ሥርዓት ዘሰሙነ ፍልሰታ
- Details
- Category: Mahbere Kidusan
- Published on Saturday, 17 August 2013 03:40
- Written by ማሕበረ ቅዱሳን
- Hits: 1830
ነሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም.
በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓመት ውስጥ የተለያዩ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ የሆኑ ተግባራትን ታከናውናለች፡፡ ዋጋ የሚያሰጡ፣ ከፈጣሪ የሚያስታርቁ በዓላትንም ታከብራለች፤ ለምሳሌ በዓለ ልደት፣ በዓለ ጥምቀት፣ በዓለ ትንሣኤ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለእነዚህ በዓላት የተለያየ የአከባበር ሥርዓት አላቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያናችን ኃጢአትን የሚያስተሰርዩ፣ ከፈጣሪ የሚያስታርቁ፣ ሥጋ ለነፍስ እንድትገዛ የሚያግዙ፣ ከባሕርየ እንስሳ ወጥተን ሰማያውያን መላእክትን እንድንመስላቸው የሚያደርጉ የተለያዩ የአዋጅና የፈቃድ አጽዋማት አሏት፡፡ እነዚህን ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተግባራት የምታከናውን ቤተ ክርስቲያን የምትመራው በዘፈቀደ ሳይሆን እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ የሚያደርግ፣ ከመደናገር የሚያድን ግልጽና ወጥ ሥርዓት አላት፡፡ ምክንያቱም የመሠረታት እግዚአብሔር በወዳጆቹ ቅዱሳን አድሮ “ሁሉም በአግባብና በሥርዓት ይሁን” ብሎ መክሯታልና /1ቆሮ.14፥40/፡፡
ስለሆነም ምእመናን በሥርዓት እንዲመሩና፣ ሥርዓት ከሌላቸው ወገኖችም እንዲጠበቁ አጥብቃ ትመ ክራለች ታስተምራለች፡፡ ይህም ከፈጣሪዋ ያገኘችው ሰማያዊ ትምህርት ነው፡፡ “ወንድሞች ሆይ፤ ከእኛ እንደተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዝዛችኋለን” በማለት ለቤተ ክርስቲያን ምርጥ ዕቃ አድርጎ ባዘጋጀው በቅዱስ ጳውሎስ አድሮ ተናግሯልና /2ተሰ.3፥6/፡፡ እነዚህና የመሳሰሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችም የሥርዓትን አስፈላጊነት በግልጽ ያሳዩናል፡፡ በእርግጥም እንኳንስ ዓለም አቀፋዊ የሆነችዋን ተቋም ቤተ ክርስቲያንን ቀርቶ ሥርዓት ከሌለ ቤተሰብንም ቢሆን ለመምራት አይቻልም፡፡ “እርስ በርሷ የምትለያይ ቤት አትጸናም” የተባለው ለዚህ ነው /ማቴ. 12፥25/፡፡ በዘመናችን ሥርዓት እንደ ማያስፈልግ የሚያወሩ ቢኖሩም በሥርዓት ትመራ ዘንድ ከፈጣሪዋ የታዘዘች ቤተ ክርስቲያናችን ለዘመናት የዘለቀችው በሕጉ በሥርዓቱ የምትመራ በመሆኗ እንደሆነ ልናስተውል ይገባናል፡፡
በርሳችን እንደተጠቀሰው ቤተ ክርስቲያናችን በሥርዓት ከምታከናውናቸው ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዱ ጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ይህ ጾም በክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በሐዋርያት የተጀመረና፣ ብዙ ምእመናንን ዋጋ እያሰጠ ረጅም ዘመናትን ተሻግሮ ከዚህ የደረሰ ከፈጣሪ የምንታረቅበት፣ ውስጣዊ ፍላጎታችንን ከእግዚአ ብሔር የምናስፈጽምበት ታላቅ ጾም ነው፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲ ያናችን ለልደት፣ ለጥምቀት፣ ለዐቢይ ጾም፣ ለሰሙነ ሕማማት፣ ለትንሣኤ ወዘተ ልዩ ልዩ ሥርዓቶችን እንደም ታከናውን ሁሉ በሰሙነ ፍልሰታም በውስጥና በውጭ ከሌሎቹ ጊዜያት ለየት ያሉ ሥርዓቶችን ታከናውናለች፡፡ የሰሙነ ፍልሰታ ሥርዓት በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል፡፡ የውስጥና የውጭ በሚል፡፡
ሀ. በውስጥ
፩. ሰዓታት፡- ሰዓታት የኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ የደረሰው ድርሰት ሲሆን እመቤ ታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር የምትመሰገንበትና ከልጇ ከወዳጇ እንድታማልደን እንድታ ስፈጽመን የምንማጸንበት የጸሎት ክፍል ነው፡፡ ይህን ጸሎት ካህናቱ፣ ሊቃውንቱ፣ ዲያቆናቱ በመጀመሪያው ሰዓተ ሌሊት ጀምረው በያሬዳዊው ሰማያዊ ዜማ ሙሉ ሌሊቱን ሲማጸኑ ያድራሉ፡፡ ምእመናንም በረከቱ ይደርሳቸው ዘንድ ከሊቃውንቱ፣ ከካህናቱና ከዲያ ቆናቱ ጋር ቁመው የእናት አማላጅ አድርጎ እመቤታችንን የሰጠ ፈጣሪያቸውን፣ ሲያመሰግኑ፣ ድንግልን አማልጅን በማለት ሲማጸኑ ያድራሉ፡፡
፪. ኪዳን፡- በሰሙነ ፍልሰታ ሊቃውንቱ፣ ካህናቱ፣ ዲያቆናቱ ቆመው ላደሩት ሰዓታት ማጠቃለያው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዮሴፍና ለኒቆዲሞስ የገለጠላቸው፣ ለሐዋርያት ያስተማራቸው ኪዳን የተሰኘው ጸሎት ነው፡፡ በሰዓታት ያደሩ ልዑካንና ምእመናንም ከባድ ችግር ካልገጠማቸው በስተቀር ኪዳን ሳይደርስ ወጥተው አይሔዱም፡፡ ሊሔዱም አይገባም፡፡ ምክንያቱም ማሳረጊያው ጸሎተ ኪዳን ነውና፡፡ ስለሆነም ሰዓታቱ ከተፈጸመ በኋላ ጥዋት ኪዳን ይደርሳል፡፡
፫. ስብሐተ ነግህ፡- ስብሐተ ነግህ ማለት ከስሙ እንደምንረዳው የጥዋት ምስጋና ማለት ነው፡፡ የሌሊቱ ምስጋና ሰዓታቱና ኪዳኑ ከተከናወኑ በኋላም በየዕለቱ በነግህ የዜማ ባለሙያዎቹ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን /መሪጌታዎች/ በያሬዳዊ ዜማ ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንም አማልጅን እያሉ ይማጸናሉ፡፡ ምስጋናውም ወቅቱን ያገናዘበና በእመቤታችን ማንነት ላይ የሚያተኩር ነው፡፡
፬. ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፡- ውዳሴ ማርያም ማለት እመቤ ታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምትመሰገንበት፣ ምእመናን በየዕለቱ የሚጸልዩትና ሊጸልዩትም የሚገባ በሰባቱ ዕለታት የተከፋፈለ ጸሎት ነው፡፡ ደራሲውም ቅዱስ ኤፍሬም ይባላል፡፡ ይህ ቅዱስ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅር በልቡናው የተጻፈበት ጠንካራ ክርስቲያን ነበር፡፡ ከፍቅሯ ጽንአት የተነሣም የእመቤታችን ምስጋና እንደ ሰማይ ኮከብ እንደ ምድር አሸዋ በዝቶልኝ፣ እንደ ልብስ ለብሼው፣ እንደ መጎናጸፊያ ተጎናጽፌው፣ እንደ ምግብ ተመግቤው እያለ ይመኝ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስም ከልብ የለመኑትን መስጠት ልማዱ ነውና እልፍ ከአራት ሺህ ድርሰት እንዲደርስ አድርጎታል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም “አኀዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ፤ አቤቱ በእኔ ላይ ያሳደርኸውን የድርሰት መንፈስ እንዲገታ አድርግልኝ” እስከ ማለት ደርሷል፡፡ ከእነዚህ ድርሰታትም “ውዳሴ ማርያም” አንዱ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን ከሉቃስ ወንጌል “ወበሳድስን /በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል ወደ አንዲት አገር ተላከ” የሚለውን /ሉቃ.1፥26/ “ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምን አውጥቶ በእመቤታችን ዕድሜ ልክ ስልሳ አራት፣ ስልሳ አራት ጊዜ ይጸልየው ነበር፡፡
ከዕለታት ባንድ ቀን ዕለቱ ሰኞ፥ ጊዜው ጠዋት ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም የጠዋት ተግባሩን /ጸሎቱን/ አድርሶ ተቀምጦ ሳለ እመቤታችን መጣች፡፡ የብርሃን ድንኳን ተተከለ፣ የብርሃን ምንጣፍ ተነጠፈ፣ የብርሃን ድባብ ተዘረጋ፡፡ ከዚያ ላይ ሆና “ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም ወፍቁረ ወልድየ፤ ወዳጄ፣ የልጄም ወዳጅ ኤፍሬም ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን አላቸው፡፡ እርሱም ታጥቆ እጅ ነሳትና ቆመ፡፡ እመቤታችንም “ወድሰኒ አመስግነኝ” አለችው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም “እፎ እክል ወድሶተኪ ዘኢይክሉ ወድሶ ተኪ ሰማያውያን ወምድራውያን፤ ምድራውያን ጻድቃን ሰማዕታት ሰማያውያን፣ መላእክት አንቺን ሊያመሰግኑሽ የማይቻላቸው ሲሆን እኔ እንደምን ይቻለኛል አላት፡፡
እመቤታችንም “በከመ አለበ ወከ መንፈስ ቅዱስ ተናገር፤ መንፈስ ቅዱስ እንደገለጠልህ አመስግን” አለችው፡፡ እሷ “ወንድ ሳላውቅ መፅነስ እንደምን ይቻለኛል? ብላ መልአኩን በተከራከረችው ጊዜ “መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል” ብሎ ረትቷት ነበርና እመቤታችንም “መንፈስ ቅዱስ እንደገለጠልህ አመስግን በማለት ረቂቁንና የማይ ቻለውን ነገር ለመንፈስ ቅዱስ በመስጠት ቅዱስ ኤፍሬምን ረታችው/አሳመነችው/፡፡ በተረቱበት ይረ ቱበት የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡
ቅዱስ ኤፍሬምም “መንፈስ ቅዱስ አይገልጥልኝም ብልማ ክህደት ይሆንብኝ የለምን” ብሎ ሌላ ጥያቄ ሳያነሣ ባርኪኝ አላት፡፡ እመቤታችንም “በረከተ ወልድየ ወአቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ ይኅደር በላእሌከ፤ የልጄ የአባቱ የመንፈስ ቅዱስም በረከት በአንተ ላይ ይደር አለችው፡፡ እርሱም ተባርኮ ምስጋናዋን ጀመረ፡፡ ሲያመሰግናትም ደቀ መዝሙር ቅኔ ቆጥሮ እንዲቀኝ ድርሰት ደርሶ እንዲጽፍ አይደለም፡፡ ብልህ ደቀ መዝሙር የተማረውን ቃለ እግዚአብሔር በመምህሩ ፊት ምንም ሳያሳስት ሰተት አድርጎ እንዲያደርሰው ሰተት አድርጋ አስደርሳዋለች፡፡
ስታስደርሰውም በሰባቱ ዕለታት ከፍላ አስደርሳዋለች፡፡ ስለምን ቢሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሰባቱ ዕለታት ሁሉ እንድ ትመሰገን ፈቃዷ ስለሆነ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሰባቱ ዕለታት ምሳሌዎቿ ናቸው፡፡ እመቤታችን በዕለተ እሑድ ትመሰላለች፡፡
በዕለተ እሑድ አሥራው ፍጥረታት /የፍጥረታት መሠረቶች/ የሆኑ አራቱ ባሕርያት ተገኝተዋል፡፡ እነዚህም መሬት፣ ውኃ፣ እሳትና ነፋስ ናቸው፡፡ የፍጥረታት ሁሉ ጥሬ ዕቃ ዎች /መገኛዎችም/ እነዚህ ናቸው፡፡
ዕለተ እሑድ ለፍጥረታት መሠረት የሆኑ እነዚህን እንዳስገኘች ሁሉ እመቤታችንም የፍጥረታት ሁሉ መገኛ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አስገኝታለችና ስለዚህ ነው፡፡
በዕለተ ሰኑይ /ሰኞ/ ትመሰላለች፡- ከመሬት እስከ ሰማይ ያለው ቦታ በውኃ የተሞላ ነበር፡፡ በዕለተ ሰኑይ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ውኃን ከሦስት ከፍሎታል፡፡ አንዱን እጅ ከላይ ሰቅሎታል፤ ሀኖስ ይባላል፡፡ ብጥብጥ ውኃ ነው፡፡ አንዱን እጅ በዙሪያው ወስኖታል፤ ውቅያኖስ ይባላል፡፡ አንዱን እጅ ከሀኖስ በታች ወስኖታል፤ ጠፈር ይባላል፡፡ የብርሃን መመላለሻ ነው፡፡ ዕለቲቱ የእመቤታችን ምሳሌ፣ ጠፈር ከእመ ቤታችን የነሣው ሥጋ፣ ብርሃን የጌታ ምሳሌ ነው፡፡
በዕለተ ሠሉስ /ማክሰኞ/ ትመስ ላለች፡፡ በዕለተ ሠሉስ “ለታብቊል ምድር “ሐመልማለ ሣዕር ዘይ ዘራእ በበዘርዑ፣ ወበበዘመዱ….. ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደወገኑ ታብቅል” ባለ ጊዜ በእጅ የሚለቀሙ አትክልት፣ በማጭድ የሚታጨዱ አዝርእት፣ በምሳር የሚቆረጡ ዕፅዋት ተገኝተዋል /ዘፍ.1፥11/፡፡ እነዚህም ለሥጋ ውያን ፍጥረታት ምግቦች ናቸው፡፡ ከእመቤታችንም የመንፈሳውያን እውነተኛ ምግብ ክርስቶስ ተገኝቷልና፡፡
በዕለተ ረቡዕ ትመሰላለች፡- በዕለተ ረቡዕ “ለይኲኑ ብርሃን በገጸ ሰማይ፤ በሰማይ ብርሃናት ይፈጠሩ” ባለ ጊዜ ለሥጋውያን ምግብ የሚሆኑ ፀሐይ ጨረቃ፣ ከዋክብት ተገኝተዋል፡፡ ከእመቤታችንም የመንፈሳውያን ምግባቸው ጨለማን ያራቀ እውነተኛ ብርሃን ክርስቶስ ተገኝ ቷልና፡፡
በዕለተ ሐሙስ ትመሰላለች፡- በዕለተ ሐሙስ አምላካችን እግዚአብሔር “ለታውጽዕ ባሕር ዘቦ መንፈሰ ሕይወት፤ ባሕር ሕይወት ያለውን ነገር ሁሉ ታስገኝ” ባለ ጊዜ በልባቸው የሚሳቡ፣ በእግራቸው የሚሽከረከሩ፤ በክንፋቸው የሚበሩ በደመ ነፍስ ሕያዋን ሆነው የሚኖሩ ፍጥረታት ተገኝተዋል፡፡ በልባቸው የሚሳቡት የሰብአ ዓለም የዓለማውያን ሰዎች/ በእግራቸው የሚሽከረከሩት ከትሩፋት፣ ወደ ትሩፋት የሚሔዱት የባሕታውያን፣ በክንፋቸው የሚበሩት ተመስጦ ጸጋ ያላቸው የሰማዕታት ምሳሌ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ የተገኙባት ዕለቲቱ የእመቤታችን፣ ውኃው የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ባሕታዊ ሰማዕት መባልና የብሕትውና፣ የሰማዕትነት ዋጋን ማግኘት የተቻለው በእርሷ ነውና በዕለተ ሐሙስ ተመስላለች፡፡
በዕለተ ዓርብ ትመሰላለች፡- በኲረ ፍጥረታት /የፍጥረታት ሁሉ የመጀመሪያው/ አዳም የተገኘው በዕለተ ዓርብ ነው፡፡ ከእመቤታ ችንም ዳግማዊ አዳም የተባለ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኝቷልና፡፡
በዕለተ ቀዳሚት ትመሰላለች፡- ዕለተ ቀዳሚት ዕረፍተ ሥጋን የምታስገኝ የዕረፍት ቀን ናት፡፡ ከእመቤታችንም የመንፈሳውያን ዕረፍታቸው የሆነ ጌታ ተገኝቷልና፡፡ ስለሆነም ቅዱስ ኤፍሬም በሰባቱም ዕለታት ከፋፍሎ በተለያዩ ምስጢራዊ በሆኑ ቃላት እመቤታችንና ልጇን አመስግኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም በታላቅ ትጋትና ምኞት ከፈጣሪ የተገኘውን ይህን ምስጢር አዘል ውዳሴ ለምእመናን ተርጉማ፣ አመስጥራ የምታስተምረው በዚህን ወቅት በሰሙነ ፍልሰታ ነው፡፡ ይህ ሥርዓቷም ምእመኑ ትምህርት ከማግኘቱ ባሻገር ቅዱስ ኤፍሬም ለተሰጠው ቃል ኪዳን ተካፋይ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አመስግኖ በጨረሰ ጊዜ ውዳሴዬን የሚሰማውን የሚያሰማውን አንተ ከገባህበት ውሳጤ መንጦላእት አስገባዋለሁ ብላ ቃል ኪዳን ገብታለታ ለችና፡፡ ስለሆነም ምእመናን የቃል ኪዳኑ ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ የእመቤታችን ውዳሴ ሲተረጎም ሊሰሙ ይገባል፡፡
፭. ቅዳሴ ማርያም፡- ቅዳሴ ማርያም ስለምስጢረ ሥላሴ፣ ስለ ምስጢረ ሥጋዌ የሚያመሰጥር እመቤታችንን በተለያዩ ምሳሌያት እየመሰለ የሚያመሰግኑበት የጸሎት ክፍል ነው፡፡ ደራሲውም አባ ሕርያቆስ ነው፡፡ ይህ ቅዱስ አባት የብሕንሳ ገዳም አስተዳዳሪ ነበር፡፡ ብሕንሳም ሴትና ወንድ ያልተለየባት ገዳም ነበረች፡፡ በዚህች ገዳም የተሾመው አባ ሕርያቆስ ብዙም ትምህርት ስላልነበረው ይንቁ ታል፡፡ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” እንዲሉ ከመሾም በፊት መማር አይቀድምም” እያሉም ይዘብቱበት ነበር፡፡ እርሱ ግን እንደ ጠሉኝ ልጥላቸው ሳይል በፍቅር በትሕትና ይመክራቸው ነበር፡፡ እነርሱ ግን በምን ምክ ንያት እንሻረው እያሉ ይመክሩ ነበር፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን ቀድሰህ አቁርበን እንበለውና አይ ሆንም ካለን በዚህ ምክንያት እንሻረው ብለው መከሩ፡፡ ሞኞቹም እንደ ቅዱስ ኤፍሬም የእመቤታችን ምስጋና እንደ ባሕር አሸዋ እንደ ሰማይ ኮከብ በዝቶልኝ እንደልብስ ለብሼም እንደ ምግብ ተመግቤው የሚል ነበር፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴውን ፈጽሞ ወደፍሬ ቅዳሴው ሲደርስ የትኛውን ሸካራ /ከባድ/ ቅዳሴ ቀድስ እንበለው እያሉ ይመካከሩ ጀመር፡፡ እርሱ ግን ከቅዳሴ ሐዋርያት በቀር የሚያውቀው አልነበረም፡፡ የለመኗትን የማትነሣ፣ የነገሯትን የማትረሣ እመቤታችንም የልቡን መሻት ተመልክታ “ጎስዐ ልብየ ቃለ ሠናየ፥ ልቡናዬ በጎ ነገርን አወጣ›› በማለት ጀምሮ ዛሬም አብን ወልድንና መንፈስ ቅዱስን እናመስግን” እስከ ሚለው ድረስ ሰተት አድርጋ አስደርሳዋለች፡፡ እነርሱም አድንቀው ቅዳሴ ዐሥራ ሦስት ነበርና ዐሥራ አራተኛ አድርገው ጽፈውታል፡፡ ይህም ስለ እመቤታችን በሰፊው የሚያመሰጥር በመሆኑ በሰሙነ ፍልሰታ ይተረጎማል፡፡ ዕለቱን የሚመለከቱ ምስጢራትም በዕለቱ ይተረጎማሉ፡፡ ምሳሌ ነሐሴ ሦስት የበዓታና፣ ነሐሴ ሰባት የፅንሰታ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የበዓታ “ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ልጆች በጨዋታ ያደግሽ አይደለሽም፡፡ በቅድስና፣ በንጽሕና በቤተ መቅደስ ኖርሽ እንጂ” የሚለውን ይመለከቷል፡፡ ነሐሴ ሰባትም “ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀ ነስኪ፤ ድንግል ሆይ፤ ኃጢአት በሆነ ሩካቤ የተፀነስሽ አይደ ለሽም” የሚለውን ይመለከቷል፡፡
፮. ትምህርተ ወንጌል፣ በሰሙነ ፍልሰታ የገጠሪቱን ቤተ ክርስቲያን ሁሉ የሚያጠቃልል ባይሆንም ውዳሴ ማርያም ከተተ ረጎመ በኋላ ለቅዳሴው መዳረሻ መምህራነ ወንጌል ወቅቱን ያገናዘበ ሆኖ በመረጡት ርዕስ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡
፯. ቅዳሴ፡- በሰሙነ ፍልሰታ ቅዳሴ የሚቋረጥበት ዕለት የለም፡፡ የሚቀደሰውም ቅዳሴ ማርያም /ጎስዐ ልብዬ ቃለ ሠናየ/ የሚለው የአባ ሕርያቆስ ድርሰት ነው፡፡ እስከ ነሐሴ ዐሥራ አራት ቀን ድረስ ሌላ ቅዳሴ መቀደስ አይቻልም፡፡ በዚህን ወቅት ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም ምእመናን በተመስጦ ያስቀድሳሉ፡፡ የሚቻላቸው ቆርበው፣ ሌሎችም ጠበል ጠጥተው፣ እምነት ተቀብተው፣ መክፈልት በልተው ወደ ቤታቸው በታላቅ መንፈሳዊ ደስታ ይመለሳሉ፡፡ ከዚህ በፊት ያልነበ ራቸውን መንፈሳዊ ጥንካሬም ገንዘባቸው ያደርጋሉ፡፡
፰. መልክዓ ፍልሰታ፡- በሌ ሎቹ በዓላትና አጽዋማት ከማይ ዘመሩ ዝማሬያት መካከል መልክዓ ፍልሰታ አንዱ ነው፡፡ መልክዓ ፍልሰታ ከዓመት አንድ ጊዜ የሰሙነ ፍልሰታ ብቻ በሊቃውንት፣ በካህናት፣ በዲያቆናት ለእመቤታችን የሚቀርብ ስለ እመቤታችን ረቂቅና ጥልቅ ምስጢርን ያዘለ ውዳሴ ነው፡፡
ለ. በውጪ
9. ጸሎተ ምሕላ፡- ይህ ጸሎት አስቀድሰው ምሳ ከበሉ በኋላ የሚከናወን የሰርክ ጸሎት ነው፡፡ የሰርክ ጸሎት ሁል ጊዜም በቤተ ክርስቲያን ቅጽር እንዲሆን ሥርዓት ቢሆንም በሰሙነ ፍልሰታ ግን ለየት ባለ ሁኔታ ጸሎተ ማርያም፣ ውዳሴ ማርያም እግዚኦታና ሌሎችም የጸሎት ዓይነቶች ይከና ቀጥሎም በመምህራን ትምህርተ ወንጌል ይሰጥና ምእመናኑ በጸሎት ይሰናበታሉ፡፡
0. ሱባኤ፡- ቃሉ የግእዝ ሲሆን ሱባኤ ማለት ሰባት ማለት ነው፡፡ ከያዝነው ርዕሰ ጉዳይ አንጻር ስንመ ለከት ግን የሰው ልጆች ራሳቸውን ከዓለምና ከዓለማውያን ለይተው በጾም በጸሎት ተወስነው እግዚአብሔርን ለማስደሰት፣ ኃጢአትንም ለማስወገድ የልቡናን ግዳጅ ለማስፈጸም የሚደረግ ቅዱስ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም በሰሙነ ፍልሰታ ብዙ ኢትዮጵያውያን ምእመናን የሞቀ የደመቀ ቤታቸውን ትተው፣ የላመ፣ የጣመ ከመመገብ ተቆ ጥበው በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይወድቃሉ፡፡ በዚህም ኀጢአታቸውን፣ በደላቸውን ያስወግዳሉ፣ ከፈጣሪያቸው ጋር ይታረቃሉ፤ የልቦናቸውን መሻት /ፍላጎትም/ ያስፈጽማሉ፡፡ ጸጋን፣ በረከትንም ይጎናጸፋሉ፡፡
ሱባኤ መግባትም ከጥንታውያን ምእመናን ጀምሮ የነበረና ብዙዎቹ የእግዚአብሔር ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር የታረቁበት ብዙ በረከት ያገኙበት ግዳጃቸውንም የፈጸሙበት ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ ዓርባ ቀን ያህል ከሰው ተለይቶ በጾም በጸሎት፣ በሱባኤ ቢጸና ጸወነ ሥጋ ጸወነ ነፍስ የምትሆነው ታቦተ ጽዮንን ከፈጣሪው ተቀበለ /ዘጸ.!4፥!4/፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤልም ለባቢሎን ጠቢባን ያስቸገረውን ንጉሥ ናቡከ ደነጾር አይቶት የነበረውን ሕልም የተረጎመና ሊገደሉ የነበሩ የህልም ተርጓሚዎችን ያዳነው ሱባኤ ገብቶ ፈጣሪውን በመማጸን ነበር /ዳን.2፥18/፡፡ ሐና እና ኢያቄምም የዓለም እመቤት የሆነች ድንግል ማርያምን ያገኙት ሱባኤ በመግባት ነው /ስንክሳር ግንቦት 1/፡፡
ስለሆነም ቤተ ክርስቲያናችን ለሱባኤ ታላቅ ቦታ አላት፡፡ ይሁን እንጂ ሱባኤ ለማንኛውም ሰው የሚፈቀድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ግዳጅ የማስፈጸም ኀይሉ ከባድ እንደሆነ ሁሉ ሥርዓቱና፣ ፈተናውም የዚህን ያህል ከባድ ነውና፡፡ በመሆኑም በሰሙነ ፍልሰታ /ጾመ ማርያም/ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን /በዐውደ ምሕረቱ/ ዙሪያ ሱባኤ የሚይዙ ምእመናን የሚከተለውን ቅድመ ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባል፡፡
ሀ. ንስሐ መግባት፡- የሰው ልጅ ከበደል የሚጸዳበት ጊዜ አለመኖሩን መጻሕፍት በሰፊው ይመሰክራሉ፡፡ “ሰማይኒ ኢኮነ ንጹሐ በቅድሜየ፤ ሰማይም ቢሆን በእኔ ዘንድ ንጹሕ አይደለም” ብሏልና፡፡ ስለሆነም ከጾሙ ከጸሎቱ ከሱባኤው በፊት ከንስሐ አባት ጋር በመነጋገር የእግዚአብሔር ማደሪያ ሰውነታችንን በንስሐ ሳሙናነት ማጽዳት፣ ማጠብ ይገባል፡፡ ያለዚያ ግን ሰውነ ታችንም ይጎዳል ምኞታችንም አይፈጸምም፡፡
ለ. የተጣላነው ካለ መታረቅ፡- ፈጣሪው ይቅር እንዲለው ሱባኤ የሚገባ ክርስቲያን እርሱም ሌላውን ይቅር ይል ዘንድ የግድ ነው፡፡ “ኅድግ ለነ አበሳነ ወጌጋየነ ከመን ሕነኒ ንኅድግ ለዘአበሰለነ” የሚለውን አምላካዊ ቃል አብዝቶ ሊጸልይ ነውና ወደ ሱባኤ የሚገባው /ማቴ. 6፥11-13/፡፡
ሐ. አቅምን ማወቅ፡- ለሥጋ ዊም ሆነ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን አቅምን ማወቅ ጥቅሙ የጎላ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በደላችንን የምናስወግድባቸው፣ ምኞታችንን የምናስፈጽምባቸው ሦስት ደረጃዎች አሉ፡፡ አንደኛ ጾም ነው፡፡ ሁለተኛው ቀኖና ሦስተኛው ሱባኤ ነው፡፡ ጾም፡- ከልዩ ልዩ ነገሮች ሕዋሳትን ማቀብ፣ ወደ ኀጢአት ከሚመሩ ነገሮች መቆጠብ ነው፡፡ ቀኖና በጾም በጸሎት መበርታትና ሰዓት ሲደርስ መመገቡ እንደተጠበቀ ሆኖ የጾም ሰዓት ሲደርስም ቢሆን ከሚበላውም፣ ከሚጠጣውም ቢሆን በትንሹ ቀንኖ/መጥኖ/ መብላት መጠጣት ነው፡፡ ሱባኤ ግን ከሁለቱም ሥርዓቶች ከበድ ያለና ከረቂቃን አጋንንት ጋር ለመዋጋት ዝግጁ መሆንንም የሚጠይቅ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡
ብዙዎቹ በሥርዓተ ቀኖና ራስን ማለማመድ ይቅርና ሰባቱን የአዋጅ አጽዋማት ስንኳን በሥርዓቱ ሳይጾሙ ደረጃውን አልፈው ሂደው ሱባኤ ይይዛሉ፡፡ ቅደም ተከተሉን ጠብቀው ስላልመጡም በቦታ ሲጣሉ፣ አትግፊኝ አትግፉኝ ሲባባሉ፣ ለተለያየ ሐሜት ሲጋለጡ ወዘተ ይስተዋላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሱባኤ በረከት ከማሰጠት ይልቅ መቅሰፍት የሚያስከትል መሆኑን መረዳትና ሰሙነ ፍልሰታን እንደ አቅማችን ማሳለፍ መንፈሳዊ ብልህነት ነው፡፡
ከቁጥር አንድ ጀምረን እስከ ዘጠኝ እንደተመለከትነው ቤተ ክርስቲያናችን በሰሙነ ፍልሰታ ከምንም ጊዜ በላይ በምእመናን ልጆቿ ታጅባ ለሃያ አራት ሰዓት እነዚህ ሁሉ አገልግሎቶች ሥርዓት ባለው መልኩ የሚከናወኑባትና በረከትን ለልጆቿ የምታሰጥበት ወቅት ነው፡፡ ይህን የተረዱ ምእመናንም የበረከቱ ተካፋይ ለመሆን ዙሪያዋን ከበው በመቆም ይማጸናሉ፡፡ “እግትዋ ለጽዮን ወእቀፍዋ፤ ጽዮንን ክበቧት እቀፏትም” የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃልም በዚህን ወቅት ፍጻሜውን ያገኛል /መዝ.86/ ጽዮን የተባለችውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ጽዮን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናትና፡፡
ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ “ወባቲ ለዛቲ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ መላእክት አርአያ ዘበሰማያት ቤተ ክርስቲያንሰ ትትሜሰል በጽርሐ አርያም ዘላዕሉ” ለዚህች ቤተ ክርስቲያን የመላእክት ሥርዓት፣ ሰማያዊ ምሳሌ አላት፤ ስለሆነም ከላይ ባለች በጽርሐ አርያም ትመሰላለች፡፡ በማለት አመስጥሮ እንዳመሰገነ ሁሉ እንደ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ምስጋና አይቋረጥባትም፤ በሮቿም አይዘጉም፡፡ /ኵሎሙ ዘዘወትር፣ ራእ. 21፥24/፡፡ ስለሆነም ይህን ዓይነት ሥርዓት ስለተሰጠን እያመሰገን ከባሕርየ እንስሳ ይልቅ በሰማያዊቷ መቅደስ የሚያገለግሉ ባሕርየ መላእክትን በመከተል በእመቤታችን ጾም የሚገኘውን ክብር፣ ጸጋ ለመጎናጸፍ ያብቃን አሜን፡፡
- ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ ልዩ ዕትም ነሐሴ 2005 ዓ.ም.
Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1310-2013-08-17-09-48-13