የ33ኛ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጀመረ፡፡
- Details
- Created on Wednesday, 15 October 2014 04:57
- Written by Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Sunday School Department Official Website
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የሚካሔደው ዓመታዊ የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ዛሬ ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የወላይታ ኮንታ ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፣ የሁሉም አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችና ልዑካን፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተጀመረ ፡፡
የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ካህናት ጸሎተ ወንጌል በማድረስ የተጀመረ ሲሆን፤ የቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት መዘምራን ያሬዳዊ መዝሙር በማቅረብ የጉባኤውን ጅማሬ አብስረዋል ፡፡ በመቀጠል ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የእንኳን ደኅና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬና ቃለ ምዕዳን እንዲሰጡ በጋበዟቸው መሠረት ሰፊ አባታዊ ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን አዲሱን ዘመን ሥራ የምንሠራበት፣ የተጣመመ የምናቀናበት፣ የሚጎለንን የምንሞላበት ዘመን እንዲሆን ከተመኙ በኋላ ከቅርብ ዘመናት ወዲህ እየታየ ያለው የምእመናን ቁጥርን መቀነስ እጅግ በጣም አሳዛኝ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን ለስብከተ ወንጌል ተልዕኮ ከፍተኛ ትኩረትና ብርቱ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል ፡፡
መልካም አስተዳደርን በተመለከተ በቤተ ክርስቲያናችን በምልዓት ሊሰፍን የሚገባ መሆኑንና በዚህ ምክንያትም ቤተ ክርስቲያናችን የነበራትን ጥንተ ልዕልናና ክብር አስጠብቃ መቀጠል አልቻለችም ፡፡ ስለዚህ የመልካምነት ሁሉ መገኛ የሆነችውቤተ ክርስቲያናችን መልካም አስተዳደርን ሙሉ በሙሉ በማስፈን ያጣናቸውን ጥንተ ታሪኮቻችንን በሙሉ መመለስ ይኖርብናል ፡፡
በሀገራችን ብሎም በዓለማችን ለሕዝባችንና ለሀገራችን ከፍተኛ ውርደት የሆነው የሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን አስከፊነት በተመለከተ ከስብከተ ወንጌል ጎን ለጎን ሁሉም ሊቃውንት አበክረው እንዲያስተምሩ አደራ ጭምር አስተላልፈዋል ፡፡
በመጨረሻም በየወቅቱ እየተነሡ የሰው ልጅን በመቅሰፍ ላይ የሚገኙ በሽታዎች እግዚአብሔር በድንቅ ጥበቡ ከዓለማችን እንዲያስወግድልንና ወደሀገራችንም እንዳይገቡ አጥር ቅጥር ሁኖ እንዲጠብቀን በሁሉም ዘንድ ከገጠር እስከ ከተማ ጸሎተ ምኅላ እንዲደረግ መልእክት በማስተላለፍ ቃለ ምዕዳናቸውን አጠናቀዋል ፡፡
ጉባኤው በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ሪፖርት አቅራቢነት የተጀመረ ሲሆን ሁሉም አህጉረ ስብከት በተያዘላቸው መርሐ ግብር መሠረት ሪፖርታቸውን እያቀረቡ ጉባኤው በመካሔድ ላይ ይገኛል ፡፡
የተከበራችሁ አንባቢዎች የጉባኤው መክፈቻ መርሐ ግብር በድምፅ ወምስል፣ የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አጠቃላይ ሪፖርት ያቀረብን ሲሆን የጉባኤውን መንፈስ እየተከታተልን የምናቀርብ መሆናችንን እንገልጻለን ፡፡