ቅዱስ ፓትርያርኩ የመቄዶንያ አረጋውያንና ሕሙማን ጎበኙ
- Details
- Created on Tuesday, 30 September 2014 06:04
- Written by Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Sunday School Department Official Website
በቤተ ክርስቲያኗ ስም መቶ ሺህ ብር ለተረጂዎች ድጋፍ አድርገዋል
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መስከረም 17 ቀን 2007 ዓ.ም ከጥዋቱ በሦስት ሰዓት አረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን ወገኖቻችን ከሚረዱበት በመቄዶንያ አረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ዘንድ በመገኘት ጉብኝትና በቤተ ክርስቲያኒቷ ስም ለመረጃ ማእከሉ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የመቄዶንያ መርጃ ማዕከል ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር ዶ/ር ፀጋዬ በርሄ እንደገለፁት መርጃ ማዕከሉ በአንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ /አቶ ቢንያም/ አማካኝነት የተጀመረ መሆኑን ገልጸው አሁን ግን ከስድስት መቶ አረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን አገልግሎት በማግኘት ላይ እንደሚገኙ በስፋት ገልጸዋል፡፡ የመርጃ መዕከሉ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆነው ወጣት ቢንያም በበኩሉም ይህን መርጃ ማዕከል በጥቂት ሰዎች ጀምሮ አሁን በሦስት ማዕከላት ከስድስት መቶ ተገልጋዮች በላይ መኖራቸውን ገልጸው እነዚህ ወገኖች የሚረዱት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ስለሆነ ሁሉም በጎ አድራጊ ወገኖችን ምስጋና ካቀረቡ በኋላ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግን ለምታደርግላቸው ሁለገብ ድጋፍ ምስጋናቸውን ከፍ ያለ መሆኑ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በቦታው ለተገኙ አረጋውያንና ለመረጃ ማዕከሉ ሠራተኞች ሰፊ አባታዊ ቡራኬና ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፡፡ በቃለ ምዕዳናቸውም "ተርቤ አብልታችሁኛልና፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፣ ታርዤ አልብሳችኁኛልና" የሚል ቃለ ወንጌል መሠረት አድርገው ለአገልጋዮችና ለተገልጋዮች የማጽናኛና የበረከት ትምህርት ካስተማሩ በኋላ በመርጃ ማዕከሉ ለሚገኙ አረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን መርጃ የሚሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስም መቶ ሺህ ብር በመስጠት ማዕከሉን አበረታቷል፡፡ የተከበራችሁ አንባቢዎች በወቅቱ የተደረገውን ጉብኝት በተመለከተ የሚያሳይ ቪድዮ እንድትመለከቱ አቅርበናል፡፡