መስቀል በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ
- Details
- Created on Tuesday, 30 September 2014 05:59
- Written by Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Sunday School Department Official Website
መ/ር ፀገዬ ኃይሌ
መስቀል በብዙዎች ሰዎች ኀሊና በብዙ ዓይነትና ቅርጽ የተሰራ ተደርጎ የሚታዩ ወይንም የሚተረጎም ቢሆንም እኛ ግን ከዘመነ ብሉይ መጀመሪያ እስከ ዘመነ ሐዲስ እስከ አለንበት ዘመን ስለአለው ስለክርስቶስ ነገረ መስቀል እንናገራለን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል አስቀድሞ ከዘመነ አበ ብዙኃን ከአዳም ጊዜ ጀምሮ ብዙ ነቢያት በተለያየ ኅብረ አምሳል ትንቢት የተናገሩለት በዘመነ ሐዲስም እራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአት የወደቀውን የሰውን ልጅ ከራሱ ጋር ያስታረቀበት እስከ አሁንም ድረስ አስቀድሞ የክፋት ምንጭ የሆነው ዲያብሎስ ሰውን ከፈጣሪው እንዲለይና መከራ ውስጥ እንዲወድቅ እንዳደረገው አሁንም ደግሞ ለተመሳሳይ ፈተና እንዳያጋልጠው ሥልጣነ አምላክ በተሰጣቸው ሐዋርያትና ደቀመዛሙርቶቻቸው አማካኝነት በተናገረው ቃሉና በተሰቀለበት ዕፀ መስቀል እራስ እራሱን እየቀጠቀጡበት ለሚያምኑበት ብልሃት ለማያምንኑበት ሞኝነት ሆኖ ሲጠብቀን ይኖራል፡፡
መስቀል በብሉይ ኪዳን
መስቀል በብሉይ ኪዳን በነበሩ ሰዎች ዘንድ በተለያየ ቅርጽ እና ከተለያዩ ቁሳቁስ ማለትም ከብረት ከእንጨትና ከከበሩ ማዕድናት ይሠራ እንደነበር ብዙ ጸሐፍትና መምህራን በአፍም በመጽሐፍም ሲጽፉና ሲያስተምሩ ይነገራል፡፡ እንሰማለን አምሳለ ቅርጹንም በቲ (T) በኤክስ (X) በመስቀል አይነት ቅርጽ ይሰራ እንደነበር ብዙዎች ሰዎች ሲጽፉ አገልግሎቱም እንደየ ሀገሩና እንደአካባቢው የተለያየ ቢሆንም በኢትዮጵያን ነገሥታት ዘንድ እንደአርማ ይጠቀሙበት በእጃቸውም ይይዙት በጦርነት ጊዜም በዘንግ አምሳል እንደሚይዙት እንዲሁም በፈረሶቻቸው ግንባር ላይ ይስሉት እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ በሌሎችም የዓለም ብዙ ሀገራት ዘንድ ከኢትዮጵያ ነገሥታት በተመሣሣይ የሚጠቀሙበት ጥቂት ነገሥታት የነበሩ ቢሆንም ብዙዎቹ ነገሥታት ግን ለጥፋተኛ ሰው መስቀያ ይጠቀሙበት እንደነበር በቂ የጽሑፍ ማስረጃዎች ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በግብፅ በፊንቄ ግሪክ ሮማ ፋሪስ አሥር ካርቴጅና ሕንፃ ለወንጀለኛች መስቀያ ይጠቀሙበት እንደነበር በቀዳሚነት ሲጠቀሱ ለአተገባበራቸውም የተለያዩ ትርጓሜ እንደነበራቸው ያስቀምጣሉ፤
ለምሳሌ በፋሪስ ወንጀለኛን በመስቀል መስቀል እንደተጀመረ ሲገልጹ ምክንያቱንም በዘመኑ የነበሩ የፋሪስ ነገሥታት ሕዝብ በመሬት የሚያመልኩ ስለነበሩ እና የሰው ደም በመሬት ከፈሰሰ ያረክሳል ብለው ስለሚያምኑ ከመሬት ከፍ አድርገው በመስቀል ላይ ይሰቅሉ ነበር ይላሉ ሮማዊያንም ከእነርሱ ወስደው እንደተገበሩትም ይጽፋሉ፡፡
የመስቀል ኅብረ አምሳል በብሉይ ኪዳን
ነቢያት በተገለጸላቸዉ መጠን መስቀልን በተለያየ ኅብረ አምሳል ሲገልጹ ቆይተዋል
1. በገነት ውስጥ ያለው ዕፀ ሕይወት /ዘፍ. 10፡22/
2. ኖኅ ከነቤተሰቡ የደንበት የመርከብ እንጨት /ዘፍ. 6፡14-22/
3. ለይስሐት ቤዛ የሆነው በግ የታሰርበት ዕፀ ሳቤቅ /ዘፍ. 22፡13-19/
4. ሙሴ የኤርትራን ባሕር የከፈለባት በትረ ሙሴ ዘፀ. 14፡16፣17፥9
መስቀል በሐዲስ ኪዳን
አበ ብዙኃን አደም ዕፀ በለስን በልቶ ቢሞት ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ንስሐ በመግባቱና በመጽደቁ ምክንያት የቀዳማዊ አደምን ሞት በሞቱ ሽሮ ወደ ቀደመ ክብሩ እንደሚመልሰው በገቡት ቃል መሠረት ቃሉን ፈጽሞ ሞቱን በሞቱ ሽሮ ወደ ቀደመ ክብሩ የመለሰው በሰውና በፈጣሪው መካከል የነበረው የደብ ግድግዳ የፈረሰበት ቀራንዮ ላይ የተዘረጋው የፍርድ ወንበር ነው /ኤፌሶን 2፡12-19/ ቆላሲስ 1፡19፡፡
ትግሥትን የምንማርበት መጽሐፍ ነው
ቀዳማዊ አደም በኃጢአት ምክንያት ወድቆ ረጅምና መራራ ኃዘን የደረሰበት ለርሱ ብቻ ሳይሆን ከእርሱ ለተገኙት ለልጆቹ ሁሉ ነበር ሆኖም ግን በጠየቁት ይቅርታ መሠረት የተስፋ ቃሉ እስከሚደርስ ድረስ የጠበቁት በትዕግሥት ነበር የእውነት ባለቤት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም ለእነርሱ የገባውን ቃል የፈጸመው በተመቻቸ ሁኔታ ሳይሆን እጅግ በጣም አሰቃቂ በሆነ ፀዋትወ መከራ ሲሆን መከራውን በመታገሥ ብቻ ሳይሆን ከእርሱ እንድንማርም አባት ሆይ ይቅር በላቸው በማለት እኛም መማርን ትዕግሥትን አስተምሮናል፡፡ ዕብራዊያን 12፡1-2 ኤፈሶን 2፡14-17
መመኪያችን ነው
ጌታችን መድኃኒታችን በመስቀል ላይ መከራን ተቀብሎ ያስተማረን ወደቀደመ ክብራችን መመለሳችን ብቻ ሳይሆን ወደቀደመ ኃሣራችንም እንድንመለስ ክፉ መካሪ ከሆነው ዲያብሎስ ምክር ርቀን የቀደሙትን ጎጂ ባሕሎቻችን ትተን አዲስ ልብስ እንድንለብስና ጠላታችን ዲያብሎስን በመስቀሉ ድል እያነሳነው እንድንኖር ነው ገላትየ. 6፡14፡፡