ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ከቦታ ቦታ እየተመላለሰ ካከናወናቸው ድርጊቶች አንዱ ደቀ መዛሙርትን እንዲሁም ሌሎችን አርድእት (ረዳቶችን)በመምረጥ ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ ነበር። በምክርም ሲያጸናቸው የሚልካቸው እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እንደሆነና ሥራቸውም ቀላል እንዳልሆነ አስተምሯቸዋል። ወደ ከተሞች በመሄድ በዚያ ድውይ እንዲፈውሱና የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማሩ ወደ መንግሥቱ እንዲያቀርቡ ሥልጣን ሰጣቸው።በተለይም አጋንንት በእርሱ ስም ከሰዎች እንዲወጡ ማድረጋቸው ያስደሰታቸው አርድእት፥ “ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል” ባሉት ጊዜ ጌታችን ሲመልስ “... በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጎዳችሁም ምንም የለም። ነገር ግን መናፍስት ስለተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ስለተጻፈ ደስ ይበላችሁ።” ብሏቸዋል። (ሉቃ ፩፥ ፱-፳)
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ክርስቶስ አካልነቷ እርሱን ወክላ እንደ እርሱ ሆና እንድትኖርና እንድትሠራ ጌታ ፈቅዶላታል። ቤተ ክርስቲያንንም እንዲጠብቋት የሾማቸውን ሐዋርያት የእርሱ እንደራሴዎች አድርጓቸዋል። ይህንም ሲያሳይ ጌታችን በመጀመሪያ ለሐዋርያት፣ ቀጥሎም ለተተኪዎቻቸው "የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፥ እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል፤ እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል።" ብሏቸዋል። (ሉቃ ፲፥፲፮) የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ካህናት፥ ምእመናኑን ለመጠበቅና ለማስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። በተለይም መንጋውን በመጠበቅ ለነፍሳት አባትና እረኛ ለሆኑት ሁሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት እንደሚጠብቃቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያስጠነቅቃል። (የሐዋ ፳፥፳፰-፴)
በቤተ ክርስቲያን ለሚካሄዱት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተግባራት መሳካት ካህናት ብቻ ሳይሆኑ ምእመናንም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ይህም ክፉውን በማስወገድ የቅድስናን ኑሮ በመኖርና መልካም አርአያነትን በማሳየት፥ የፍቅርና የጽድቅን ሥራ በመሥራት፥ ችግረኞችን በመርዳት፥ ምጽዋትና ልዩ ልዩ አስተዋጽኦ በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጎልቶ የሚታይ ኃላፊነት አለባቸው።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሁላችንም ናት። በጠቅላላ ጉባኤው የተመረጡት አሥራ አንዱ የሰበካ ጉባኤ አባላት የሚያወጡትን የሥራ ዕቅድ መተግበር የሚችሉት የሁላችንም ድጋፍ ሲጨመርበት ብቻ ነው። እግዚአብሔር አምላካችንም ይህን መተባበራችንንና አንድነታችንን ሲመለከት በበለጠ በረከት ያትረፈርፈናል። በተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎች ውስጥ እያገለገልን የምንገኝ አባላት ስማችን በሰማያት ስለተጻፈ እጅግ በጣም ደስ ሊለን ይገባል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወደፊትም ቢሆን የጀመረችውን ይህን መጠነ ሰፊ አገልግሎት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መቀጠል ያስችላት ዘንድ ከሁላችንም ያላሰለሰ መንፈሳዊ ትጋት ያስፈልጋል። ጌታችን ለአርድእቱ እንዳስተማረው ምድራዊ ምሥጋናን በመናቅ ሰማያዊውን ሀብት በመሻት እስከ መጨረሻው ተሳትፎአችንን መቀጠል ይኖርብናል። በተለይም ደግሞ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ላለብን የሀገረ ስብከት ስብሰባ አስተናጋጅ አጥቢያ እንደመሆናችን ከካህናቱ አንሥቶ ማንኛውም ምእመን በኅብረት መሳተፍ ይኖርብናል፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በመገንባት ለሀገረ ስብከት ስብሰባ መመረጣችንን በማሰብ አገልግሎታችንን እናጠናክር።እግዚአብሔር አምላክ የጀመርነውን አዲስ ምዕራፍ እስከመጨረሻው ጠብቆልን የመንግሥቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ የእርሱ ቅዱስ ፈቃድ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን በረከት አይለየን፥ አሜን።
ወይትባረክ አምላከ አበዊነ
የርእሰ ደብሩ ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ