ጳውሎስ ኞኞ (1926-1984)
አዘጋጅ፡- ደረጀ ትእዛዙ
ኅትመት፡- 2006 ዓም
የገጽ ብዛት፡- 308
ዋጋ፡- 84 ብር
ስለ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የታሪክ ሰው ጳውሎስ ኞኞ ታሪክ፣ ሥራዎችና ሀገራዊ አስተዋጽዖ የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ ደረጀ የጳውሎስ ጎረቤት ነበረ፡፡ ያደገውም እነ ጳውሎስ ሠፈር ነው፡፡ የልጅነቱ ትዝታ ስለ ጳውሎስ እንዲያጠና እንዳደረገው ይነግረናል፡፡ የጳውሎስን ሥራዎችና ስለ እርሱ የተጻፉ መዛግብትን አገላብጦ፤ ዛሬም በሕይወት ለታሪክ ቆይተው ያገኛቸውን የቅርብ ሰዎቹን አናግሮ ዙሪያ መለስ የሆነ ሥራ አቅርቦልናል፡፡
የጳውሎስን ጉዞ ከትውልድ መንደሩ እስከ ተጓዘባቸው የዓለም ክፍሎች፣ ከትውልድ ሥፍራው ቁልቢ እስከ መቀበሪያው ቀራንዮ
የጳውሎስን ጉዞ ከትውልድ መንደሩ እስከ ተጓዘባቸው የዓለም ክፍሎች፣ ከትውልድ ሥፍራው ቁልቢ እስከ መቀበሪያው ቀራንዮ
መድኃኔዓለም ደረጀ ስለ ጳውሎስ የሚመሰገንበትን ብቻ ሳይሆን የሚወቀስበትን፣ የሚደነቅበትን ብቻ ሳይሆን የሚነቀፍበትን፣ ብርታቱን ብቻ ሳይሆን ድክመቱንም እንድናየው አድርጎናል፡፡ ከጠባዩ እስከ ችሎታው፣ ከእምነቱ እስከ ፍልስፍናው፣ ከኩርፊያው እስከ ደግነቱ ያሳየናል፡፡
በጳውሎስ ኞኞ ታሪክ በኩል የኢትዮጵያን ፕሬስ ጉዞ፣ የነበሩትን ዋና ዋና ተዋናዮች፣ የነበረባቸውን ፈተና፣ አስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊና ፍልስፍናዊ ተግዳሮት፣ በየዘመናቱ የተነሡ ጋዜጠኞች ለፕሬስ ነጻነት እንዴት ይጋደሉ እንደነበር፣ ከንጉሥ እስከ ሰካራም፣ ከአንባቢ እስከ አለቃ ይደርስባቸው የነበረውን መከራ ያሳየናል፡፡
ጳውሎስ ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን ራሱን በራሱ ያስተማረ፣ ታሪካችንን ፈልፍሎ በራሳችን ቋንቋ ሊያቀርብልን የሞከረ፣ በሀገሪቱ በተከሰቱ ልዩ ልዩ ችግሮች ወቅት ወገቡን ታጥቆ ለወገኑ የለፋ፣ ከመንደሩ ማኅበራዊ ግንኙነት እስከ ብሔራዊ ችግሮች ድረስ፣ ከድርቅ እስከ ሶማሌ ጦርነት ድረስ ለሀገሩ የደከመ ክቡር ዜጋ መሆኑን መጽሐፉ ያሳየናል፡፡
ጳውሎስ የተማረው እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ብቻ ነው፡፡ ራሱን በራሱ አስተምሮ ግን ከሊቃውንቱ በላይ ለመሥራት ችሏል፡፡ መማርን ለደመወዝና ለግድግዳ የምረቃ ፎቶ ብቻ ለሚያደርጉ ሰዎች ጳውሎስ ታላቅ ማስተማሪያ ነው፡፡ የውጤት መንገዱ ፍላጎት፣ ጥረትና ያለ መታከት መሆኑን ጳውሎስ ያሳየናል፡፡ ዛሬ ብዙ ዕድሎች ተመቻችተውልን ጊዜውን በቀልድ ለምናሳልፍ ሰዎች ጳውሎስ መውቀሻ ነው፡፡
ወጣቶች የከተፋና የቶሎ ቶሎ ሥራዎች ላይ ተጠምደዋል እየተባለ በሚተችበት በዘህ ጊዜ ደረጀ ትችቱን ሐሰት አድርጎ ጊዜ የሚወስድ፣ ሰነድ ማገላበጥን የሚጠይቅ፣ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ አያሌ ደጅ መጥናቶችን የግድ የሚል ሥራ ይዞ መምጣቱ ያስመሰግነዋል፡፡
ጳውሎስ ኞኞን የምታውቁት ትዝታችሁን ይጭርላችኋል፡፡ የማታውቁት ታሪኩን አብራችሁ የነበራችሁ ያህል ያሳያችኋል፡፡ በዚያውም የአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ታሪክ የሀገሪቱ ታሪክ መሆኑን በሚገባ ያሳያችኋል፡፡ ጥላሁን ገሠሠ ‹‹ምናለ አንዳንዱ ሰው ዳግመኛ ቢፈጠር›› ያለው ሊሠራባቸው ከሚገቡት አንዱ ጳውሎስ ኞኞ መሆኑን መጽሐፉን ስታነቡ ታረጋግጣላችሁ፡፡
መልካም ንባብ፡፡
Read more http://www.danielkibret.com/2014/07/1926-1984.html