሰላም ሰዎች አድርገን በማለት እንጾማለን።

አባቶቻችን በደነገጉት የበዓላትና የአጽዋማት ቀኖና መሠረት የነቢያት ጾም አርባ ቀናት እንዲሆን ደንግገዋል። እነዚህም አጽዋማት ፵ ቀናት ጾመ ነቢያት፤ ፫ ቀናት ጾመ አብርሃም ሶርያዊ፤ ፩ ቀን ገሐድ ጾም በመባል ለ፵፬ ቀናት ይጾማል። የገና ጾም ገሐድ ከጾሙ ተያይዞ የተቀመጠ እንጂ ለብቻው የተቀመጠ አይደለም። የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቷ ለሁሉ እኩል የተደነገገና የተሠራ ነው።

ዘመነ አስተምህሮ፥ ብዙ ለመተንተን ጊዜ ቢያጥርም ወቅቶቹን ማወቁ ጠቀሜታ ስላለው በጥቂቱ እንተነትናለን። ይኽም የዘመነ አበው ምሳሌ እንደማለት ነው።

ከኅዳር ፮ እስከ ታኅሣሥ ፮ ዘመነ አስተምህሮ ይባላል (ትምህርቱም ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በመባል ይታወቃል።)

ከኅዳር ፮ እስከ ኅዳር ፲፪ አስተምህሮ ይባላል

ከኅዳር ፲፫ እስከ ኅዳር ፲፱ ቅድስት ይባላል

 

ከኅዳር ፳ እስከ ኅዳር ፳፮ ምኩራብ ይባላል

ከኅዳር ፳፯ እስከ ታኅሣሥ ፫ መፃጉዕ ይባላል

ከታኅሣሥ ፬ እስከ ታኅሣሥ ፮ ደብረ ዘይት ይባላል

(ለሦስት ቀናት ብቻ ነው)

 

ከታኅሣሥ ፯ እስከ ታኅሣሥ ፲፫ ዘመነ ስብከት ይባላል

ከታኅሣሥ ፲፬ እስከ ታኅሣሥ ፳ ዘመነ ብርሃን ይባላል

ከታኅሣሥ ፳፩ እስከ ታኅሣሥ ፳፯ ዘመነ ኖላዊ ይባላል

ታኅሣሥ ፳፰ እና ታኅሣሥ ፳፱ ልደት ተብለው ይጠራሉ።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤

ወለመስቀሉ ክቡር

መጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ አሐዱ አስረስ