ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በሠላሳ ዓመቱ ለድኅነተ ዓለም አንድም ለአብነት በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቋል። ያጠመቀውም ዮሐንስ ወልደ ዘካርያስ ነው። በተጠመቀ ጊዜ የባሕርይ አባቱ አብ በደመና ሆኖ "በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው" ብሎ መስክሮለታል። መንፈስ ቅዱስም በጸዓዳ ርግብ አምሳል በራሱ ላይ ተቀምጧል። ማቴ፣ ፫፥ ፲፫–፲፯
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ቅዱስ ዕለት በዓል ሠርታ በየዓመቱ በማኅሌትና በቅዳሴ በተለየ ሁኔታ ታከብረዋለች። ይህ በዓል በሚከበርበት ጊዜ በዋዜማው ታቦታቱ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወጥተው በወንዝ ዳር /በሰው ሰራሽ የውሃ ግድብም ቢሆን/ በዳስ በድንኳን ያድራሉ። ሌሊት ስብሐተ እግዚአብሔር ሲደርስ አድሮ ሥርዓተ ቅዳሴውም ይፈጸማል። ሲነጋ በወንዙ ዳር ጸሎተ አኰቴት ተደርሶ አራቱም ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ውኃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል። አንዳንድ ደካሞች የጠበሉን መረጨት አይተው "የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ታጠምቃለች" ብለው የሚተቹ አሉ። ነገር ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ይህን የምትፈጽመው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ብሎ ያሳየውን ትሕትና ለመመስከርና፣ ምዕመናንን የጌታን በረከተ ጥምቀት ለማሳተፍ እንጂ የተጠመቁትን ምዕመናን እየመላለሰች በየዓመቱ አታጠምቅም።
ጥምቀት አሐቲ መሆኗን ታውቃለችና። ኤፌ፣ ፬፥፬ እርግጥ ያልተጠመቁ አረማውያንና ሌሎችም የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ጊዜ እየመጡ በክርስቶስ አምነው ይጠመቃሉ።ጥምቀት የሚከበረው በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን ነው። ጥምቀት ረቡዕ ቢውል ገሀዱ ማክሰኞ አርብ ቢውል ገሐዱ ሐሙስ ለውጥ ሁኖ ይጦማል። ጥምቀት የሚውልባቸው አርብና ረቡዕ ስለ በዓሉ ታላቅነት ፍስክ ይሆናሉ። ጥምቀት በፍስክ ቀናት ቢውልም ዋዜማው ይጾማል። በበዓለ ጥምቀት የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድ ጌታ በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱ ምሳሌ ነው።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ የተጠመቀው ስለ ሁለት ነገር ነው፦
፩ኛ• ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት "ባሕር አየች ሸሸችም፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ" ብሎ
የተናገረውን ትንቢት በእርሱ ጥምቀት ለመፈጸም። መዝ፣፻፲፫፥፫
፪ኛ• በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤያችንን እንደ ሰውነቱ ረግጦ፤ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ ሊደመስስልን።
ምሥጢረ ጥምቀት
ጥምቀት ሰው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቆ የእግዚአብሔር ልጅ የሚሆንበት ታላቅ ምሥጢር ነው። ማቴ፣ ፳፰፥፲፰ ይህ ምሥጢር ከምሥጢራት ሁሉ የመጀመሪያ ነው። ምሥጢር መባሉም በዓይን በሚታይና በጆሮ በሚሰማ አገልግሎት በዓይነ ሥጋ የማይታይና በዕዝነ ሥጋ የማይሰማ ጸጋ ስለሚገኝበት ነው። አገልግሎቱ ሲፈጸም ይታያል፣ ይሰማል፤ ተጠማቂው ከውኃና ከመንፈስ ተወልዶ የልጅነት ጸጋ ሲያገኝ ግን አይታይም፣ አይሰማም። ይህ ምሥጢር የሌሎች ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ በር ነው። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ጌታችን በወንጌል "ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም" ብሏል። ዮሐ፣ ፫፥፯ ይኸንን ነው ጌታችን ዳግም ልደት ያለው ዮሐ፣፫፥፫ የመጀመሪያው ልደት ከአባት አብራክና፣ ከእናት ማኅፀን በሥጋ መወለድ ሲሆን ሁለተኛው ልደት ግን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስና፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ረቂቅ በሆነ ልደት በመንፈስ መወለድ ነው። ይኸንንም ጌታችን "ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው።" ብሎታል። ዮሐ፣፫፥፮
በጥምቀተ ክርስትና የምንጠመቀው ጥምቀት የተመሠረተው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጌታ ጥምቀትን ራሱ ከፈጸመ በኋላ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ በማለት ጥምቀተ ክርስትናን እንደመሠረተ፣ ሰው ዳግመኛ ከውኃና፣ ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ እንደማይችል ከላይ በተቀመጡት ጥቅሶች ተመልክተናል።
በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት መሠረት ሁለተኛ መወለድ ማለት እንደገና ወደ እናት ማሕፀን ተመልሶ በሥጋዊና በደማዊ ፈቃድ መወለድ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ረቂቅ ልደት ማለት /የነፍስን ልደት/ መወለድ መሆኑን ታውቋል። ከእግዚአብሔር የመወለድ ጸጋ የሚገኘውም በጥምቀት መሆኑ ተረጋግጧል። ይህ ከሆነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከማይጠፋ ዘር የምንወለደውን ልደት ወንድ ልጅ በተወለደ በ፵ ቀኑ ሴት ልጅ በተወለደች በ፹ ቀኗ ታጠምቃለችእንዲሁም ዘግይተው የመጡትን ግን እንደ አመጣጣቸው አንድነቱን ሦስትነቱን፣ አምላክ ሰው፤ ሰው አምላክ መሆኑን ተምረው ካመኑ በኋላ ታጠምቃቸዋለች። ማር፣ ፲፮፥፲፮ ይህ ከእግዚአብሔር የመወለድ ጸጋ የተገኘውም በሃይማኖት ነው። ክርስቶስን አምላክ ወልደ አምላክ ነው ብሎ በሃይማኖት ያልተቀበለ ከእግዚአብሔር መወለድ አይችልም። ለአመነና በሃይማኖት ለተቀበለ ግን ይችላል።
ወንጌላዊው ዮሐንስ ይኽንን ታላቅ የመዳን ምሥጢርና ከእግዚአብሔር ልጅነትን የማግኘትን ስልጣን ሲያስረዳ «ሰውን በአርአያችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር ብሎ ወደ ፈጠራቸው ወገኖቹ ወደ አዳም ልጆች፣ የበኲር ልጆቼ ናችሁ ወደ አላቸው ወደ እስራኤል መጣ። እነሱ ግን አልተቀበሉትም ማለትም አላመኑበትምና። ላመኑበት ግን በስሙ ያመኑ የእግዚአብሔር ልጆች ይባሉ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው።» ዮሐ፣፩፥፲፩–፲፫ በማለት አምልቶና አስፍቶ የጻፈልን። በዚህምመንፈሳዊ ልደታቸው ከሥጋዊ ከደማዊ ግብር ወንድና ሴት ተዋደው ከሚሠሩት ግብርም ያልተገኙ ናቸውና። በመንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ተወልደዋል እንጂ።
እንግዲህ የጥምቀትን በዓል ታሪኩንና፣ ምሥጢሩን በሚገባ በመረዳት በ፵ እና በ፹ ቀን በጥምቀት ያገኘነውን ልጅነት በመጠበቅ በመንፈሳዊ ሥርዓት ልናከብረው ይገባናል። ይህ ዕለት ሰማይ የተከፈተበት፣ የአብ ድምጽ የተሰማበት፣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል የተገለጠበት፣ ስመ ግብርናታችን ተደምስሶ የጸጋ ልጅነታችን የተመለሰበት፣ ተራሮች እንደ ኮርማዎች፣ ኮረብቶች እንደ ጠቦቶች የዘለሉበት ዕለት በመሆኑ ታላቅ ክብር አለው።
ሊቀ ብርሃናት ቀሲስ ሄኖክ ያሬድ