የቅ/ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በማስተርስ መርሐ ግብር የመጀመሪያዎቹን ደቀ መዛሙርት አስመረቀ
- Details
- Created on Wednesday, 09 July 2014 14:19
- Written by Hara Tewahido
- በ፲፱፻፹፯ ዓ.ም. ዳግመኛ ከተከፈተ ወዲህ የተመረቁት ደቀ መዛሙርት ብዛት 2175 ደርሷል
- የተቋማዊ ነፃነት ዕጦትና የበጀት እጥረት ‹‹ጥናትና ምርምር ላይ እንዳላተኩር አድርጎኛል፡፡››
- መሠረቱ የወጣው ሕንፃ ሥራ እንዲቆም በጀቱም እንዲመለስ የተላለፈው ትእዛዝ አወዛግቧል
- ወደ ዩኒቪርስቲ ደረጃ የማሸጋገሩ ሒደት በግንባታ ላይ የሚገኘውን ሕንፃ መጠናቀቅ ይጠብቃል
- ‹‹ከዛሬው ደስታችኹ የሚበልጥ ደስታ ከፊታችኹ ስለተዘጋጀ ደስታችኹ ዕጥፍ ድርብ ነው፡፡›› /ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ/
***
- መስተጋድላን አኃውና አኃት ደቀ መዛሙርት በእጅግ ከፍተኛና ከፍተኛ ማዕርጎች ተመርቀዋል
- የሴት ደቀ መዛሙርት ብዛት እና ውጤታማነት ‹‹አገልግሎቱን የተሟላ ያደርገዋል›› ተብሏል
- ምሩቃኑ ነገ በጠቅ/ቤ/ክህነቱ የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ የአገልግሎት ምደባ ዕጣ ያወጣሉ
- በየገጠሩ ሊቃውንቱ እየተገፉ ያልተማሩት በንዋይ ብዛት የሚንደላቀቁበት ኹኔታ በቅኔዎች ተተችቷል
- ‹‹ግእዝ የኛ ብቻ ስላልኾነ በተቋማት ኹሉ ይሰጥ፤ ዲፕሎማውም ወደ ዲግሪ ይደግ፡፡››/ምሩቃን/
***
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴዎሎጂ የማስተርስ ዲግሪ (Masters Degree in Systematic Theology) መርሐ ግብርያሠለጠናቸውን 25 ደቀ መዛሙርት፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ ሰኔ ፳፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሔደው ሥነ ሥርዓት አስመረቀ፡፡
ኮሌጁ በ፳፻፭ ዓ.ም. የጀመረው የኹለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ቀዳሚ ዕጩ ደቀ መዛሙርትን ለምረቃ ማብቃቱ፣ የዘንድሮውን የምረቃ በዓል የተለየ እንደሚያደርገው አካዳሚክ ምክትል ዲኑ መ/ር ግርማ ባቱ ተናግረዋል፡፡
ምረቃው ‹‹የመጀመሪያና ታሪካዊ አጋጣሚ›› ከመኾኑ ባሻገር በተለያዩ መርሐ ግብሮች የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ደቀ መዛሙርትን ቀጣይ የትምህርት ዕድገት ለማረጋገጥ ኮሌጁ በማድረግ ላይ የሚገኘው ዝግጅት አካልም እንደኾነ አካዳሚክ ምክትል ዲኑ አስታውቀዋል፡፡
ከነባራዊ ኹኔታዎች ግምገማና ከሚጠበቅበት አንጻር፣ ኮሌጁን ብዙኃን ተስፋ ወደሚያደርጉት ቀጣይ ደረጃ ለማድረስ ስለሚካሔደው ዝግጅት በንግግራቸው የዘረዘሩት አካዳሚ ምክትል ዲኑ፣ ለአንድ ግዙፍ የትምህርት ተቋም የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ግብአቶችን ያሟላ ሕንፃ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
በግንባታ ላይ የሚገኘው ሕንፃ÷ የመማሪያና የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች፣ ቤተ መጻሕፍትና የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንደሚያካትትና የተቋሙ ቀጣይ ዕቅዶችም ከሕንፃው መጠናቀቅ ጋራ የተያያዘ እንደኾነ አካዳሚክ ምክትል ዲኑ አመልክተዋል፡፡ ግንባታው የሚከናወነው በአስቸጋሪ የበጀት እጥረት ውስጥ መኾኑን የጠቆሙት መ/ር ግርማ፣ ለፍጻሜውም የበጎ አድራጊ አካላትን እገዛ ጠይቀዋል፡፡
ተቋማዊ ነፃነት በዲኑ ንግግር የተጠቆመ ሌላው ችግር ነው፡፡ ነፃነቱ ከምን አኳያ እንደኾነ የተብራራ ነገር ባይኖርም፣ ኮሌጁ ‹‹በሙሉ አቅሙ ጥናትና ምርምር ላይ እንዳያተኩር አድርጎታል፤›› ብለዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ከአገሪቱ አንጋፋ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ የኾነው ኮሌጁ በቴዎሎጂ የማስተርስ ዲግሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማስመረቅ መብቃቱ ‹‹ትልቅ ስኬት ነው፤›› ያሉት የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ የዲኑን ጥቆማ በማጠናከር ባስተላለፉት መልእክት÷ የተቋማዊ ነፃነት ጥያቄው፣ የኮሌጁን ኹለ ገብ ሕንፃ በማስተዳደር የኪራይ ገቢውን ለራስ አገዝ ልማታዊ ፕሮግራሞች መጠቀምን በሚመለከት በኮሌጁ አስተዳደርና በጠቅ/ቤተ ክህነት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት የሚጠቅስ እንደኾነ በንግግራቸው አጠይቀዋል፡፡
ከኮሌጁ ቀጣይ ፕሮግራሞች መካከል በዋናነት የተቀመጠው፣ ‹‹ኮሌጁን ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገው ጥረት ነው፤›› ያሉት ብፁዕነታቸው፣ ለዚኽም እንዲረዳ የረጅምና የአጭር ጊዜ ዕቅዶች ተነድፈው መተግበራቸውንና በመተግበር ላይ እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ብፁዕነታቸው ገለጻ፣ የኮሌጁ ኹለ ገብ ሕንፃ ግንባታ ከረጅም ጊዜ ዕቅዶቹ አንዱ ነው፡፡ ከሕንፃው የኪራይ አገልግሎት ከሚሰበሰበው ገቢም የራስ አገዝ ልማታዊ ፕሮግራሞችን በመንደፍ ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ለሚደረገው ሽግግር አቅም እየተፈጠረ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
ኮሌጁ አኹን በማስገንባት ላይ የሚገኘው ‹‹የትምህርት መስጫና ማገዣ ክፍሎች››ን ያሟላ ዘመናዊ ሕንፃም አንጋፋው ተቋም÷ ‹‹ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ መሸጋገሩ እውን ሊኾን መቃረቡን የሚያሳውቅ ነው፤›› በማለት ያመለከቱት ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ‹‹የነበሩ ሒደቶች ብዙ ያስተማሩንና ጽናትን ገንዘብ እንድናደርግ ያስቻሉን በመኾናቸው ዕቅዶቻችን በልዑል እግዚአብሔር አጋዥነት ለወደፊትም እንደሚሳኩ እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡
የበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ ‹‹ለዛሬው ስኬታችኹ ከነቤተሰቦቻችኹ እንኳን ደስ አላችኹ›› በማለት ለዓመቱ ተመራቂዎች ያስተላለፉትን መልእክታቸውን ያጠቃለሉት፣ የመሸጋገርያ ቅድመ ዝግጅቱ ለኮሌጁ ምሩቃን ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ‹‹ዕጥፍ ድርብ ደስታ›› መኾኑን በማስታወቅ ነው – ‹‹ከዛሬው ደስታችኹ የሚበልጥ ደስታ ከፊታችኹ ስለተዘጋጀ ደስታችኹ ዕጥፍ ድርብ ነው፡፡ የሚበልጠውን ለማየት እግዚአብሔር ያብቃችኹ፡፡››
የቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብዛት በሦስት ብቻ መገደብ እንደሌለባቸው አክለው ያመለከቱት ብፁዕነታቸው፣ የተቋማቱን ቁጥር ከመጨመር ጋራ ውስጣዊ አቅማቸውን በማሳደግ ለውጤታማነት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ መንፈሳዊ ኮሌጁ ዛሬ ለሚገኝበት ደረጃ ከፍተኛ የአመራር ሰጭነት ሚናውን ተወጥቷል ያሉትን የሥራ አመራር ቦርድ አባላት አመስግነዋል፤ በኮሌጁ የምረቃ ታሪክም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተባለ የምስጋና ምስክር ወረቀት ለመምህራኑ ተበርክቶላቸዋል፡፡
በአካዳሚክ ምክትል ዲኑና በበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ ንግግር የተጠቀሰው፣ ከ50 ሚልዮን ብር ያላነሰ ጠቅላላ በጀት እንደተመደበለት የተነገረው የዐዲስ ሕንፃ ግንባታ፣ በአኹኑ ወቅት በኮሌጁ ቅፅር መሠረቱ ወጥቶ ይታያል፡፡ የሕንፃ ሥራው የተጀመረው፣ ኮሌጁ ኹለገብ ሕንፃውን ካስገነባበት ከ፳፻፩ ዓ.ም. አንሥቶ በኪራይ አገልግሎት የሰበሰበውንና በዝግ ሒሳብ ሲከማች የቆየውን 21 ሚልዮን ያኽል ብር ፓትርያርኩ ለባንክ በጻፉት ትእዛዝና በፓትርያርኩ፣ በበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስና በዋና ዲኑ ፊርማ ወጪ በማድረግ እንደኾነ ታውቋል፡፡
ገንዘቡ ወጭ የኾነበትና ሥራ ላይ እንዲውል የተወሰነበት አካሔድ፣ ‹‹የጠቅ/ቤተ ክህነቱን የፋይናንስ አሠራር ይጥሳል፤ ቅ/ሲኖዶስ ስለ መንፈሳውያን ኮሌጆች በጀትና ስለ ሕንፃው አስተዳደር ካስተላለፈው ውሳኔ ጋራም ይፃረራል፤›› በሚል ቋሚ ሲኖዶሱ አግዶታል፡፡ ይህን ተከትሎም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት÷ ‹‹የዐዲሱ ሕንፃ ግንባታ እንዲቆም፣ ወጪ የተደረገውም ገንዘብ እንዲመለስ›› ኮሌጁን ማዘዙ የተቋማዊ ነፃነት ጥያቄው መንሥኤ እንደኾነ ነው የተነገረው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት ፳፻፮ ዓ.ም. ውሳኔው፣ የቅድስት ሥላሴን ጨምሮ የሦስቱም መንፈሳውያን ኮሌጆች በጀታቸው ተጠቃሎ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ገቢ እየኾነ በጀታቸውንም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እየበጀተ እንዲከፈል መወሰኑና፤ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ‹‹አቅም የሚፈጥርልኝና ራሴን የሚያስችል ገቢ አገኝበታለኹ›› ያለው ኹለገብ ሕንፃም በቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ሥር ኾኖ የኪራይ ገቢው በሕጋዊ መንገድ እንዲሰበሰብ አዝዞ እንደነበርም መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል መንፈሳዊ ኮሌጁ፣ በመደበኛ ማስተርስ ዲግሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ካስመረቃቸው 25 ደቀ መዛሙርት በተጨማሪ፡-
- በቀን መደበኛ የዲግሪ መርሐ ግብር – 25
- በማታው ተከታታይ የዲግሪ መርሐ ግብር – 53
- በማታው ተከታታይ የዲፕሎማ መርሐ ግብር – 116
- በማታው ተከታታይ የግእዝ ዲፕሎማ – 7
- በርቀት ትምህርት መርሐ ግብር በሰርቲፊኬት – 83
በጠቅላላው 309 ደቀ መዛሙርትን ለምረቃ አብቅቷል፡፡
በነገረ መለኰት የማስተርስ ዲግሪ ምሩቃን በመርሐ ግብሩ አስተባባሪ ቀሲስ ዶ/ር ጆሲ ጃኮብ፣ በቀን መደበኛ የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን በአስተባባሪው በመ/ር ቸርነት አበበ፣ የማታ ተከታታይ የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን በአስተባባሪው መ/ር ብርሃኔ ገብረ ፃድቃን፣ የግእዝ ዲፕሎማ ምሩቃን በአስተባባሪው በመ/ር ዘርዓ ዳዊት አድኀና እንዲሁም በርቀት ትምህርት ፕሮግራም የሰርተፊኬት ምሩቃን በአስተባባሪው በመ/ር መዝገበ ቃል አቅራቢነት፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ እየተመረቁ ዲግሪያቸውን፣ ዲፕሎማቸውንና ሰርተፊኬታቸውን ተቀብለዋል፡፡
ከየመርሐ ግብሩ ምሩቃን መካከል፣ በየዓመቱ ዕድገት እያሳየ ነው የተባለው የሴቶች ደቀ መዛሙርት ቁጥርና ውጤታማነት በዘንድሮው ዓመትም ተጠናከሮ መቀጠሉ ተገልጧል፡፡ በሲስተማቲክ ቴዎሎጂ የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር ከተመረቁት 25 ደቀ መዛሙርት መካከል ኹለቱ አንስት(ወ/ሮ ዘውዴ ገብረ እግዚአብሔር እና ወ/ሮ ይመኙሻል ግዛው) በእጅግ ከፍተኛ ማዕርግ እና በከፍተኛ ማዕርግ ነው ለምረቃ የበቁት!! ከ53 የማታው ተከታታይ ዲግሪ ደቀ መዛሙርት ደግሞ አራቱ፣ ከ116 የዲፕሎማ ተከታታይ ደቀ መዛሙርትም አምስቱ ሴቶች እንደኾኑ ታውቋል፡፡
በግእዝ ቋንቋ በዲፕሎማ ከተመረቁት ሰባት የተከታታይ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት መካከል ሦስቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ከሦስቱ ኹለቱ የከፍተኛ ማዕርግ ተመራቂዎች ከመኾናቸውም በላይ ከተመራቂዎቹ አንዷ የኾነችው ፍረ ወይኒ ገብረ ሥላሴ በግእዝ ባሰማችው ቃለ ተዋስኦ÷ ግእዝ ቋንቋነቱ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ እንዳልኾነ፣ በሌሎችም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሰጥ፣ ኮሌጁም የዲፕሎማ መርሐ ግብሩን ወደ ዲግሪ በማሳደግ ትኩረት መስጠቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቃለች፡፡
በሴቶች ደቀ መዛሙርት ላይ በቁጥርም በውጤትም ለታየው ዕድገት በተለይ የማታው ተከታታይ መርሐ ግብር መከፈት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ በኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ተገልጧል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተመረቁ የፕሮግራሙ ፍሬዎች የኾኑ ሴቶች፣ መጻሕፍትን በማዘጋጀትና በሌሎችም ዘርፎች በመሠማራት መንፈሳዊው አገልግሎት ‹‹በኹለት ክንፍ የሚበርና የተሟላ እንዲኾን አስችለውታል፤›› ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡ የሚደረግላቸው ድጋፍ ሊበረታታ እንደሚገባውና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ በተለያዩ መርሐ ግብሮች በድምር ውጤታቸው ከሦስት ነጥብ በላይ ያመጡ ስድስት አንስት ደቀ መዛሙርትም ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡
የምረቃውን መርሐ ግብር የመሩት አካዳሚክ ምክትል ዲኑ፣ ኮሌጁ÷ ነባር፣ ጥልቅና ረቂቁን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት፣ ሥርዓትና ታሪክ ዘመኑን በዋጀ አቀራረብ ለትውልድ ለማስተላለፍ እንደተቋቋመ አስታውሰዋል፡፡ ኮሌጁ ዳግመኛ ከተከፈተበት ከ፲፱፻፹፯ ዓ.ም. ወዲህ ያስመረቃቸው ደቀ መዛሙርት ብዛት 2175 መድረሱን በየመርሐ ግብሮቹ ዘርዝረው ያስረዱት መ/ር ግርማ ባቱ÷ የኮሌጁ ምሩቃን ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት መዋቅሮች ጀምሮ እስከ ፓትርያርክነት፣ በመንግሥት አስተዳደርም ከሚኒስትርነት እስከ ጀነራልነት ደርሰው በአገር ውስጥና በውጭ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸውን በማገልገልና አገራቸውን በመጥቀም ላይ እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
በቴዎሎጂ ማስተርስ ዲግሪ የመጀመሪያ ምሩቃን መካከል፣ አካዳሚክ ምክትል ዲኑ መ/ር ግርማ ባቱ በድምር ውጤታቸው ሙሉ አራት ነጥብ በማምጣት የዓመቱን ከፍተኛ ውጤት ሲያስመዘግቡ፣ የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው መ/ር ቸርነት አበበ እና የዓለም ቤተ ክርስቲያን መምህሩ መ/ር መኰንን ወርቅነህ በእጅግ ከፍተኛ ማዕርግ፤ የሬጅስትራር ሓላፊው መ/ር አንድነት አሸናፊና የማታ ተከታታይ መርሐ ግብር ሓላፊው መ/ር ብርሃኔ ገብረ ጻድቃን ደግሞ በከፍተኛ ማዕርግ አጠናቅቀዋል፡፡
ገና በውጥኑ ለተቋሙ የሰው ኃይል አቅም ግንባታም ያገለገለው የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብሩ አስተባባሪ ቄስ ዶ/ር ጆሲ ጃኮብ በፈቃዳቸው መልቀቂያ በማቅረባቸው በመ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝ ተተክተዋል፤ በግእዝ ትምህርት ክፍል ሓላፊነትና መምህርነት ሲሠሩ የቆዩትን መ/ር ዘርዓ ዳዊት አድኃናን ደግሞ በዚኽ ሳምንት በጥንት ጽሑፎች ሥነ ድርሳን(ፊሎሎጂ) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በዶክትሬት ዲግሪ በሚመረቁት (ዕጩ ዶክተር) ሐዲስ ትኵነህ ተክተዋቸዋል፡፡ የድጓ፣ የቅኔና የአቋቋም ባለሞያው መ/ር ሐዲስ ትኵነህ፣ በነገረ መለኰት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በጥንት ሥነ ድርሳን ደግሞ የኹለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሲኾን በኮሌጁ ሥርዓተ ቅዳሴንና ዜማን በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡
ወደ ውጤታማ ምሩቃን ደቀ መዛሙርት ስንመለስ፡- በኮሌጁ የሉተርን እንክርዳድ ለመዝራት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቅጥረኞች የዘረጉትን አደረጃጀትና የውስጥ ተባባሪ ምንደኞቻቸውን ማንነትና እንቅስቃሴ፣ የኮሌጁ አስተዳደር ጉባኤ ባቋቋመው መድረክ ላይ በሃይማኖታዊ ጽናትና በታመነ ማስረጃ እያስደገፉ በማጋለጥ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ካደረጉት፣ የቀኑ መደበኛ ዲግሪ መርሐ ግብርመስተጋድላን አኃው ደቀ መዛሙርት መካከል÷ ትምህርትን ከክህነታዊ አገልግሎት ጋራ ሳያስታጉል አስማምቶ በማሔድ የሚታወቀው ዲያቆን ፀሃይ ዴዲማስ 3.97 ድምር ውጤት በማስመዝገብ በእጅግ ከፍተኛ ማዕርግ በአንደኛ ደረጃ ተሸላሚ ኾኗል፡፡
‹‹ኮሌጁ የኦርቶዶክሳውያን እንጂ የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ እየበሉ ለፕሮቴስታንት ለሚሠሩት ተላላኪዎች አይኾንም›› በሚል በምሳሌነት ለእውነት ከተጋደሉት ወንድሞች ደቀ መዛሙርት ጋራ አቋሙን ያስተባበረው መንፈሰ ብርቱው ዲያቆን ፀሃይ፣ በሞያው ቀደም ሲል ከባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ በኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ በከፍተኛ ውጤት የተመረቀ መሐንዲስ ነው፡፡ ከምዕራብ ሰቲት ሑመራ ሀ/ስብከት ተልኮ ወደ ኮሌጁ የገባው ለአምስት ዓመታት የሠራበትንና ከፍተኛ ደመወዝ የሚያገኝበትን ሥራውን ትቶ፣ በሰዓታቱ፣ በቅዳሴውና በቅኔው ሞያዎችና በአገልግሎትም ጭምር ራሱን አዘጋጅቶ ነው፡፡ ምረቃው ግና፣ እንደ ንስር መጥቆ ለመብረር የማኮብኮብ ያህል እንደኾነና ወደ ቴዎሎጂው ጠልቆ ገብቶ ዋኝቶ ለመውጣት በሩቁ እንዳለመ በሥዕለ ገጹ ግርጌ ያሰፈረው ጥቅስ ይጠቁማል – “Long walk to Theology”
ከአፋር ሀ/ስብከት ተልኮ የመጣው ዲያቆን እስክንድር ቢፍቱ የቀኑን መደበኛ ዲግሪ መርሐ ግብር በ3.85 እጅግ ከፍተኛ ማዕርግ በማጠናቀቅ ከዲያቆን ፀሃዬ ቀጥሎ በኹለተኛ ደረጃ ተሸላሚ የኾነ፣ እንደ ዲያቆን ፀሃዬ ቀደም ሲል ከባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ሞያ በከፍተኛ ውጤት የተመረቀ ሰይፍ ዘክልኤ አፉሁ ነው፡፡
በ3.72 ድምር ውጤት ሦስተኛው የከፍተኛ ማዕርግ ተሸላሚው ሎንዶነር ነው፤ ዲያቆን ሮዋን ዊልያምስ ይባላል፤ ከእንግሊዝ መጥቶ ትምህርቱን በኮሌጁ በመከታተል ላይ ሳለ ኢትዮጵያዊት ሚስት በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አግብቷል፡፡ የነገው ምድብ ዕጣ ይመለከተው እንደኾነ ባይታወቅም ኮሌጁ ለመምህርነት ከሚሻቸው ውጤታማ ምሩቃን አንዱ እንደኾነ እየተነገረ ይገኛል፡፡
በማታው የዲግሪ መርሐ ግብርመስተጋድላን አኃው ዲያቆን ደሳለኝ መድኅን እና ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ፣በዲፕሎማ ተከታታይ መርሐ ግብር የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ርዝራዦች በተጋለጡበት መድረክ በሕግ ባለሞያነቱ የአስተዳደር ጉባኤውን የደገፈው መ/ር ብርሃኑ ታዬ በእጅግ ከፍተኛ ማዕርግ በማጠናቀቅ ቀዳሚዎቹ ተሸላሚዎች ኾነዋል፡፡ ሌሎችም በርካታ መስተጋድላንና መስተጋድላት አኃውና አኃት ደቀ መዛሙርት በከፍተኛ ማዕርግና በማዕርግ ደረጃዎች ለመመረቅ በቅተዋል!!! ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ፡፡
***
ተከታዩ ግጥም፣ ከዘንድሮው የማዕርግ ተመራቂ ደቀ መዛሙርት አንዱ የኾነው መጋቤ ሥርዓት ቀሲስ ዮሴፍ ተስፋዬ ለምረቃ መጽሔት ካበረከተው የተገኘ ነው፡፡ የሕግ ዐዋቂም የኾነው መጋቤ ሥርዓት ዮሴፍ፣ በኮሌጁ የደቀ መዛሙርት መማክርት ጉባኤ ጸሐፊነት በነበረበት ሓላፊነት፣ እንደ ዲያቆን ዓምደ ጽዮን አድማሱና አባ ኃይለ ገብርኤል ካሉት መስተጋድላን አኃው ደቀ መዛሙርት ጋራ በመኾን ÷ የሉተርን እንክርዳድ ለመዝራት ከውጭ ወደ ውስጥ የሚሸረበው ሤራ እንዲጋለጥ፣ በአስተዳደሩ በፍትሐዊነት እንዲታይና በይቀጥላልም የሊቃውንት ጉባኤ እንዲያውቀው በማድረግ በአያሌው የተጋ፣ በዚኽም የድርሻውን የተወጣ ውጤታማ ደቀ መዝሙር ነው፤ ምንም እንኳ ጉዳዩ በአኹኑ ወቅት በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ታግቶ ቢገኝም፡፡
ለዓመቱ ተመራቂዎች ደቀ መዛሙርት በሙሉ፡- እንኳን ደስ አላችኹ፤ አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር በየምድብ ዕጣችኹ የመልካም አገልግሎትና የውጤት ዘመን ያድርግላችኹ፤ እያልን መስተጋድላንና መስተጋድላት አኃውና አኃት ደቀ መዛሙርት በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ተላላኪዎች አንፃር የፈጸሙትን ተጋድሎና ቀጣይነቱን በስምሪታቸውም የሚጠብቃቸውን ሓላፊነት በሚያንፀባርቀው በተከታዩ የመጋቤ ሥርዓት ቀሲስ ዮሴፍ ተስፋዬ ግጥም እንሰናበታችኋለን፡፡
ትምህርተ ክርስቶስ ነዶውን ላነሣ
ገባኹኝ ዘልዬ ከቄርሎስ ማሳ
በጊዜ መወሰን መመረቅ መውጣቱ
አካዳሚያዊ ሕግ ኾነና ሥርዓቱ
ከመምህራን ማዕድ ልርቅ ነው በውነቱ፤
እርሻውን ላስፋፋ ለመዝራት እንዳቅሜ
ከኮሌጅ ወጣኹ ዘሩን/ቀንበሩን/ ተሸክሜ፤
ከመምህራን ሪቅ ተከማችቶ ስንዴ
ምነው መቀላወጥ ከጎረቤት ጓዴ!
ምን ዕውቀት ባይኖረኝ እነርሱን ባልተካ
እኔስ ባዕድ ምግብ ለዚያውም ያልቦካ፤
ላልጨምር ቃል ገባኹ በጣፋጭ ምግባችኹ
የመምህራን ልጅ ነኝ ምያለኹ በእጃችኹ፤
በመልካሙ መሬት ሊበትን እንክርዳድ
በኮሌጁ ዙሪያ ጠላት ሲንጎራደድ
በኮሌጁ ዙሪያ ሉተር ሲንጎራደድ፣
በአርድዕት በመምህራን ደግሞም በእያንዳንዱ
ተያዘ ዘንድሮ እስከነ እንክርዳዱ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
***
ለትውስታ፡-