ነገረ ማርያም ከሁለት ቃላት የተገኘ ነው። ነገር፣ የአንድን ትምህርት መግለጫ አጉልቶ የሚያሳይ ሲሆን ማርያም፣ የእመቤታችን መጠሪያ ስም ነው። በመሆኑም ነገረ ማርያም ማለት በእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እግዚአብሔር ወዶ ፈቅዶ ለሰው ልጅ የገለጠውን ምሥጢር የምንማርበት ትምህርት ነው። ስለ እመቤታችን ያለው ትምህርት እጅጉን ሰፊ ስለሆነ በዚች መልእክት ላይ ነገረ ማርያምን ለማስፈር አይሞከርም። አባይን በጭልፋ ቀድቶ መጨረስ እንደማይቻል ሁሉ የእመቤታችንንም ነገር አስተምሮ ለመጨረስ አይቻልም። ነገር ግን በዚህ መልእክት ሦስት አበይት ነጥቦችን እናነሳለን። እነርሱም፦
፩. የቅድስት ድንግል ማርያም የትውልድ ሐረግ
፪. የድንግል ማርያም የስሟ ትርጓሜ
፫. እመቤታችን የምትታወቅባቸው ተጨማሪ ስሞች
፩. የቅድስት ድንግል ማርያም የትውልድ ሐረግ
እግዚአብሔር አምላክ ማደሪያው ሁሉ ንጹሕና ቅዱስ ፍጹምም ነው።ስለሆነም እርሱ ያደረበት ሰውም ሆነ ቦታ ወይም ንዋይ ሁሉ ቅዱስ ይባላል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ ማደሪያ ሆና ስለተገኘች ቅድስት ትባላለች። የተገኘችውም እግዚአብሔር ካደረባቸው ቅዱሳን ስለሆነም ጭምር ቅድስት ተብላለች።
፪. የድንግል ማርያም የስሟ ትርጓሜ
ማርያም ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ማሪሃም ከሚለው ቃል የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም የብዙኃን እናት ማለት ነው፤ አብርሃም
ማለት የብዙኃን አባት ማለት እንደሆነ። (ዘፍ. ፲፯፥፭) በቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት የቅድስት ድንግል ማርያምን ስም እንደሚከተለው ያመሰጥሩታል፦
ማርያም ማለት፦
ሀ. መርሕ ለመንግሥተ ሰማያት (ወደ መንግሥተ ሰማያት መርታ የምታገባ) ማለት ነው፦
የአዳም ዘር በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ወደ ገነት የገባው ወይንም ወደ ቀደመ ክብሩ የተመለሰው ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሷን ሥጋ ተዋሕዶ በመወለዱ ስለሆነ እንዲሁም ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚያስገባው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙም ከርሷ የነሣው በመሆኑ ነው። በተጨማሪም የድንግል ማርያምን አማላጅነት ሳያምኑ መንግሥተ ሰማያት መግባት አይቻልምና ነው።
ለ. ጸጋና ሐብት ማለት ነው፦
የእመቤታችን ወላጆች ለጊዜው በመምከናቸው በሰው ዘንድ ተንቀው የነበሩ ሲሆን የእርሷ መወለድ ሀብት እና ጸጋ ሆኗቸዋል። ፍጻሜው ግን አማላጅነቷን ዐውቀው ቃል ኪዳኗን አምነው ለሚመጡ ምእመናን ሁሉ ሀብት እና ጸጋ ሆና ተሰጥታለች። (ዮሐ ፲፱፣ ፳፯) በበደሉ ምክንያት ከጸጋ እግዚአብሔር ተራቁቶ በእግረ አጋንንት ይቀጠቀጥ የነበረው አዳም ጸጋው ተመልሶለት ሀብተ መንፈስ ቅዱስን ገንዘብ ያደረገው በእመቤታችን በኩል ነው። “አዳም ከገነት በተባረረ ጊዜ ተስፋው አንቺ ነሽ” ብሎ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ያመሰገናትም ለዚህ ነው።
ሐ. በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ፍጽምት ማለት ነው፦
እግዚአብሔር በባሕርዩ ፍጹም አምላክ ስለሆነ ለምሥጢረ ሥጋዌ ሰው ይሆንባት ዘንድ በመለኮታዊ ጥበቡ የመረጣት በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ፍጽምት ትሆን ዘንድ ይገባልና በሥጋም በነፍስም ፍጽምት አደረጋት።
መ. ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች ማለት ነው፦
እግዚአብሔር በፈጠራቸው በመላእክትና በቅዱሳን ላይ በረድኤት ወይንም በጸጋ ነው ያደረባቸው። በድንግል ማርያም ላይ ግን በረድኤትና በጸጋ ብቻ ሳይሆን ከሥጋዋ ሥጋን፤ ከደሟ ደምን፤ ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ነው የተገለጠው(ሰው የሆነው)። ለዚህም ነው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” ያላት (ሉቃ ፩፣፳፰)። ስለሆነም ድንግል ማርያም ከመላእክትም ከቅዱሳንም ትበልጣለችና ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ ተብላለች።
ሠ. የብዙዎች እናት ማለት ነው፦
አንድ ቤት የቤት እመቤትና አባወራ እንዳለው ሁሉ በክርስቶስ አምነው ላሉ ክርስቲያኖች ሁሉ እመቤታቸው (እናታቸው) ድንግል ማርያም ናት፤ የቤታቸው ራስ ልጇ አማኑኤል እንደሆነ ማለት ነው።
ረ. በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የምትላላክ ማለት ነው፦
ለሰዎች በሥጋ ዘመዳችን ስትሆን ለፈጣሪ ደግሞ እናቱ ነች፤ በመካከል ሆና የምታገናኘን ወይንም የምታማልደን ስለሆነች በሰውና በፈጣሪ መካከል ያለች መካከለኛ ትባላለች። የሰውን ልመና ወደ እግዚአብሔር፣ የእግዚአብሔርንም ይቅርታ ወደ ሰው በማድረስ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ፣ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እያማለደች ታሰጣለችና።
፫. እመቤታችን የምትታወቅባቸው ተጨማሪ ስሞች
እመ አምላክ ወላዲተ አምላክ
ኪዳነ ምሕረት ቤዛዊተ ዓለም
እምነጽዮን ሰአሊተ ምሕረት
ሶልያና አዶናዊት
መጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ አሐዱ አስረስ