/፩ኛ ሳምንት ዘወረደ/

በዚህ ዕለት ነቢያት የሰበኩት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ስለ መውረዱና የማዳን ሥራው ስለመጀመሩ ይሰበካል። ቅዱስ ዮሐንስ በአንደኛ መልዕክቱ ምዕራፍ ፫፡፰ ላይ «የዲያብሎስን ሥራ ሊያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ» እንዳለው ጠፍቶ የነበረውን ሰው ወደ ቀደመ ክብሩ በእንዴት ያለ ሁኔታ እንደተመለሰ በሰፊው ይነገራል። አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷልና» (ሉቃ. ፲፱፡፲) በማለት የተናገረው ቃል በትምህርትና በዝማሬ ይነሣል። የሰው ልጆችም ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመፈጸም በትኅትናና በፈሪሃ እግዚአብሔር መኖር እንደሚገባን ከቅዱስ ዳዊት ቃል የመዝሙሩ ምስባክ ይደመጣል። እግዚአብሔር በፍርሓት እንድንገዛለትና እንድናከብረው ይሻልና የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛን በማስተዋል መኖር እንደሚገባን ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ በሚልክያስ አድሮ «ልጅ አባቱን፥ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ? (ሚልክያስ ፩፥፮) ብሎ እንዳስተማረን

በዚህ በመጀመርያው ሳምንት ከመዝሙረ ዳዊት ላይ የሚሰበከው ምስባክ፦

በግዕዝ፦    ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሐት

   ወተሐሰዩ ሎቱ በረአድ

   አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመአዕ እግዚአብሔር

በአማርኛ፦  ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥

   በረዓድም ደስ ይበላችሁ

  ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቈጣ። (መዝ. ፪፡፲፩-፲፪)

 

/፪ኛ ሳምንት ቅድስት/

ይኽ ሳምንት ቅድስት ተብሎ በመጠራት የሚታወቅ ሲሆን ከቅድስት ሰኞ ጀምሮ ፆመ ኢየሱስ በመባልም ይጠራል። በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዝማሬውም ሆነ ምስባኩ እንዲሁም ወንጌሉ ስለ እግዚአብሔር ቅድስና ይናገራል። የእግዚአብሔር ምሕረትና የሰንበት ቅድስናም በሰፊው ይጠቀሳል። በዚች በተቀደሰች ሰንበተ ክርስቲያን እግዚአብሔር የሰውን ልጆች የነፍስ ዕረፍት ሰጥቷቸዋልና ሰው ከባርነት ነፃ ወጥቶ በቅድስና መኖር መጀመሩ ይሰበክበታል። በተጨማሪም ሰው ሁሉ በቅድስና መንገድ በመመላለስ የክብሩ ባለቤት የመንግሥቱ ወራሽ እንዲሆን እግዚአብሔር እኔ ቅዱሳን ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ በማለት ስለማስተማሩ ሰፊ ትምህርት ይሰጥበታል። ለእግዚአብሔር ቅድስና የባሕርይ ገንዘቡ ነውና በአፈ መላእክት የሚጠራውና የሚቀደሰው በልሳነ ሰብእም (በሰዎች አንደበት) «ይትቀደስ ስምከ» (ስምህ ይቀደስ) እየተባለ የሚጠራው ስሙ ለዘላለም ቅዱስ ነው።

በዚህ በሁለተኛው ሳምንት ከመዝሙረ ዳዊት ላይ የሚሰበከው ምስባክ፦

በግዕዝ፦   እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ

  አሚን ወሰናይት ቅድሜሁ

ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ

በአማርኛ፦ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።

   ምስጋናና ውበት በፊቱ ነው፥

   ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው። (መዝ. ፺፭(፺፮) ፭

 

/፫ኛ ሳምንት ምኩራብ/

አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ እየገባ የወንጌልን ትምህርት እንዳስተማረ፤ ብዙ ድውያንን እንደፈወሰ፤ የሰንበት ጌታ እንደሆነ፤ የአባቴ ቤት የጸሎት ቤት እንጂ የንግድ ቦታ አይደለም በማለት በቤተ መቅደሱ አካባቢ የሚነግዱ ነጋዴዎችን ስለ መገሰጹ ትምህርት ይሰጥበታል። በተለይም ለታሰሩት መፈታትን፤ ለሞቱት ሕይወትን፤ ለተጠቁት ነፃነትን፣ በፍርድ ላሉ ሁሉ ምሕረትን ስለማስተማሩ፤ የሰሙትም በትምህርቱ ስለመገረማቸው ይገለጻል። ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስም ይኽን ድንቅ ትምህርት በአንክሮ እንዲህ ሲል ተናግሮታል፦ ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፥ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር። (ማቴ ፱፥፴፭)

በዚህ በሦስተኛው ሳምንት ከመዝሙረ ዳዊት ላይ የሚሰበከው ምስባክ፦

በግዕዝ፦   እስመ ቅንዓተ ቤተከ በልዓኒ

  ትዕይርቶሙ ለእለ ይትኤየሩከ ወድቀ ላዕሌየ

  ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ

በአማርኛ፦ የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፥

  የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና።

  ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፥ ለስድብም ሆነብኝ። መዝ. ፷፰፡፱

 

በአቶ አበጀ ሀደሮ