በዚህ በምንኖርበት በውጪው ዓለም በወርኃ ኅዳር «የምስጋና ቀን» በሚል ስያሜ ቤተሰብ ተሰባስቦ እየተበላና እየተጠጣ በዓሉ ይከበራል። ዓመቱን በሙሉ በቀን ሃያ አራት ሰዓት ክፍት ሆነው አገልግሎት የሚሰጡ የንግድ ቦታዎች ሳይቀሩ በዚህ ቀን ይዘጋሉ። ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ዓመቱን በሙሉ በምስጋና አጥሮት በእያንዳንዱ ቀን ዓለማትን ለፈጠረ ለእግዚአብሔር ምስጋና እንዲገባ ለዕለቱ ተስማሚ የሆነውን ቃለ እግዚአብሔር በመምረጥ ከሌላው የዓለም ሕዝብ በተለየ ኢትዮጵያውያን በምስጋና እንዲኖሩ የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻችቷል።

ምንም እንኳን ከላይ በመግቢያው ላይ ወርኃ ኅዳር «የምስጋና ቀን» በመባል በአሜሪካ ምድር ስለሚታወቅ ልጆቻችንም ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ በዓል እንዴት አድርገው እንዳከበሩ ስለሚጠየቁና በዚሁ ቀንም ከቤተሰብ ጋር የሚያከብሩት ይኽ በዓል የቤተሰብ በዓል በመሆኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቤተ ክርስቲያናችን ከተቋቋሙት ማኅበራት መካከል የሥላሴ ማኅበር አባላት ይኽን ዝግጅት በኃላፊነት ወስደው በተከታታይ ዓመታት እያከበሩት ይገኛሉ። የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት አጋጣሚዎች በየጊዜው አዲስ በመሆናቸው እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ወጥተው ወደ ቅድስት አገር ሲያመሩ ለተደረገላቸው ነገር ሁሉ ምስጋና እንዲያቀርቡ እንዲህ የሚል ቃል ተነግሯቸዋል፦

አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መልካም ምድር፥ ከሸለቆና ከኮረብታ የሚመነጩ የውኃ ጅረቶችና ፈሳሾች ምንጮችም ወዳሉባት ምድር፥ ስንዴ ገብስም ወይንም በለስም ሮማንም ወይራም ማርም ወደ ሞሉባት ምድር፥ ሳይጎድልህ እንጀራን ወደምትበላባት አንዳችም ወደማታጣባት ምድር፥ ድንጋይዋ ብረት ወደ ሆነ፥ ከተራራዋም መዳብ ወደሚማስባት ምድር ያገባሃል። ትበላማለህ፥ ትጠግብማለህ፥ ስለሰጠህም ስለመልካሚቱ ምድር አምላክህን እግዚአብሔርን ትባርካለህ። ዘዳ ፰፥፯-፲

ከላይ እንደገለጽነው ምስጋና ለሚገባው ለእግዚአብሔር ምስጋና ለመስጠት የርእሰ አድባራት ቅድስት ሥላሴ ልጆች ከጠበቅነው በላይ ብዙ ስለተደረገልንና አምልኮተ እግዚአብሔር ለአንዲት ቀን እንኳን ሳይቋረጥ የእራሳችን የሆነ ቦታ ገዝተንና ሠርተን ከመግባታችን በፊት በኪራይ መልኩ በምንንቀሳቀስበት ጊዜ ሁሉ በየሳምንቱ ቅዳሴ እያስቀደስን ሕፃናት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ተወልደው ሁለተኛ ልጅነትን እያገኙ መኖራቸው ከድንቅ በላይ ድንቅ ነውና ዘወትር እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። ተወልደን ካደግንበት ከቅድስት አገር ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ርቀን ብንገኝም ሃይማኖታችንን በአግባቡ ከመያዝ የሚከለክለን አንዳች ነገር ስለሌለ ጊዜ እንዳመጣው አመራር ከእናት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ተለይቶ መኖርን ባለመፈለጋችን ካህናቱና ሕዝበ ክርስቲያኑ በመንፈስ ቅዱስ አነሣሽነትና በፈቃደ እግዚአብሔር ጥንታዊትና ዘላለማዊት የምትሆን የቤተ ክርስቲያናችንን መንገድ በመከተል እንደ ዶግማውና ቀኖናው በአስተዳደርም አንድ ለመሆን ብዙ ዋጋ በመክፈል ዛሬ ወደ ደረስንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በጊዜ እና በዕውቀት እንድናገለግል እድሉን ለሰጠን ለአምላካችን ምስጋና ለማቅረብ የኅዳር ወርን ለዚሁ አገልግሎት በመመደብ ባለፉ ሦስት ዓመታት እንዳከበርነው በቀጣዩ ዓመታትም ከተተኪ ወጣቶች እና ሕፃናት ጋር በመሆን «አድርገህልናልና ለዘላለም እናመሰግንኻለን» በማለት ባለማቋረጥ ለማክበር ተዘጋጅተናል። አምላካችን እግዚአብሔር በገሐድ ሥራ ሲሠራልንና የጠየቅነውን ሁሉ ሲያደርግልን በዓይናችን በማየታችን ምስክርነታችን ፍጹም እውነተኛ ነውና ብዙዎች እግዚአብሔር ያደረገልንን አይተው «የረዳችሁ አምላካችሁ የታመነ ነው» በማለት ስላዩትና ስለሰሙት ሲናገሩ መስማታችን የዕለት ከዕለት ደስታችን ነው። ባለፈው ወር በነበረው የምስጋና ቀን ላይ ከአትላንታ ቅዱስ ገብርኤል ተጋብዘው የመጡት አባታችን ከቅድስት አገር ኢትዮጵያ መጥተው ያጋጠማቸው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንግዳ በመሆኑ «እንዲህ ያለ አገልግሎት እየሰጠሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያኔን አላሳዝንምና ወደ መጣሁበት ወደ ኢትዮጵያ መልሱኝ» በማለት በቁርጠኝነት ተናግረው ሁኔታዎችን ያስተካከሉ አባት በመሆናቸው የርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም አባላት የወሰድነውን አቋም በመደገፍ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። የከርሞ ሰው ይበለን፤ እግዚአብሔርን በማመስገን እንኑር።

 

አብርሃም ሰሎሞን