ትኩረት ለአብነት መምህራንና ለአብነት ት/ቤቶች በሚል የአብነት መምህራን ጉባኤ ዛሬ ተጀመረ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/በት በትምህርትና ማሰልጠኛ መምሪያ አማካኝነት ለሁለት3 ቀናት የሚቆይ የምክክር ጉባኤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የወላይታ ኮንታ እና ዳውሮ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎችና ምክትል ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት የአብነት መምህራንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ዛሬ ሰኔ 18 ቀን 2006 ዓ.ም ተጀምሮአል፡፡

ለሁለት ቀናት ሚቆየው የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጸሎተ ቡራኬ ተጀምሮ ጸሎተ ወንጌል በማድረስ ጉባኤው የተከፈተ ሲሆን የጉባኤው አጠቃላይ መንፈስ በተመለከተ ቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት የትምህርትና ማሰልጠና መምሪያ ዋና ኃላፊ የሆኑት ቆሞስ አባ ሠረቀብርሃን ወ/ሳሙኤል ሰፊ መክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም የአብነት ትምህርት ቤቶችና መምህራን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ያህል ዘመን ትምህርትዋንና ቀኖናዋን በአግባቡ ተጠብቆ ዘመን መሻገር የቻለው በአብነት መምህራንና ት/ቤቶች መሆኑን ገልጸው አሁን የሚገባቸው ያህል ትኩረት ባለመሰጠቱ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠው እንደሚገኙ አስምረው የዚህ ጉባኤ ዋና ዓላማም በአብነት መምህራንና ት/ቤቶች ችግሮች ዙርያ ከፍተኛ ምክክርና ውይይት በማድረግ መፍትሔዎች ማፈላለግ፤ ለተግባራዊነቱም በጋራ መንቀሳቀስ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠል ቅዱስ ፓትርያርኩ ሰፋ ያለ ቃለምዕዳንና ቡራኬ በመስጠት ጉባኤው በአብነት መምህራንና ት/ቤቶቹ ዙርያ ከፍተኛ የሆነ ምክክር አድርጎ መፍትሔ እንደሚያፈላልግ ብቻ ሳይሆን መፍትሔ በመስጠትም ጭምር በጋራ በመንቀሳቀስ ዘላቂ የሆነ ሥራ ከጉባኤው እንደሚጠበቅ አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጀርባ አጥንት የሆኑት የአብነት መምህራንና ት/ቤቶች መሰረታዊ የሆነ ችግራቸው ምን ምን እንደሆነ መጀመሪያ ለይቶ አውጥቶ ማጥናት ያስፈልጋል፤ በምክክር የተደረገው ጥናት መሠረት በማድረግ በቀጣይነት ወይም በዘላቂነት ችግሮቹን ለመፍታት ደግሞ ሁላችንም አብረን በጋራ በሕብረት መነሳት አለብን ብለው አጽኦት ሰጥተው ካብራሩ በኋላ መልካም የምክክር መድረክ እንዲሆን ተመኝተው ጉባኤው በይፋ ከፍተዋል፡፡

በመቀጠል በደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሊቃውንት ያሬዳዊ መዝሙር ከቀረበ በኋላ "የአብነት ትምህርት ቤቶች ትናንትናና ዛሬ" በሚል ርእስ በብፁዕ አቡነ ገሪማ የቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግኑኝነት የበላይ ኃላፊ በጉባኤው ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በመጣው መርሐ ግብር መሠረት "የአብነት ት/ቤቶች የመማር ማስተማር ዘዴና ጥራት" የሚል በሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ፣ "የኢትዮጵያ ስልጣኔና የአብነት ትምህርት ቤቶች ሚና" የሚል በንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ፣ "የአብነት ትምህርት ቤቶች የሥርዓተ ትምህርትና የትምህርት ፖሊሲ አስፈላጊነት" በሚል በመምህር ዳንኤል ሠ/ሚካኤል፣ "ወቅታዊ የአብነት ትምህርት ቤቶች ወቅታዊ ተግዳሮቶች" በሚል በአባ ሠረቀብርሃን ወ/ሳሙኤል፣ "የአብነት ትምህርት ቤቶች ለማስፋፋት ከመምህራን ምን ይጠበቃል" የሚል በሊቀ ትጉኃን ኃ/ጊዮርጊስ ዳኘ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ከፍተኛ ውይይት እንደሚደረግባቸው የሚጠበቅ ሲሆን የምክክር መድረክ ጉባኤው የአቋም መግለጫ በማውጣት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡ የተከበራችሁ አንባቢዎች በዕለቱ የሚቀርቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ተከታትለን እናቀርባለን፡፡

Read more http://eotcssd.org/the-news/384-q----q------.html