ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ኾነው ተመደቡ

ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ኾነው ተመደቡ

ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም

ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬ፣ ጥቅምት ፲፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. አራተኛ ቀን ውሎው የድሬዳዋና ምዕራብ ሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲሠሩ የምደባ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምልአተ ጉባኤው ውሳኔውን ያሳለፈው፣ ከግንቦት ፳፻፭ ዓ.ም. ጀምሮ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ኾነው በነበሩት ብፁዕ አቡነ ዳንኤልና በማኅበሩ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ዙሪያ ከመከረ በኋላ ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ አለመግባባቱን ለመፍታት ፈቃደኛነታቸው ተረጋግጦ በተነሡት ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ቦታ ለመመደብ ያመለከቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጥያቄ መርምሮ ለውሳኔ የሚያቀርብ አምስት ብፁዓን ሊቃ ጳጳሳት የሚገኙበት ኮሚቴ በትላንትናው ውሎው ሠይሞ ነበር፡፡

የኮሚቴው አባላት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ገሪማ፣ አቡነ ቀውስጦስ፣ አቡነ እስጢፋኖስ፣ አቡነ ጎርጎርዮስ እና አቡነ ዲዮስቆሮስ÷ ለምልአተ ጉባኤው ምክረ ሐሳባቸውን ካቀረቡ በኋላ ከፍተኛውን ድምፅ ያገኙት ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም እንዲመደቡ መወሰኑ ታውቋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ከጥቅምት ፳፻፭ ዓ.ም. ጀምሮ የድሬዳዋና ምዕራብ ሐረርጌ አህጉረ ስብከትን ሲመሩ ቆይተዋል፡፡

በተለይም ሥራው ለስድስት ዓመታት የተጓተተው የሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ግንባታ ጥራትና ሒሳብ በውጭ ኦዲተር እንዲመረመር ቋሚ ሲኖዶስ ያሳለፈውን ውሳኔ ከደብሩ አስተዳደር ጋራ ኾነው በማስፈጸማቸው ከፓትርያርኩ ጋራ ቅራኔ ውስጥ ገብተው ቆይተዋል፡፡

እስከ ልዩ ጽ/ቤት በተዘረጋ የሙስና ሰንሰለት ከስምንት ሚልዮን ብር በላይ የምእመናን ገንዘብ መመዝበሩ የተረጋገጠበት የኦዲት ሪፖርት፣ በደብሩ ጽ/ቤት ለምእመኑ ይፋ መኾኑን ተከትሎ ‹‹የደብሩ ሰላም ይታወካል›› በሚል ሰበብ የደብሩ አለቃ ያለብፁዕነታቸው ዕውቅና በፓትርያርኩ ቀጥተኛ ትእዛዝ ተነሥተው ያለሥራ እየተንገላቱ ይገኛሉ፡፡

ፓትርያርኩ ለአማሳኞች የምዝበራ ሰንሰለት ሽፋን የሚሰጠው የጣልቃ ገብነት ርምጃቸው ስሕተት መኾኑን አምነው ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱን ይቅርታ ቢጠይቁም በኦዲት ሪፖርቱ ግኝቶች ዙሪያ የፀረ አማሳኞች ትብብሩን   ያጠናከረው የከተማው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አገልጋይና ምእመን፣ ምዝበራን ያጋለጡት አለቃ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱና ከዚኽ ውጭ የሚደረግ ምደባን ላለመቀበል በመወሰኑ ደብሩ ያለአስተዳዳሪ እንደሚገኝ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በአህጉረ ስብከቱ በብፁዕነታቸው ቦታ የሚመደቡትን ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ በተመለከተ ምልአተ ጉባኤው ለጊዜው ባይወስንም አህጉረ ስብከቱ በተለይም የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የተወላጅነት መቧደንንና አስተዳደራዊ ችግሮችን ከለላ ባደረጉ የኑፋቄ ርዝራዦች የሚታመስበት ችግር ከፍተኛ ትኩረትና አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚሻ ተመልክቷል፡፡

 


ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ኾነው ተመደቡ

Read more http://haratewahido.wordpress.com/2014/10/25/%E1%89%A5%E1%8D%81%E1%8B%95-%E1%8A%A0%E1%89%A1%E1%8A%90-%E1%8B%95%E1%8A%95%E1%89%A3%E1%89%86%E1%88%9D-%E1%8B%A8%E1%8A%A2%E1%8B%A8%E1%88%A9%E1%88%B3%E1%88%8C%E1%88%9D-%E1%88%8A%E1%89%80-%E1%8C%B3/