ሰበር ዜና – ቋሚ ሲኖዶስ: የተሐድሶ ኑፋቄ በኮሌጆች የሚገኝበትን ኹኔታ የሚያጠና ኮሚቴ ሠየመ፤ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያኑ የእምነት መግለጫ ምላሽ እን
- Details
- Created on Friday, 12 February 2016 08:47
- Written by haratewahido
- በመንበረ ፓትርያርኩ ይፋዊ መግለጫ ይሰጥበታል
- አሳታሚው እና ማተሚያ ቤቱ በሕግ ይጠየቃሉ
ቋሚ ሲኖዶስ፥ በዛሬ፣ የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው፣ ለቤተ ክርስቲያናችን የህልውና ስጋት የኾነውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ከመከላከልና ከማጋለጥ አኳያ ወሳኝ የኾኑኹለት ዐበይት ውሳኔዎችን አሳልፏል፤ ትእዛዞችንም ሰጥቷል፡፡
የተሐድሶ መናፍቃን፣ መንፈሳውያን ኮሌጆችን የእንቅስቃሴአቸው ዕንብርትና ማእከል(ስትራተጅያዊ ቦታ) በማድረግ የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮ በአጭር ጊዜ ወደ ፕሮቴስታንታዊ አቅጣጫና መንገድ ለመለወጥ በኅቡእ ስለሚያካሒዱት ዘመቻ የተወያየው ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ኹኔታውን በጥልቀት አጥንተው ለመጪው ግንቦት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሚያቀርቡየፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ኮሚቴአባላትን ሠይሟል፡፡
በጥቅምቱ ምልዓተ ጉባኤ የተቋቋመውን የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቋሚ ኮሚቴ በሚመሩት በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልሰብሳቢነት በኮሌጆቹ ላይ ምርመራውንና ፍተሻውን የሚያካሒዱት የኮሚቴው አባላት ብዛት ስድስት ሲኾኑ እነርሱም፡-
1) መጋቤ ሐዲስ ኃይለ እግዚእ አሰፋ
2) ሊቀ ጠበብት ሐረገ ወይን አገዘ
3) መሪጌታ ሳሙኤል አየሁ
4) ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ
5) ዶክተር በለጠ ብርሃኑ
6) ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ቋሚ ሲኖዶሱ፣“ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ”በሚል ርእስ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ግንባር ቀደም አራማጆች በኅቡእ ላሰራጩት የኑፋቄ ዐዋጅ፣ በመንበረ ፓትርያርኩ ይፋዊ መግለጫ እና በሊቃውንት ጉባኤውም መጽሐፋዊ ምላሽ እንዲሰጥበት በመወሰን ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
እናድሳለን ባዮቹ ግንባር ፈጥረው፣ በስድስት ዐበይት ክፍሎች በ44 ገጾች ያዘጋጁትንና በሠኔ ወር 2007 ዓ.ም. በመጽሐፍ መልክ አሳትመው ያወጡትን ይህንኑ መግለጫ፣ በዚኽ ዓመት ጥቅምት ወር በድብቅ አስመርቀው በማሠራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡
አሳታሚዎቹ፣ በሽፋኑ የማተሚያ ቤቱን ስም ብቻ በማስፈር ስማቸውን ባይጠቅሱም፣ “የወንጌል አገልግሎት ማኅበራት ኅብረት” በሚል ስም በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ግንባር የፈጠሩ የኑፋቄው አራማጆች መኾናቸው ተጠቅሷል፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሕግ አገልግሎት፣ ጉዳዩን እንዲከታተል በቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ትእዛዝ የተሰጠ ሲኾን ማተሚያ ቤቱ እንዲኹም አሳታሚዎቹ በሕግ እንደሚጠየቁ ተገልጧል፡፡
ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያኑ፣ “በማንነት ቀውስ ውስጥ ይገኛል” ላሉት የተለያዩ ቡድኖች የተሐድሶ እንቅስቃሴ፣“የጋራ ራእይና አቅጣጫ ለመስጠት” ግንባር ፈጥረው ያዘጋጁት ይኸው መግለጫ፥ ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያናችንን፣ “እንደ ማንኛውም በምድር ላይ ያለች ቤተ ክርስቲያን” በማለት ነው በተርታነት የሚጠቅሳት፡፡
ነቢያት በትንቢት፣ ሐዋርያት በስብከት፣ ሊቃውንት በትምህርት የተባበሩበትን፤ ትላንትም፣ ዛሬም ነገም ያልተለወጠውንና የማይለወጠውን የቀና እና የጸና ትምህርተ ሃይማኖቷን ደግሞ፣“ከመጽሐፍ ቅዱስ የራቀና ቅይጥ ነው፤ የስሕተት ትምህርቶችና ልምምዶች ተቀላቅለውበታል” በሚል ነው፣ ኦርቶዶክሳዊ ማንነቷን በፕሮቴስታንታዊነት ለመለወጥ “ተሐድሶ ያስፈልጋታል” የሚለው፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ተቋሞቿንና አባላቷን ከኑፋቄው ሤራ ለመጠበቅ በየጊዜው የወሰደቻቸውን የመከላከል፣ የማጋለጥና አውግዞ የመለየት ሉዓላዊና ሕጋዊ ርምጃዎቿንም በመኰነን በአሳዳጅነት ይፈርጃታል፤ ይህም ለኪሳራ እንደሚዳርጋት በመግለጽ ሉተራዊ ዓላማውን ገሃድ አድርጓል፡፡
ምልዓተ ጉባኤው በጥቅምት 2008 ዓ.ም. ስብሰባው፣ የኑፋቄውን አጠቃላይ ወቅታዊ እንቅስቃሴ በማስረጃ አስደግፎ ለውሳኔ እንዲያቀርብ ቀደም ሲል የሠየመውን ኮሚቴ አፈጻጸም ገምግሞ ተጨማሪ መመሪያ የሰጠ ሲኾን፤ ሰባክያንና መምህራን የሚፈልቁባቸው የኮሌጆቻችን የውስጥ ይዘትም(አስተዳደራዊ መዋቅር እና አሠራር)እንዲፈተሽና ደቀ መዛሙርቱን በጥራት ለመቅረፅ የሚያስችል ተቋማዊ ኹኔታ የሚፈጥር ጥናት እንዲቀርብለት ማዘዙ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ በርእሰ መንበሩ እንደተነገረው፣ “ምንጩ ድፍርስ ከኾነ የተጠማው መንገደኛ ውኃ ለመጠጣት ይቸገራልና”፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና ታሪካዊ ትውፊት እንዳይፋለስ የመጠበቅና የማስጠበቅ ዓላማዎች ላሉት ቅዱስ ሲኖዶስ ተጠሪ ኾኖ የውሳኔዎቹንና የመመሪያዎቹን ተግባራዊነት የሚከታተለው ቋሚ ሲኖዶሱ፣ በዛሬው ዐበይት ውሳኔዎች፣ ኮሌጆቹን ከኑፋቄው ተላላኪዎች ለማጥራት በመጋደላቸው ከሥራ እና ከትምህርት ገበታዎቻቸው ከማባረር ጀምሮ የተለያዩ አድልዎች ሲፈጸሙባቸው ለቆዩትና አኹንም በተመሳሳይ ኹኔታ ውስጥ ለሚገኙት ቀናዕያን መምህራን፣ ሠራተኞችና ደቀ መዛሙርት ታላቅ የምሥራች ነው፤ ከኮሌጆቹም ውጭ በተጠናከረ አኳኋን እየተካሔደ ለሚገኘው የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አድማሳዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ የሞራል ብርታት የሚሰጥ በመኾኑ ለፍፃሜው ተገቢው የተቀናጀ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል፡፡