የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በጄኔብ ተካሄደ
- Details
- Created on Tuesday, 02 September 2014 07:11
- Written by Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Sunday School Department Official Website
የኢ.ኦ.ተ.ቤተክርስቲያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የዋጃት በስሙ የመሠረታት ቤተክርስቲያን ናት ከተቋቋመችበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ውስብስብ ችግር ቢያጋጥማትም ተግባሯ ሳይገታ ዓላማዋም ሳይዛነፍ ከዚህ ደረጃ ላይ ደርሳለች ወልድ ዋሕድ የሚለውን ቃል መሠረት አድርጋ አንድ እግዚአብሔር በሦስት ስም በሦስት ግብር በሦስት አካል አንድ አምላክ ወልደ አብ ወልደ ማርያም በተዋሕዶ ከበረ ብላ ታስተምራለች፡፡ ሆኖም በሃይማኖቷና በነጻነትዋ ጸንታ የምትኖር በመሆንዋ ያለፈተና የኖረችበት ጊዜ የለም፡፡
የኢ.ኦ.ተ. ቤተክርስቲያን እውነተኛና ጥንታዊ ከሚያሰኛት መካከል ሦስቱን ዐበይት ጉባኤያት የኒቂያን፣ የቁስጥንጥንያን እና የኤፌሶንን ጉባኤያት ተቀብላ አክብራ በመያዝዋ ነው፡፡ አራተኛው የኬልቄዶን ጉባኤ ግን አንድ ክርስቶስን ለሁለት የሚከፍል በመሆኑ አልተቀበለችውም፡፡ ይህ መለያየት ቤተክርስቲያንን እየከፋፈለና እየለያየ ከመሄዱም በላይ የዓለም ሥጋዊ መሪዎች የሃይማኖት ነገር በጉዳያችን ውስጥ አይገባም እስከማለት እንደደረሱና ከዚያም አልፎ እግዚአብሔር የለም ወደ ሚለው ስንፍና እንዲያመሩ አድርጓቸዋል፡፡
ይህም በቤተክርስቲያን አባቶች ልቦና ብርቱ መቆርቆር እና መነሳሳትን ስላአሳደረ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እንተባበር ሕብረትም ይኑረን የሚለው የተስፋ ብርሃን መታየት ጀመረ ይህም ተስፋ ለዐበይት ጉባኤያት ልደት (ምክንያት) ሆኖአል፡፡
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ከተመሠረተ 66 ዓመት አስቆጥሮአል ቦታውም በአምስተርዳም ከተማ ነበር አሁን የሚገኘው ግን በጄኔብ ከተማ በስዊዘርላንድ ራሱ ባሠራው መሥሪያ ቤት ነው፡፡
ይህ ማኅበር ሲመሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የማኅበሩ መሥራች እና አባልም ናት በአሁኑ የ2006 ዓ/ም የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የተገኘነው እኔ ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም መለሰ እና አቶ ይልቃል ሽፈራው ስንሆን ጉባኤው የተካሄደው በስዊዘርላንድ ጄኔብ ከተማ በዋናው ማዕከል ነው፡፡ የስብሰባው ጊዜም ከሰኔ 24-ሐምሌ 2 ቀን 2006 ዓ/ም ነበር መሪ ቃሉም ‹‹Apilgrimage of Justice and peace›› "የፍትሕና የሰላም አንድነት ጉዞ" በሚል ርዕስ መነሻ በማድረግ ስብሰባውን ጀምሮአል የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት በግጭት ጊዜ ለጋራ ጥቅም በሕብረት መቆም እንደሚገባ፣የአየር ለውጥ ምን ያህል ለዓለም ሥጋት እንደሆነ፣ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን፣የኦርቶደክስ ተከታዮች የራሳቸውን ውይይት ማድረግ፣በየአህጉሩ ማለትም አፍሪካ፣ ኢስያ አሜሪካ፣ላቲን አሜሪካ፣ በየክፍለ አህጉሩ ውይይት ተደርጓል፡፡ ዕቅዶችን ማፅደቅና በሥራ አስፈጻሚው የተዘጋጁትን የተለያዩ አጀንዳዎችን ማፅደቅ ነበር ባጋጠሟቸውም ችግሮች ዙሪያ ውይይት የተደረገ ሲሆን በተለይ ከኦርቶዶክስ ተሰብሳቢዎች መካከል ለነገዋ ቤተክርስቲያን ኦርቶዶክስን ወክሎ በዓለም አብያተ ክርስቲያናትም ሆነ በሌላ መድረክ ለቤተክርስቲያን የሚቆምና ሊመሰክር የሚችል ትውልድ ከመድረክ እንዳይጠፋ ወጣት ኦርቶዶክስ ምሑራንን ማበረታታት እንዲሁም ሴት የትምህርተ መለኮት ሊቃውንትም እንዲኖሩ እህቶችን ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ልዩ በስብሰባው ላይ የተነሱ የውይይት አጀንዳዎች ነበሩ በሥራ አስፈጻሚው የቀረቡ የተለያዩ አጀንዳዎችም ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡እኛም ቤተክርስቲያናችንን በሚመለከት በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ተገቢውን ማብራሪያ በመስጠትና ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የስብሰባው ፍጻሜ በሽኝት ጸሎት ተጠናቋል፡፡
በዕለተ እሁድ ጄኔባ በሚገኘው የኢ.ኦ.ተ የመድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በመገኘት ሥርዓተ ቅዳሴውን በመምራትና በማስተማር ምዕመናኖቻችንን አገልግለናል በዛ የሚገኙ ማኅበረ ምእመናንም በአንድነት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በአንድነትና በሕብረት ልጆቻቸውን በማቁረብ ሃይኖታቸውን ጠብቀው እንዲያድጉ የሚያደርጉት ጥረትና በመካከላው የሚታየው ማህበራዊ ትስስር የሚበረታታ ነው ለዚህ ደግሞ ታላቅ ተሳትፎ ያደረጉት የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ናቸው፡፡ ከምእመናንም መካከል ዶ/ር ንጉሡና ባለቤታቸው ከሄድንበት ቀን ጀምሮ እስክንመለስ ድረስ በኢትዮጵያውነት ባህል በማስተናገድ እንዲሁም አቶ መላኩና ባለቤታቸው ሲፎራ በተጨማሪም በስዊዘርላንድ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሠራተኞች በመገኘት የሽኝት የእራት ግብዣ በማድረግ ደስታቸውን ገልጸውልናል እኛም እግዚአብሔርን በማመስገን ስለተደረገልን መስተንግዶ በቤተክርስቲያን ስም ምሥጋና አቅርበናል፡፡
አባ ኃ/ማርያም መለሰ (ዶ/ር)
በጠቅላይ ቤተክህነት ም/ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማዕከላዊ ኮሚቴና
የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል
Read more http://eotcssd.org/the-news/390-2014-09-02-13-13-12.html