ሚ ላዕሌነ፤ ምን ገዶን?
(መሪጌታ ዘድንግል ለደጀ-ሰላም እንደጻፉት/ PDF)
ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ “አሜሃ ይከውን ኃዘን ዘኢይበቊዕ ኃዘን = ያን ጊዜ ኃዘን ይሆናል ግን የማይጠቅም ኃዘን ነው” እንዳለ የማይጠቅም ኃዘን የሚያዝኑ ብዙዎች ናቸው። ከነዚያው ዘንድ ቅሉ ይሁዳ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። ይሁዳ በፈጸመው እኩይ ግብር ኃዘን በተሰማው ጊዜ የሄደው ወደ ካህናቱ አለቆችና ወደ ሕዝቡ ሽማግሎች ነበር። በደሉንም መናዘዝ የጀመረው በደልን ፀነሰው፣ ወልደውና አሳድገው ለመዓርገ ሞተ ነፍስ ላደረሱና ላበቁ ፈሪሳውያን ነበር። በማቴዎስ 23፥15 “አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፣ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት ወዮላችሁ” ተብሎ እንደተጻፈ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ይሁዳን በክፉ ግብራቸው አጥምቀው የነሱ ፈጻሜ ፈቃድ/ፈቃድ ፈጻሚ ለማድረግ ብዙ ደክመዋል። ጨርሶ የድኅነት በር እንዳይከፈትለት አድርገው ለገሃነም ዳርገውታል። “ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም” እንዳለ ወንጌለ ዮሐንስ። (ዮሐ 16፥12)
ወደ እነዚህ ሰዎች ዘንድ ሄዶ ነው ይሁዳ ብሶቱን ለመግለጽ የሞከረው። የብዙ ጊዜ ሕልማችን ግቡን የመታው በዚህ ሰው ተሳትፎና ትብብር ነው ብለው ጊዜ ሰጥተው ሊያነጋግሩትና ሊያጽናኑት ፈቃደኞች አልነበሩም። እነሱ ምን ገዷቸው። ቢገዳቸውማ ንጹሕ እንዲፈስ ደሙ በእኛ በልጆቻችን ላይ ይሁን ብለው ይምሉ ነበርን? እነሱስ ይሁን ወደው በፈጸሙት ነው። ልጆቻቸው ምን አደረጉ? ኧረ ወዲያ እነሱ ምን ገዷቸው።
ዛሬም ይህንኑ ታሪክ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደገሙ ያሉ ሰዎች አሉ። እነዚህ በአየርም በመሬትም፣ በየብስም በባሕርም፣ በአራቱ ማዕዘን ሁሉ ይዞራሉ። ዓላማቸውም የሚቻል ከሆነ ቤተ ክርስቲያንን ከመሠረቷ አፈራርሶ መጣልና ትውልዱ የሚረከበው ሐዋርያዊ ትምህርተ ሃይማኖትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዳይኖር ማድረግ ነው። ይህን በማድረጋቸው ምን ይጠቀማሉ ቢሉ? ምን ገዷቸው የሚል ነው መልሱ። ቤተ ክርስቲያኒቱ ልብስ ጉርስ ሰጥታ፣ ጉባኤ ዘርግታ፣ መምህር መድባ፣ የአገልግሎት መድረክ ሰጥታ ለቁም ነገር ካበቃቻቸው በኋላ “ዘይሴሰይ እክልየ አንሥአ ሰኰናሁ ላዕሌየ፤ እህሌን የተመገበ ሰኰናውን በኔ ላይ አነሣ” እንዳለ ነቢዩ በሌሊት ከቤተ ጉባኤ እየወጡ ቤተ ክርስቲያን ሞታ የምትቀበርበትን ጉድጓድ ሲቆፍሩ ያድራሉ። በውስጣቸው ነጣቂ ተኵላዎች ሆነው ሳለ የበግ ለምድ ለብሰው ከእውነተኞቹ አገልጋዮች ጋር ተሰልፈው ይቆማሉ። እንኳን እግዚአብሔር እኛም አውቀናቸዋል። እስከ መከር አብረው ይደጉ የሚል አምላካዊ ቃል ስላለ የመከሩን ዘመን እየጠበቅን ነው እንጂ። ወይ ግሩም! መከሩማ ዕለተ ምጽአት አይደለምን የሚል ቢኖር አዎ እርግጥ ነው ግን እግዚአብሔር ሰይፈ በቀሉን በመናፍቃን ላይ የሚያነሣበት ጊዜ ሁሉ መከር ነው ብለን እንመልሳለን። ጉባኤ ኒቂያ፣ ጉባኤ ቁስጥንጥንያ፣ ጉባኤ ኤፌሶን የመከር ወቅቶች ነበሩና። ከስንዴው ጋር አብረው አድገው የነበሩ እንክርዳዶች በጥብዓተ ሃይማኖትና በነገረ ሃይማኖት ማጭድ እየታጨዱ በቃለ ግዘት ታስረው ወደማይጠፋው እሳት ተጥለዋልና።
ፈሪሳውያን ከቤተ መቅደስ እንዲወጣ ያደረጉት በይሁዳ እጅ ላይ የነበረውን ሠላሳ ብር ነው። (የሰጡት እነሱ መሆናቸው ሳይዘነጋ) የዛሬዎቹ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ግን እነሱ ከሚሞነጫጭሯቸው ምኑናት/የተናቁና የተዋረዱ መጣጥፎቻቸው በቀር ምንም አይነት ነገር በቤተ ክርስቲያን እንዲኖር አይፈልጉም።
እስቲ ከሞነጫጨሯቸው አንዱን እናንሣ። «ፋሲካችን ማነው? ክርስቶስ ወይስ ማርያም» የሚለውን ጥያቄ በማንሣት በበዓለ ሃምሳ ቅድመ ጸሎተ ኪዳን የሚደርሰውን «ለአዳም ፋሲካሁ፤ የአዳም ፋሲካ» የሚለውን የምስጋና ክፍል ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድርሰት ነው በማለት ካህናቱ ምሥጢሩን ሳይረዱ፣ ምን ያህል ስህተት እንደሆነ ሳይገነዘቡ በልማድ በዜማ ስለሚሉት የዚህ ድርሰት ችግር ሳይታያቸው ያለምንም ቅሬታና መሳቀቅ አፋቸውን ሞልተው ያዜሙታል እያሉ የድንቁርናቸውን ጣሪያ ያሳዩናል። ምን ገዷቸው። «ልጅ ለናቷ…» አይደል የተባለው።
ካህናቱ የዚህ ኃይለ ቃል ምሥጢር ካልገባቸው እነሱን ከሰማይ መልአክ ወርዶ አስተምሯቸው ነው? ወይስ እነርሱ ራሳቸው ከሰማይ ወርደው ይሆን? ይህ ሥርዓት የሚከናወነው በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ብቻ ቢሆን ጥያቄያቸው ለውይይት በቀረበ ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለችበትና ካህናቶቿና ምእመናኖቿ ባሉበት የሚከናወን ልዩ ሥርዓተ ጸሎት ነው። አስተውሉ! «ካህናቱ» የሚለው ቃል ከላይ እስከታች ያሉ አገልጋዮችን የሚወክል ቃል ነው። እንዳው በኔ ሞት አላዋቂ ማነው? መልሱን ለአንባቢ።
ፋሲካ ማለት ምን ማለት ነው?
1· እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ ብሎት ነበር። «ትበልዕዎ በጒጒዓ እስመ ፋሲካሁ ለእግዚአብሔር = የእግዚአብሔር ፋሲካ ነውና በፍጥነት ትመገቡታላችሁ» ዘጸ 12፥11፤ የእግዚአብሔር ፋሲካ የተባለው እስራኤል በቤታቸው የሠዉት በግዓ ፋሲካ ነው።
ዕዝራም «በሙሴ መጽሐፍ እንደተጻፈው በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕርጋቸው ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው አቆሙ ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አደረጉ ካህናቱና ሌዋውያኑም አንድ ሆነው ነጽተው ነበር። ሁሉም ንጹሐን ነበሩ ለምርኮኞቹም ሁሉ፣ ለወንድሞቻቸውም ለካህናቱ፣ ለራሳቸውም ፋሲካውን አረዱ» ብሏል። ዕዝራ 6፥18-20፤
ስለዚህ በዚህ ክፍለ ንባብ መሠረት ፋሲካ ማለት አንደኛ፦ በዓልን የሚያመለክት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ለበዓሉ የሚቀርበውን መሥዋዕት ያመለክታል።
2· ደስታ ማለት ነው። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ «ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ክርስቶስ = ምድር በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካን ታደርጋለች» ብሎ ዘምሯልና። የዚህ ክፍለ ንባብ ምንጭ «ይትፌሣሕ ሰማይ ወትትሐሠይ ምድር = ሰማይ ደስ ይለዋል ምድርም ደስ ይላታል» የሚል ነው። ሥረወ ቃሉም የሚገኘው በኢሳይያስ 44፥23 ላይ ነው። ስለዚህ ፋሲካ ማለት ደስታ ማለት ነው።
3· ማዕዶት ወይም መሻገሪያ ማለት ነው። «ፋሲካ ብሂል ማዕዶት ብሂል በዘቦቱ ዓዶነ እሞት ውስተ ሕይወት = ፋሲካ ማለት ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገርንበት ማዕዶት ማለት ነው» ብሎ እንደዘመረ ቅዱስ ያሬድ።
4· ቀዳማዊ ሕግ ማለት ነው። «ዛቲ ፋሲካ ቀዳሚት ሕግ = ይህች ፋሲካ የሕግ መጀመሪያ ናት» እንዲል።
5· የትንሣኤው መታሰቢያ ነው። «ፋሲካ ፋሲካ ፋሲካ ተዝካረ ትንሣኤሁ ለመድኃኒነ = ፋሲካ የመድኃኒታችን የትንሣኤው መታሰቢያ ናት» እንዲል።
6· ትንሣኤ ማለት ነው። «ትንሣኤ ሰመያ ለበዓለ ፋሲካ = የፋሲካ በዓልን ትንሣኤ ብሎ ሠየማት» እንዲል። ትንሣኤም ሁለት አይነት ነው። ትንሣኤ ልቡናና ትንሣኤ ዘጉባኤ።
በውኑ መንፈሳዊ እረፍትና ደስታ ለማግኘታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደእኛ ለመምጣቱ ምክንያት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አይደለችምን? ፀረ ማርያም አቋም ያላቸውና ነዳያነ አእምሮ የሆኑ ይህ አይዋጥላቸውም ይሆናል። ለነገሩ ምን ገዷቸው።
ከላይ ፋሲካ ማለት ቀዳማዊ ሕግ ማለት ነው ማለታችን ይታወሳል። የመጀመሪያውን ቃለ ብሥራት በመስማት እመቤታችን ዓለሙ በኃዘን እንዳይጠፋ «ይኩነኒ = ይደረግልኝ» በማለት ቀዳማዊት አይደለችምን። ከሷ ተወልዶ ዓለሙን ከወደቀበት መርገም እንደሚያድነው ሲነግራት እራሷን አሳልፋ አልሰጠችምን? ከዚህ በላይ ፋሲካ መሆንና መባል ከወዴት አለ? ልጇን እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስን ራሱን ለመስቀል አሳልፎ በመስጠቱ ፋሲካችን ስንለው እሷንም ለእግዚብሔር ፈቃድና ዓላማ ለእኛም የዘለዓለም ሕይወት ምክንያተ ድኅነት ለመሆን ራሷን አሳልፋ ስለሰጠች የአዳም ፋሲካ እንላታለን።
ሌላው ይህን ክፍለ ጸሎት ለመንቀፍ የተዘጋጁ ሰዎች የራሳቸው የሆነ ችግር አለባቸው። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፦
1፣ ይህ ጸሎት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚጸለው በቃል ነው። በቃል ለማጥናት ደግሞ ትጋትና ማስታወስ አስፈላጊ ነው። እነዚህ ሰዎች ሙሉ ጊዜያቸውን የሚያውሉት ለከንቱ ወሬና ለከርሣቸው የሚሆን ፍርፋሪ ለመፈለግ ስለሆነ አይሆንላቸውም። ከሊቃውንቱ ጋር አብረው ቆመው መጽሐፍ ዘርገተው ቢታዩ ደግሞ ውርደት ይመስላቸዋል። እነዕገሌ ሁሉ በቃላቸው ነው ምነው እናንተስ ከሚለው ጥያቄ መሸሽ ይፈልጋሉ። ከማን አንሼ አይነት ነገር ይመስላል።
2፣ የአገልግሎት ፍቅርና መንፈስ ጨርሶ የላቸውም። እንቅልፋሞችም ናቸው። ተርእዮ ይወዳሉ። ሰው በሚበዛበት ጊዜና መድረክ እንጂ መገኘት የሚፈልጉት በተመስጦ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር በሚቀርብ አገልግሎት መገኘት አይወዱም። ማን ሊያያቸው። ቀድማችሁ ገብታችሁ አገልግሉ እንዳይባሉ አገልግሎቱን ማጥላላት ምርጫቸው ሆነ።
3፣ እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት አይመቻቸውም። ለምሳሌ «ተፈሥሒ ማርያም ለአዳም ፋሲካሁ ወማዕዶታ ለሔዋን እንተ ይእቲ ዓፅመ ገቦሁ» የሚለውን ሲጠቅሱ «እስመ ግእዛኖሙ ኮነ ለወልድኪ በትንሣኤሁ = በልጅሽ ትንሣኤ ነፃነታቸው ተደርጓልና» የሚለውን መጥቀስ አይፈልጉም። በትርጓሜያችን መጽሐፍ ጭብጡን አይለቅም ለሸፋጭ ለለዋጭ አይመችም የሚል ሐተታ አለ። ለሸፍጣቸው ስለማይመቻቸው ለማጥፋት የቻሉትን ያህል ይደክማሉ።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ፋሲካ» የተባለው በለበሰው ሥጋ ነው። ይህም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ «ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢአተ ዓለም = የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ» በማለት የተናገረውን የሚተረጉም ነው። ቅዱሳት መጻሕፍት እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስን «በግ» እያሉ ሲገልጹት እሱ ራሱ በርሱ ያመኑ ምእመናን «በጎች» በማለት ይጠራቸዋል። ይህ ማለት የምእመናን «አባግዕ» መባልና መሆን የክርስቶስን ስፍራ ይይዛል ወይም ይተካል ማለት አይደለም። ለዚህ ነው ሊቁ «ለአዳም ፋሲካሁ» ካለ በኋላ «እስመ ግእዛኖሙ ኮነ ለወልድኪ በትንሣኤሁ = በልጅሽ ትንሣኤ ነፃነታቸው ተደርጓልና» በማለት ማስረጃ ያስቀመጠው።
ቅዱስ ኤፍሬምም በቀዳሚት ውዳሴው «ትትፌሣሕ ገነት እመ በግዕ ነባቢ ወልደ አብ ዘይነብር ለዓለም = ለዘለዓለም ጸንቶ የሚኖር የአብ ልጅ የተናጋሪው በግ እናት ገነት/እመቤታችን ደስ ትሰኛለች» ብሏል። እናቱ ስትደሰት የማይደሰት ልጅ የለምና። «ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ» ብሎ የገባለትን ቃል የፈጸመለት ከእመቤታችን ሰው በመሆን ነውና። እባብ የሞቱ ምክንያት እንደሆነ ሁሉ እመቤታችንም የድኅነቱና የፋሲካው ምክንያት ናትና።
ሊቃውንት በየድርሳናቸው «ትምክሕተ ኵልነ፣ አንቲ በአማን ምክሐ ዘመድነ፣ ትክምሕተ ዘመድነ በወሊዶተ ዚአከ = የሁላችን መመኪያ፣ አንቲ የባሕርያቺን መመኪያ ነሽ፣ አንተን በመውለዷ የባሕርያችን መመኪያ ናት» እያሉ የገለጿት የአዳም ፋሲካ/ደስታ በመሆኗ ነው። እግዚአብሔር ከሰማይ ወደምድር በተመለከተ ጊዜ እሱን የሚፈልግ ጠቢብ ሰው አለማግኘቱን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ። መዝ 13፥2፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ለአዳም የገባው ቃል ኪዳን የሚፈጸምበት ዘመን ሲደርስ መልአኩን ልኮታል። «ወበሳድስ ወርኅ ተፈነወ ገብርኤል መልአክ እምኀበ እግዚአብሔር = በስድስተኛው ወር መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ» እንዳለ ወንጌለ ሉቃስ። ሲያበሥራትም «ተፈሥሒ ፍሥሕት ኦ ምልዕተ ጸጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ = ደስ የተሰኘሽ ጸጋን የተመላሽ ሆይ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ» በማለት ነው። ስለዚህም ድንግል ማርያም የአዳም ፋሲካ/ደስታ ናት።
ቅዱስ መጽሐፍ ሔዋንን «የሕያዋን ሁሉ እናት» (ዘፍ 3፥20)ብሎ ሲጠራት እመ ሕይወት ድንግል ማርያምን ፋሲካ ብንላት አላዋቂነት ነውን?
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን