ማንኛውም ቤተሰብ ልጆቹ አድገው ጥሩ ደረጃ እንዲደርሱለት መልካም ምኞቱ ነው። ይሁንና ቤተሰብ እንደተመኘው ልጆች ሁሉ የቤተሰብን ፍላጎት ይዘው ያድጋሉ ማለት ግን ያስቸግራል። ለዚያም ነው አባቶች ሲመርቁ "የተባረከ ልጅ ይስጥህ" የሚሉት፤ እርግጥም ትልቅ ምርቃት ነው።
የተባረከ ልጅ ከሚለው ተነስቼ የዛሬ ጽሑፌን "የተባረክ ቤተሰብ" ብዬ ባቀርብ ማጋነን አይሆንብኝም። የዛሬ እንግዳዬ እነሆ ታዳጊ ወጣት እግዚእኃርያ ይልማ በቅፅል ስሟ (እኑዬ )በመባል ትታወቃለች።
የሊቀ መዘምራን ይልማ ኃይሉ እና የወ/ሮ ኂሩት ገዛኸኝ የበኵር ልጅ ነች። እኑዬ በይዘቱ የመጀመሪያ እና ልዩ የሆነ የአባቷን የሊቀ መዘምራን ይልማ ኃይሉን የአማርኛ መዝሙር በእንግሊዝኛ ይዛ የቀረበች ታዳጊ ወጣት ነች።
እርግጥ ነው የዚህችን ታዳጊ ሥራ ስናስብ ወዲያው ብልጭ የሚልብን ማናት? የማናት ልጅ? ቤተሰቦችዋ እነማን ናቸው? የሚለው ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። በእርግጥም ለዚህ ሥራ መሳካት ትልቅ ሚና የተጫወቱትን ቤተሰቦችዋን ለማግኘት ነው በቅድሚያ ያሰብነው።
እንደሚታወቀው ሊቀ መዘምራን ይልማ በአገልግሎት ሕይወቱ በጣም የተጠመደ በመሆኑ ምንም እንኳን ጥሪዬን ተቀብሎ ሊያነጋግረኝ ቢሞክርም በተለያዩ የፕሮግራም መደራረብ ምክንያት ሳንገናኝ ቀርቷል። ይሁንና የቤቱም፣ የውጪውም፣ የቤተ ክርስቲያኑም አገልግሎት አጠነከረኝ የምትለው ወ/ሮ ኂሩትን አግኝቼ ለማነጋገር እድሉን አግኝቻለሁ።
ትሁትና ሰው አክባሪ የሆኑት፣ ፍልቅልቅ፤ ሁሌም ፈገግታ የማይለይው የወ/ሮ ኂሩት ፊት አሁንም ድቅን ይልብኛል።
ጥያቄ- እንዬ አስተዳደግዋ እንዴት ነበር?
ወ/ሮ ኂሩት ለመመለስ አልተቻኮሉም ነበር፤ ቆዘም እንደማለት ብለው ደስ የሚል አዓናቸውን አንዴ ልጃቸውን አንዴ እኔን እያዩ ሰው ያለውን ነው የሚሰጠው እኔ ያለፍኩበትን ሕይወት ልጆቼ እንዲያልፉብት በጣም እፈልጋልሁ፤ እመኛለሁ። እንዬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ፍቅር ያደገች። ቅዳሴና ንግሥ በአላት ብቻ ሳይሆን፤ ማሕሌት እንዲያመልጣት የማትፈልግ፤ በልጅነት እድሜዋ የቤተ ክርስቲያን ፍቅር አድሮባት በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ያደገች ልጅ ናት።እንዬ እንደ ልጅ እንቅልፍ የማያታልላትና ብርድ የማይበግራት ፤ የሚኒሶታ ኔጋቲቭ ዲግሪ መቼም ጥያቄ ሆኖባት የማያውቅ ልጅ ናት ብል ማጋነን
አይሁንብኝ። የ2:00 A.M ማሕሌት ለመካፈል የመቀስቅሻ ሰዓቷን ለ12፡00 A.M. ሞልታ ማንም ሳይቀሰቅሳት እራሷ በርትታ ሌሎቻችንን የምታበረታ፥ ታላቅ እኅት፣ ልጅ፣ እንደ መካሪም ፣ እናትም ሆና ያደገች ልጅ ነች። ጥያቄ- እዚህ ተወልዳ ካደገች አማርኛ ቋንቋ እንዴት አላስቸገራትም?
ወ/ሮ ኂሩት- ትምህርት ቤት ሲዘጋ/ summer time/ እቤት ውስጥ ያለ ምንም መሰላቸት እንደ አንድ ፕሮጀክት ወስጄ አማርኛ ዕለት ዕለት ከሁለቱ ወንድሞችዋ ጋር አስተምራቸው ነበር። ሌላው ራሱን የቻለ የቤተሰብ ጊዜ አለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አለን ያ የበለጠ አማርኛውንም የእግዚአብሔርንም ቃል ለመማማር ረድቶናል። ልጅ እያሉም ለሁለት ዓመት ያህል ኢትዮጵያ ሄደው ከአያታቸው ጋር ለትንሽ ጊዜም ቢሆን አሳልፈዋል።
ጥያቄ- እንዬ ባሕሪዋ እንዴት ነው?
ወ/ሮ ኂሩት- ይሄን ጥያቄ ስመልስ እውነትም ከልጄ ፊት ወይም እሷ በሌለችበት የምናገረው እውነታ ነው። እንዬ በቃ "እናት" ናት ብዬ ነው የምገልጻት። ሰው አክባሪ፣ ከሰው ተግባቢ፣ አፍቃሪ፣ አዛኝ፣ ለጋሽ፣ ረዳት፣ ለታናናሾቿ አርአያ የምትሆን፣ ለሰው ልጅ መልካም የምታስብና መልካም ሥነ-ምግባር ያላት ልጅ ነች። ይገርማል! እግዚአብሔር የባረካት እንዬ ይኼ ሁሉ ስለሷ ሲባል ምንም ድንቅም አላላትም ነብር። ይልቁንስ በሃሳብ እናቷን ለመርዳት ስትሞክር ግርም እያለኝ ነበር የማስተውላት። ወደሷ ዞር አልኩና፦
ጥያቄ- እንዬ ይህንን ሥራ ለመሥራት ምን ነበር ያነሳሳሽ? መተርጎሙስ አላስቸገርሽም?
እንዬ - ፈጠን ባለና በሚጣፍጥ ጉራማይሌ እ ኖ! ኖ! ምንም አላስቸገረኝም።
ይህ ሥራ አዲስ አይደለም። ለሕዝብ ተሠርቶ አለመውጣቱ ነው እንጂ ከሠራሁት በጣም ቆይቻለሁ። ሲጀመር የአባቴን ካሴት መዝሙር ሰስማ ነው ያደኩት፤ ሲቀጥል ደግሞ ሁልጊዜ ከማዳመጤ የተነሳ ከቦታ ቦታ ሰንሄድና ከወንድሞቼ ጋር መኪና ውሰጥ ሆነን “ዜማው እንዲህ ቢሆንስ ምቱ እንደዚህ ቢቀየርስ፣ ቀጥተኛ የመዝሙሩን ትርጉም እየተረጎምን በእንግሊዝኛ እንደዚህ ብንዘምር” እያልን ቃላት እየቀያየርን እንዘምራለን። ልምዱና ፍላጎቱ ከዛ የመጣ ሲሆን ትርጉም ላይ ያለ ማጋነን ምንም አልተቸገርኩም ነበር።
ምክንያቱም እናቴና አባቴ ከጎኔ ናችውና። ለምጠይቀው ጥያቄ ሁሉ መልስ አገኛለሁ። ሌላው መጽሐፍትና መዝገበ ቃላት በጣም አገላብጣልሁ፤ አነባለሁ። የቤተ መጻሕፍት ቤትም ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል ለመረጃና ለትርጉም። በተቻለኝ አቅም የአባቴን የአዘማመር style ለመከተል ሞክሬያለሁ። አንዳንድ ጊዜ ግን ከአማርኛ ቀጥታ ወደ እንግሊዘኛ ለመቀየር የሚያስቸግሩትን ዜማዎች እኔን በተመቸኝ መልኩ አድርጌ አቅርቤዋለሁ።
ጥያቄ- ካሴት ሲዲውን ከማውጣትሽ በፊትና በኋላ ያለው የሰው አመለካከትና ግንዛቤ እንዴት ነው? ያስተዋልሽው ነገር ካለ? ድጋፍ ወይም ማስተካከያ የሰጠሽ አለ?
እንዬ- እውነት እውነት የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት መጠበቅ የሚወድ፣ ሥርዓቱ የተጓደለ ሲመስለው የሚቆጣን ኅብረተሰብ እንዳስተውል አድርጎኛል። ባጋጣሚ ሲዲው ከመታተሙ በፊት ለሲዲው የሽፋን ሰእል አስበነው የነበረው አሁን ካለው የተለየ ነበር። ይኽውም ባጋጣሚዎች አለመመቻቸትና በነገሮች አለመስተካከል ያሰብነው ሳይሆን ያልታሰበው ምስል የሽፋን ሰእል ሆኖ ወጣ።
በአጋጣሚ ተነስቸው የነበረ የኔ ፎቶ ሲሆን ይሀ ፎቶ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልግሎት ላይ ሆኜ ያለ ምስል አልነበረም፤ ነገር ግን ይህ ፎቶ ብዙዎችን ጥያቄ አስነስቶባቸዋል። እኔ ግን የሰማሁዋቸውን ሐሳቦች ሁሉ "እውነት ነው ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ከማሰባቸው ነው" ብዬ ጠቃሚነቱን ተቀብዬ አልፌዋለሁ። ግን በሥርዓት በኩል እግዚአብሔር ይመስገን ሁሉንም ጠንቅቄ አውቃለሁ እናትና አባቴ ምስጋና ይግባቸው።
ከትምህርት ሰጪነቱ ጎን አያይዛ ደግሞ እዚህ ሀገር የተወለዱ አንዳንድ ሕፃናትና ወጣቶች መዝሙር ሲዘምሩ ትርጉሙ ሳይገባቸው ነበር የሚያልፉት አሁን ግን ደስ ብሏቸው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ትርጕሙ ገብቷቸው ሲዘምሩ ስሰማ ውስጤን ደስ ይለዋል።
ብዙዎች "THANK YOU ደስ ብሎናል" ያሉኝም አሉ። ካሴቱ በብዙዎች ተደማጭ ነው ለሌሎች መማሪያ፣ አማርኛ ለማይናገሩ ግን ስለ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዝሙር ማወቅ ለሚፈልጉ ትልቅ አስተማሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁና እግዚአብሔር ይመስገን።
ጥያቄ- ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን እየሠራሽ ነው ለመሥራትስ የምታስቢው ነገር ካለ?
እንዬ- ዲዛይን ማድረግ አርት ነገር በጣም ደስ ይለኛል ከዚህ ቀደምም የሠራኋቸው ዲዛይን ሥራዎች አሉኝ፤ በምኖርበት ካውንቲ አርት ሴንተር ውስጥ ለሕዝብ ዕይታ ቀርቧል። ወደፊትም በዛ መቀጠሉን እፈልጋለሁ።
ሌላው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ቤተስብ የሌላቸውንና እርዳታ ለሚፈልጉ ሕፃናት እርዳታ ማድረግ እወዳለሁ።
ከዚህ በፊት ከምማርበት ትምህርት ቤት አስተባብሬ በአዲስ አበባ የሚገኙ በአራዳ ክፍለ ከተማ ትምህርት ቤት ውስጥ ታዳጊ ሕፃናትን በቁሳቁስና በሚያስፈልጋቸው ረድቻለሁ። እሱንም ቀጣይ የሚሆንበትን መንገድ ወደፊት ለመቀጠል አስባለሁ። በወጣትነቴ ብዙ መሥራት አስባለሁ፤ በእኔ መጠቀም የሚችሉ ካሉ መጥቀም እፈልጋለሁ። ከሁሉ በበለጠ እግዚአብሔርን ለማገልገል እፈልጋለሁ "ALL ABOUT GOD" ወንድሞቼን፣ እናትና አባቴን በጣም እወዳቸዋለሁ፤ አመስግናቸዋለሁ። በሁሉ ነገር ስለሚረዱኝ በበለጠ ደግሞ እናቴ (MY BEST FRIEND) አሰልጣኜ፣ አማካሪዬ፣ ጓደኛዬ ነች። አባቴም HE IS MY ROLE MODEL በጣም እወደዋለሁ ብላለች።
እውነት ለመናገር ከዚህ የተከበረ ቤተሰብ ጋር የነበረኝ የሁለት ሰዓት ቆይታ ቃለ መጠይቅ ሳይሆን አንድ የሥነ-ምግባር አጭር ኮርስ የምወስድ ያህል ነው የተስማኝ። ቆይታችን ልዩ በተመስጦ ልብ የሚማርክ ከመሆኑ አንዳንድ ጊዜ ሳላስበው የእንባ ዘላላዎች ሳብስ አገኘው ነበር እራሴን። እውነት ለመናገር ወደፊት ሰፋ ባለ መድረክ ይኼን ቃለ መጠይቅ ይዤ ለመቅረብ ቃል እገባለሁ። በቦታ እጥረት ብዙ ቆርጠናልና። ስለ እንዬ ወንድሞች ኢያቄምና ይኩኑ አምላክ ራሱን የቻለ አንድ ወጥ ጽሑፍ አለኝና።
እውነት ይህ ቤተሰብ በተለየ መልኩ እግዚአብሔርን ሲያገለግል እግዚአብሔርም ይህን ቤት እየባረከ እና እያገለገለ እንዳለ በፍጹም መገመት አያዳግትም። ከፍ ያለ ምስጋና ለወ/ሮ ኂሩት ገዛኸኝ፣ ለሊቀ መዝምራን ይልማ ኃይሉ ከሄደበት ከኖርዌይ ድረስ እየደወለ በማናገር ለረዳኝ፣ ልዩ የሆነ ሥራ ይዛልን ለቀረበችው ታዳጊ ወጣት እግዚእኃርያ ይልማ ታላቅ አክብሮቴን አቀርባለሁ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን!
በወ/ት ዘመናይ ዘሪሁን