፩- የቅዱሳት ሥዕላት ትርጉም፤
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት እና ትውፊት ቅዱሳት ሥዕላት ማለት፤ በአብያተ ክርስቲያናት ግድግዳ፡ በሸራ፡ በብራና፡ በወረቀት እና በመስቀሎች ላይ በቀለም ወይም በጭረት ባለ ሁለት ጎን (two dimensional) ሆነው የሚሠሩ የልዑል እግዚአብሔርን፡ የእመቤታችንን፡ የቅዱሳን መላዕክትን፡ የጻድቃንን እና የሰማዕታትን ማንነት የሚገልጥ መንፈሳዊ ጥበብ ነው። ሥጋዊውን ዓለም ከሚያንጸባርቁ መንፈሳዊ መልዕክት ከሌላቸው ሌሎች ሥዕላት ፈጽመው ስለሚለዩ ቅዱሳን ሥዕላት ይባላሉ።
፪- የቅዱሳት ሥዕላት አመጣጥ፤
፪-፩ በብሉይ ኪዳን
ሥዕል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለያዘው ቦታ መሠረቱ የሁሉ አስገኝ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር አስቀድሞ ለነቢዩ ሙሴ ሥዕለ ኪሩብን በሥርየት መክደኛው ታቦት ላይ እንዲያዘጋጅ ማዘዙ ነው። ለዚህም መሠረት በዘጸ. ም. ፳፭፡ቁ ፳፪ “በዚያም ካንተ ጋር እገናኛለሁ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል በስርየት መክደኛው ላይ ሆኜ አነጋግርሃለሁ” ብሎ መናገሩ ነው። እግዚአብሔርም የተናገረውን የማያስቀር ነውና ሊቀ ነቢያት ሙሴን በሥዕለ ኪሩብ መካከል ሆኖ ድምጹን አሰምቶታል።
፪-፪ በሐዲስ ኪዳን
ከሐዋርያዊ ተልዕኮውና የሕክምና ሞያው በተጨማሪ የሥዕል ጠቢብ የነበረው ቅዱስ ሉቃስም ምስለ ፍቁር ወልዳን (እመቤታችን ከልጇ ከወዳጇ ጋር ሆና) በመሳል ለትውልድ አቆይቶልናል። በተጨማሪም ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ለጢባርዮስ ቄሳር የጌታችንን ሥነ-ስቅለት ሥዕል አዘጋጅቶ ሰጥቶታል።
፫- ቅዱሳት ሥዕላት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነ ፊደል፡ ሥነ ጽሁፍ፡ ዜማ፡ ኪነ ህንፃ… ወዘተ እንዳሏት ሁሉ የራሷ የሆነ የሥነ ሥዕል ጥበብም ያላት ስንዱ እመቤት ናት። ከጥንተ ክርስትና የአክሱማውያን ዘመን ጀምሮ ሥዕል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቦታ እንደነበረው የአርኪዮሎጂ ግኝቶችና የጥንት አብያተ ክርሰቲያናት ፍርስራሾች ያመለክታሉ። በተለይ በዘመነ አክሱም ተሠርተው በከፊል የፈረሱ እና ከመፍረስ የተረፉ እንደ አብርሃ ወአጽብሐ፡ ውቅሮ ቅዱስ ቂርቆስ፡ ደብረ ዳሞ ገዳም፡ መርጡለ ማርያም፡ ወዘተ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት የያዟቸው
ሥዕሎች የዘመኑን የሥዕል ጥበብ አሻራ ያሳያሉ። በተለይ በመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሥዕል ጥበብ ያደገበት ዘመን ነበር። በአሁኑ ወቅት በአብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት የምናገኛቸው ሥዕላት በዚህ ዘመን የተሠሩ ናቸው።
፬- የቅዱሳት ሥዕላት ጥቅም፡
፬-፩ ለሥርዓተ አምልኮ
ቅዱሳት ሥዕላት ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያገናኙ መንፈሳዊ ሀብቶች ናቸው። በሥዕል ፊት ቆሞ መጸለይ፡ ወይንም መስገድ ሥዕሉን አምላክ ማድረግ አይደለም። ነገር ግን የሥዕሉን ባለቤት በሥዕሉ ፊት ሆኖ በመማጸን በረከቱን ለማግኘት የሚፈጸም ሥርዓት ነው። ሥዕሉ ለባለቤቱ መታሰቢያ ነው። “የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው ተብሎ እንደተጻፈ” ምሳ. ፲፡፯ የሥዕሉን ባለቤት አቅርቦ ያሳየናል። ገድሉን፣ ተአምራቱንና ቃል ኪዳኑን ያስታውሰናል። በመንፈስም ድልድይ ሆኖ ከሥዕሉ ባለቤት ያገናኘናል።
ሙሴና አሮን ወደ ደብተራ ኦሪት ገብተው በታቦቱና ሥዕለ ኪሩብ ፊት እየሰገዱ ከእግዚአብሔር ትዕዛዝ ይቀበሉ ነበር ዘኁ. ፲፮፡፵፭
፬-፪ ለትምህርት
ቅዱሳት ሥዕላት ሲሣሉ የሥዕሉን ባለቤት ዐቢይ ገድልና ተአምራት በሚያጎላ መልኩ ነው። ስለሆነም ማንኛውም ምእመን የሥዕሉን ባለቤት መንፈሳዊ ተጋድሎ በቀላሉ እንዲረዳ ያደርገዋል። ለምሳሌ የጻድቁ አባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥዕል ሲሣል ለ22 ዓመታት 8 ጦሮችን ከግራ ከቀኝ ከፊት ከኋላ አስተክለው ሲጸልዩ አንድ እግራቸው በቁመት ብዛት መቆረጡን እንዲሁም ስለ ቅድስናቸው ከተሰጣቸው ስድስት የብርሃን ክንፎች ጋር ተደርጎ ይሣላል። ክህነታቸውን ለመግለጽም የእርፍ መስቀልና ጽና ይዘው ይሣላል። የሥዕሉ ባለቤት እንዲታወቅም በሥዕሉ ላይ አጭር የጽሑፍ መግለጫ ይቀመጣል። ”ዘከመ ጸለየ አቡነ ተክለሃይማኖት” እንዲል። በዚህ ሥዕል ምእመናን የጻድቁን ተጋድሎ ይማሩበታል፤ አርአያም ያደርጉታል።
እንግዲህ ቅዱሳት ሥዕላት ይህን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡን ከሆነ በጥንቃቄ በመያዝ መገልገል እንደሚገባና ዘወትር በጸሎት ሰዓት ከፊት ለፊታችን በማስቀመጥ ልንጸልይ እንደሚገባ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መልዕክቷን ታስተላልፋለች።
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!
በአቶ ፍቃዱ ቸሩ።