ዴር ሡልጣን፡- ዐሥር ነገሮች(ክፍል ሦስት)

ዴር ሡልጣን፡- ዐሥር ነገሮች(ክፍል ሦስት)
ከመቶ ዓመታት በፊት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ አባቶች

click here for pdf
ከዚህ በፊት ለኢየሩሳሌም ገዳማችን ሊደረጉ የሚገቡ ዐሥር ነገሮችን አቀርባለሁ ባልኩት መሠረት ሦስቱን አቅርቤያለሁ፡፤ አራተኛውን እነሆ
4. ጠንካራ የምልመላ መሥፈርት ይኑር
አባቶቻችን ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ ሲያደርጉ ሁለት ሺ ዓመት አልፏቸዋል፡፡ በየዘመናቱ ከአውሮፓና ከእስያ የመጡ ተጓዦችና ታሪክ ጸሐፊዎች የኢትዮጵያውያን መነኮሳትን የፈቃድ ድህነት፣ የጸሎት ትጋት፣ ተአምር አድራጊነት፣ ሊቅነት፣ መንፈሳዊነትና ፍጹማዊ ምናኔ በአድናቆት ጽፈውታል፡፡ እነዚያ መነኮሳት ወደ ቅድስት ሀገር የመጡት ለአራት ዓላማዎች ነበር፡፡
  1. ከቅዱሳን ቦታዎች በረከት ለማግኘት፣
  2.  ፍጹም የሆነ ምናኔን ለመኖር፣
  3. ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ዕውቀትን ለመገብየትና
  4. የኢትዮጵያውያንን ቅዱሳት መካናት ለመጠበቅ፡፡
ያኔ የዐረብ ሀገሮችን፣ የሱዳንንና የሳዑዲን በረሃዎች፣ የዐረቦችንና የቱርኮችን አገዛዝ፣ ውኃ ጥሙንና መከራውን አልፎ ለመምጣት መንፈሳዊ ጽናትና የጸና እምነት ያስፈልግ ስለነበር ለክፉ የሚሰጥ ሰው ይህንን ሁሉ ችሎ ወደ ኢትዮጵያውያን ገዳማት አይመጣም ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በመነኮሳቱ መካከል መለያየትና መከፋፈል እንደነበረ እቴጌ ጣይቱ መነኮሳቱን ‹‹እባካችሁ አትጣሉ፣ አንድ ሁኑ›› እያሉ የጻፉት ደብዳቤ ይነግረናል፡፡ ለገዳሙ በጎ የሠሩ አንዳንድ አባቶችም ዕጣ ፈንታቸው መሰደድ፣ መገፋትና መባረር እንደነበረ የነ አባ ወልደ ሰማዕት ታሪክ ይነግረናል( በነገራችን ላይ የአባ ወልደ ሰማዕትን አስደናቂ ታሪክና በገዳሙ መነኮሳት የደረሰባቸውን ግፍ በቀጣይ ሳምንት እመለስበታለሁ፡፡ በዘመናቸው የዓይን ምስክሮች የነበሩ ሁለት ሰዎች የጻፉትን፣ ሁለት ሌሎች ሰዎች ደግሞ ከእርሳቸው ሰምተው ለትውልድ ያስቀመጡትን ታሪክ አግኝቻለሁ)

ዛሬ መነኮሳትን ለኢየሩሳሌም ገዳማት የሚመድበው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ነው፡፡ ስለዚህም በመንገድ የሚደርስ ፈተና፣ በኑሮ የሚደርስ ችግር፣ ረሃብና እርዛት የለም፡፡ መከራ የሚያጠራው ሰውም የለም፡፡ ለዚህም ነው ወደ ኢየሩሳሌም ገዳማት ለሚመደቡ አባቶችና እናቶች ጠንካራ የምልመላ መሥፈርት ያስፈልጋል የምንለው፡፡ መንፈሳዊነታቸው፣ ለጸሎት ያላቸው ትጋት፣ ዐቅመ ደካሞችን ለመርዳት ያላቸው ፍላጎትና ብርታት፣ ለመማርና ዕውቀት ለመሸመት ያላቸው ጉጉትና ዐቅም፣ በዓላማቸው ለመጽናትና የመጡበትን ግዳጅ ለመፈጸም ያላቸው ዝግጁነት መታየት አለበት፡፡
ከዘረኛነት የነጹ፣ ነጋ ለኪዳን መሸ ለቁርባን የሚሉ፣ ቅዳሴና ሰዓታት የማይሰለቻቸው፣ በሕይወት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ፣ ንጽሕናቸውንና ቅድስናቸውን ጠብቀው በመኖር ነገ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለምትፈልጋቸው መዓርግ ዝግጁ የሆኑ፣ አፍቅሮ ነዋይ የራቀላቸው፣ ቤት ልሥራ ዘር ልዝራ የማይሉ እንዲሆኑ ጠንካራ የመመልመያ መሥፈርት ያስፈልጋል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የኢየሩሳሌም መነኮሳት የሠሯቸው ሥራዎች የሚያስደንቁ፣ የሚያኮሩና እንኳን እኛ ልጆቻቸውን ሌሎችንም ያስገረሙ ነበሩ፡፡ ዛሬ አንዳንድ መነኮሳት ‹‹እኛ ለጸሎት እንጂ ዕውቀት ለመሸመት ወይም ተግባረ ዕድ ለመሥራት ኢየሩሳሌም አልመጣንም›› ቢሉም በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ግን ዕውቀትና ገዳማዊ ሕይወት ተለያይተው አያውቁም፡፡ ሌላው ቀርቶ በ13ኛው መክዘ ምርጦቹ ስምንት መቶ መነኮሳት በመንፈሳዊ ሕይወት በስለው፣ በምንኩስና ተክነው፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት ተራቅቀው የወጡት ከሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም መሆኑን መርሳት አይገባም፡፡ መካከለኛዋን፣ ምዕራብና ምሥራቅን ብሎም ደቡብ ኢትዮጵያን ተካፍለው ያስተማሩት አሥራ ሁለቱ ንቡራነ ዕድ ተምረውና ተቀርጸው የወጡት ከደብረ ሊባኖስ ነበር፡፡ በኤርትራና በትግራይ ያስተማሩት አምስቱ ከዋክብትና ሰባቱ ከዋክብት የሚባሉት ሐዋርያውያን የተገኙት ከደብረ በንኮል ነበር፡፡

ታላላቅ የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳት መጻሕፍት ከግሪክ፣ ከዐረብኛ፣ ከዕብራይስጥና ከላቲን ወደ ግእዝ የተተረጎሙት በዴር ሡልጣን መነኮሳት ትጋት መሆኑ ተረስቶ ቋንቋ አለማወቅ ዛሬ አንዳንዶቹን ያኮራቸዋል፡፡ በቅዱሳት መጻፍት የአንድምታ ትርጓሜ ላይ የኢየሩሳሌም ገዳማት መነኮሳትን አስተዋጽዖ ለማወቅ የእሥራኤልን ቦታዎች ከጎንደር ቦታዎች አነጻጽረው የተረጎሙበትን ዘይቤ ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ የነበሩት አባቶች ጸሎት ብቻ አልነበረም ተግባራቸው፡፡ ዙሪያ መለስ ነበሩ፡፡ በዐፄ ናዖድ ዘመነ መንግሥት(1487-1500 ዓም) ወደ ኢየሩሳሌም ከመጡት የደብረ ብሥራት ዜና ማርቆስ አሥራ ሁለት አባቶች አንዱ የሆነው አባ በኃይለ ማርያም፣ በተዋሕዶ እምነቱ ምክንያት ለደረሰበት ተዋርዶ ከካቶሊካዊው  ሰው ጋር በኢየሩሳሌም አደባባይ ለመከራከር ሲጠይቅ ዳኛው ‹‹በምን ቋንቋ ትከራከረዋለህ?›› ብሎ ሲጠይቀው ‹‹በዐረብኛ ወይም በዕብራይስጥ›› ሲል መለሰለት፡፡ ዳኛውም ‹‹እንዴት እነዚህን ቋንቋዎች ልታውቅ ቻልክ›› ብሎ በአድናቆት ሲጠይቀው ‹‹ወአነ አአምር በልሳነ ዓረብ ወዕብራይስጥ ፍካሬሆን ለመጻሕፍተ ሕግ ወነቢያት እስመ ተምህርኩ እም ኀበ መምህር ዐቢይ ኢሳይያስ በትእዛዘ ንጉሥ ናዖድ ፈራሄ እግዚአብሔር ዘምስለ ዕንባቆም እኅወ መምህር ዐቢይ ዘስሙ እንድርያስ - እኔም የሕግና የነቢያት መጻሕፍትን ትርጓሜያቸውን በዐረብና በዕብራይስጥ ቋንቋ ዐውቃለሁ፡፡ እግዚአብሔርን በሚፈራ ንጉሥ በናዖድ ትእዛዝ ከታላቁ መምህር ከኢሳይያስ ዘንድ የእንድርያስ ወንድሙ ከሚሆን ከዕንባቆም ጋር ተምሬያለሁና፡፡›› አለው ይላል ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከመካከለኛው ዘመን በኋላ የዕብራይስጥና የዐረብኛ ቋንቋ በሦስት ቦታዎች ይሰጡ ነበር፡፡ ደብረ ሊባኖስ(ሸዋ)፣ ደብረ ማርያም(ጎንደር) እና ማኅበረ ሥላሴ(ጎንደር)፡፡ ብዙዎቹ መነኮሳት በእነዚህ ቦታዎች ገብተው ቋንቋውን አጥንተው ነበር ወደ ኢየሩሳሌም የሚመጡት፡፡ የደብረ ማርያሙን የዕብራይስጥ መጽሐፍ እኔም አይቼዋለሁ፡፡

ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እንደ ጻፉትና ዛሬም በቫቲካን ቤተ መዛግብት እንደምናገኘው ታሪክ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን የዴር ሡልጣን መነኮሳት በፍሎሬንስ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ተካፍለው ነበር፡፡ ጉባኤው የተካሄደው በላቲን ቋንቋ ነበር፡፡ ኢትጵያውያን መነኮሳትም ጉባኤውን የተሳተፉት በላቲን ቋንቋ ነበረ፡፡ በነገራችን ላይ አርመኖች የራሳቸውን ፊደል እንዲፈጥሩ የረዷቸው በዴር ሡልጣን የነበሩ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ናቸው፡፡ የአርመንን ፊደል የፈጠረው መነኩሴ የኖረው በዴር ሡልጣን ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ወደ አርመንኛ ሲተረጉምም የረዱት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት የግእዝ ፊደልን የሚመስሉ ፊደሎችና የግእዝ ቃላት በአርመንኛ ቋንቋ ውስጥ በብዛት ይገኛል፡፡

‹‹ቄሱ ዮሐንስ - ፐሪስተር ጆን›› በሚል ስያሜ ኢትዮጵያን ሲፈልጉ የኖሩት የ14ኛው፣ 15ኛውና 16ኛው የአውሮፓ አሳሾች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ መረጃ ያገኙት ከኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት መነኮሳት ነበር፡፡

ይህንን ሁሉ የማነሣው ቀደምት አባቶቻችን እንዴው ሲጸልዩና ርስት ሲጠብቁ ብቻ እንደኖሩ አድርጎ የመመልከት ደካማ አስተሳሰብ በኢየሩሳሌማውያን ላይ ስለሚታይ ነው፡፡ አባቶቻችንና አባቶቻችሁ እንዲያ ብቻ አልነበሩም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከራሳቸው አልፈው የሌሎች መመኪያ ለመሆን የበቁና በሌሎች ሀገሮች ገዳማትን የመሠረቱ አባቶችም ነበሩ፡፡ ሶርያውያን ‹‹ሞሰስ - አል - ሐበሽ - ኢትዮጵያዊው ሙሴ›› ብለው የሚጠሩት በ6ኛው መክዘ የነበረው የዴር ሡልጣን መነኮስ በሶርያ ከታወቁት የገዳማት መሥራቾች አንዱ ነው፡፡ ታሪኩ የንጉሥ ልጅ እንደነበር ይገልጣል፡፡ የአርመን ቤተ ክርስቲያን የምታከብራቸው አቡነ ኤዎስጣቴዎስም በዴር ሡልጣን ኖረው ነው ወደ አርመን የተጓዙትና በዚያ ያረፉት፡፡

የኢየሩሳሌም መነኮሳት ለሀገራቸው ያበረከቱት መጻሕፍትን ብቻ አልነበረም፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችም ወደ ኢትዮጵያ ይገቡ ከነበሩበት መንገድ አንዱ ከኢየሩሳሌም በሚመጡ መነኮሳት አማካኝነት ነበር፡፡ እነ አቡነ ዕዝራ በ16ኛው መክዘ ኢየሩሳሌም ኖረው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የውኃ ወፍጮ ይዘው በመምጣት ነበር ለገዳማቱ ያስተዋወቁት፡፡የግራኝ ጦርነት ተከታትሎ ተነሥቶ ተክኖሎጂው ባይስፋፋም አባታችን ግን ጥረት አድርገው ነበር፡፡

የእነዚህን አባቶች ብቃት፣ ዕውቀትና ትጋት ስናይ ዛሬ ያለንበትን ደረጃ መመዘን እንችላለን፡፡ ለዚህም ነው በኢየሩሳሌም ገዳማት የሚመደቡ አባቶች የቀደሙትን ደረጃ የሚያስጠብቁ፣ የቤተ ክርስቲያንን መልካም ገጽታ የሚገነቡ፣ የኢትዮጵያን በረከት ለዓለም፣ በሌሎች የሚገኘውን ልምድ ደግሞ ለኢትዮጵያ የሚያስተላልፉ እንዲሆኑ በሚገባ ተመርጠውና ተመዝነው መመደብ አለባቸው የምንለው፡፡ በኢየሩሳሌም የምንወዳደረው ከግብጾች፣ ከአርመኖች፣ ከግሪኮች፣ ከላቲኖች፣ ከሶርያኖች ጋር ነው፡፡ ለመሆኑ ትናንት ከግሪክ ቀጥላ በፕሮቶኮል ደረጃ 2ኛ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ ስንተኛ ናት? የእሥራኤልን የፕሮቶኮል ዶክመንት ያየ ያውቀዋል፡፡  

እንዴት ነው አሁን ለቅዳሴና ለሰዓታት ያለው ፍላጎት? እንዴት ነው ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመማር ያለው ትጋት?  እንዴት ነው የእጅ ሥራ ሠርቶ ገዳሙን ለመርዳት ያለው ሩጫ? (የገዳማውያን አንዱ ተግባር ተግባረ ዕድ አይደለም እንዴ? ለታላቁ እንጦንስ ቅዱስ ሚካኤል ሰኔል መታታት ለምን አስተማረው) እንዴት ነው በኢትዮጵያ የሚገኙ ገዳማትን ለመርዳት ያለው ትጋት? ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ያለው ጽናት?መንኖ ጥሪት ሆኖ ለመኖር ያለው ተጋድሎ? እውነት ሙሉ በሙሉ በቁሪት ነው ገዳሙ የሚተዳደረው?ለወር ጉርስ ለዓመት ልብስ በዶላር የሚከፈላቸው ባለ ቁሪቶች በኢትዮጵያ ገዳማት አሉ?እነ መምህር ወልደ ሰማዕት በኢየሩሳሌም ከተማ ለገዳማቱ ነበር ቤት የሠሩት፣ ዛሬስ የት ነው ቤቱ እየተሠራ ያለው?የዚህ ሁሉ አንዱ ችግር ከመምረጫ መመዘኛው ነውና እንደገና ቢታይ፡፡

ለመሆኑ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ጋብቻ የሚከናወነው በተክሊል ነው? ለመሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ከቅዳሴ በኋላ ጋብቻ በቢሮ ውስጥ እንዲደረግ ይፈቅዳል? ቤተ ክርስቲያንስ የኦርቶዶክስ አማኝ ያልሆኑትን ለማጋባት ሥርዓቷ ይፈቅድላታል?የእሥራኤልስ ሕግ ይፈቅዳል? ቤተ ክርስቲያን የማዘጋጃ ቤትን ሥራ መሥራት ትችላለች?ይኼ ሁሉ ለምን መጣ? ለእምነት ሳይሆን፣ ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን ለሌሎች ነገሮች ትኩረት ከመስጠት፡፡ ‹‹ሕግ ይወጽዕ እም ጽዮን›› ነበር፡፡ አሁን ግን በጽዮን ሕግ እየጠፋ ነው፡፡ ለዚህ ነው ወደ ኢየሩሳሌም የሚመጡ አባቶችን የመላኪያ መሥፈርቱ ይጥበቅ፣ ቅድሚያ ለሃይማኖት፣ ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ለጽድቅ የሚሰጡ አባቶችና እናቶች ይምጡ የምንለው፡፡

(ይቀጥላል)

ኢየሩሳሌም




Read more http://www.danielkibret.com/2014/04/blog-post_26.html