ከታሪክ ሳይሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ ምንጭ የተገኘ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ የዘመን አቆጣጠር ያላት ቅድስት አገር ኢትዮጵያ ዛሬ መስከረም ፩/፳፻፱ ዓ.ም. በማለት አዲሱን ዓመት ዘመነ ማቴዎስን ተቀብላዋለች። በመጽሐፈ ሄኖክ ምእራፍ ፳፩፣ ፳፪ እና ፳፬ እንዲሁም በመጽሐፍ ኩፋሌ ምእራፍ ፯ ላይ የዘመኑ አቆጣጠር ዓመትም ስንት ቀናት እንዳሉት በአራት ወቅትም ተክፍሎ እያንዳንዳቸው ፺፩ ቀናት እንዳሏቸው እና የጳጉሜ ቀናትንም በተመለከተ የተጻፈውን መነሻ በማድረግ አሁን የደረስንበት ፳፻፱ ዓ.ም. ትክክለኛው የዘመን ስሌት መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች። ምንም እንኳን በርካታ አገሮች ዛሬ ፳፻፱ ዓ.ም. እንደሆነ በቤተ ክርስቲያን መቁጠሪያቸው ቢናገሩም ብሔራዊ የዘመን መቁጠሪያቸውን መንግሥት በሚቆጥርበት አቆጣጠር 2016 በማለት ይጠቀማሉ። የግብጽ ቤተ ክርስቲያንም ይኽንኑ አቆጣጠር በቤተ ክርስቲያኗ ብትጠቀምበትም አገሪቱ ብሔራዊ የዘመን አቆጣጠር ብሎ የሚከተለው የግሪጎርያንን አቆጣጠር በመሆኑ በአገራቸው 2016 በማለት ይጠቀማሉ። አገራችን ኢትዮጵያ ግን ይኽንን አቆጣጠር ብሔራዊ አቆጣጠርዋ አድርጋ ካለምንም መከፋፈል ፳፻፱ ዓ.ም. በማለት በይፋ ታከብራለች፤ ትቆጥራለች። በአሥራ ሁለቱም ወራቶቿ እኩል ፴ ቀናት ያሏትና ተጨማሪ አሥራ-ሦስተኛ ወርን "ጳጉሜን" በማለት በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ስድስት ቀናት የተቀሩትን ሦስት ዓመታት አምስት ቀናት በማድረግ ዘመናትን የምትቆጥረዋ ኢትዮጵያ የዓመት መጀመርያ ወሯንም መስከረም በማለት ስትጠራ መነሻ ያደረገችው በኦሪት ዘጸአት ምእራፍ ፲፪ እና በኦሪት ዘሌዋውያን ምእራፍ ፳፫ የተጻፈውን በመገንዘብ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠርዋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ያሰኛት አቆጣጠሯ በታሪክና በነገሥታት ላይ መነሻነት የተወሰደ ባለመሆኑ ነው። አይሁድ የመጀመርያ ወር ብለው ከሚቆጥሩበት ከመጋቢት ወር ጀምሮ ብንቆጥር ሰባተኛው ወር መስከረም ላይ መሆኑን ልብ ይሏል።
ኢትዮጵያ በዘመን አቆጣጠርዋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መንገድን የተከተለች ለመሆኗ ከላይ የገለጽናቸው ነጥቦች በቂ ምሳሌዎች ቢሆኑም ዐቢይ ጾምና ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ፤ ደብረዘይት፣ ሆሣዕና፣ ትንሣኤ እና ጰራቅሊጦስ ከእሑድ፤ ስቅለት ከዓርብ፤ ዕርገት ከሐሙስ እንዳይወጣ አድርጎ ቀመር አዘጋጅቶ በአሁኑ ዓይነት መንገድ እንዲከበር ያደረገውን የዲሜጥሮስን ብሕረ ሐሳብ ትቀበላለች።
የኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር እና የአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ነሐሴ ባሉት ጊዜያት የስምንት ዓመታት እንዲሁም ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ባሉት ወራቶች የሰባት ዓመታት ልዩነት እንዳለው የታወቀ ነው። ለምሳሌ ማክሰኞ ነሐሴ ፳፫/፳፻፰ ዓ.ም. ስንል እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር August 30, 2016 ይሆናል። ልዩነቱም የስምንት ዓመታት ልዩነት ነው። መስከረም ፩/፳፻፱ ዓ.ም. ስንል እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር September 12, 2016 ማለታችን ነው። ልዩነቱም ሰባት ዓመታት ይሆናል። ምንም እንኳን አንዳንዶች የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር (ካላንደር) የሰባት ዓመታትና የስምንት ዓመታት ከግሪጎርያኑ አቆጣጠር የተለየው ኢትዮጵያ የክርስቶስን መወለድ የሰማችው ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ ከሰባት ዓመታት በኋላ በመሆኑ "ተወለደ የሚለውን ዜና ከሰማች ጀምሮ አንድ ብላ መቁጠር በመጀመርዋ ነው" ብለው ሲናገሩ ቢሰሙም ይኽ አባባል ግን ፍጹም ተቀባይነት ያለው አይደለም። አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ይወለዳል ብለው በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ እሙን ነው። ሆኖም ግን "እኛ የምንጠብቀው ኢየሱስ ክርስቶስ ለካስ ተወልዷል" ብለው ወደ ማመን ሲመጡ "እኛ ካመንን አንድ ዓመት ሞላን" ይላሉ እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው አሁን እኛ ስንሰማ ነው አይሉም።" ይኽ አነጋገር "ዓመተ ምሕረት አቆጣጠር ያሳሳተችው ኢትዮጵያ ናት" እንደ ማለት ነው። በመሆኑም በወራትም በዓመታትም የዘመን አቆጣጠራችን ልዩነት እንዴት እንደመጣ ከዚህ በታች እንመለከታለን፦
በሀብታቸውና በተሰሚነታቸው አዲስ ዓመት ሊሆን የሚገባው መስከረም ሳይሆን ጥር መሆን አለበት በማለት በአሥራ አንደኛው ምዕተ ዓመት የነበረው የካቶሊኩ ፓፓ ጎርጎርዮስ ሰባተኛ በመወሰኑ ተቀባይነት አግኝቶ ብዙዎች ተከትለውታል። የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ግብፅና ኢትዮጵያ ግን ዓመቱን በመስከረም ማክበራቸውን አልተዉም። እንግዲህ የወራት ልዩነቶቹ በዚህ ዓይነት የተከሰቱ መሆናቸውን ካረጋገጥን የዓመታቱ ልዩነት ደግሞ የመጣው በአቆጣጠር ስህተት መሆኑ ተዘግቧል። አስቀድሞ የአይሁድን ታሪክ የጻፈው ፍላቪየስ ጆሴፈስ በሉቃስ ወንጌል ላይ በምእራፍ ፪ የተጻፈውን የሕዝብ ቆጠራ ጌታችን ከመወለዱ ከሰባት ዓመት በፊት እንደሆነ ዘግቦታል። ባሕረ ሐሳብ በተሰኘው መጽሐፋቸው ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አሁን ባለው በምዕራብውያን አቆጣጠር ጌታ በተወለደበት በአንድ ዓመተ ምሕረት ወይም በአንደኛ ዓመቱ ም ራባውያን ሰባት ዓመት በማለት ይቆጥራሉ ማለት ነው። እንግዲህ ትክክለኛውን ቁጥር ለማግኘት እኛ ሰባት ዓመት መጨመር ሳይገባን እነርሱ ሰባት ዓመት መቀነስ ይኖርባቸዋል።
ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው የሮማ ካቶሊክ ፖፕ ቤኔዲክት “The calculation of the beginning of our calendar—based on the birth of Jesus—was made by Dionysius Exiguus, who made a mistake in his calculations by several years,” (የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት አስመልክቶ የተሰላው ሒሳብ ትክክል እንዳልሆነና ስሌቱ የብዙ ዓመታት ልዩነት አለው ሲሉ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ይፋ አድርገዋል። ሙሉውን ሐሳብ ለመመልከት ከዚህ በታች ባለው ድረ-ገጽ ተጠቀሙ፦ http://www.charismanews.com/world/34714-pope-says-jesus-birth-date-is-wrong
ኢትዮጵያ ፳፻፱ ዓ.ም. ዘመነ ማቴዎስ በማለት አውጃለች። የሒሳብ ስሌቱም ፳፻፱ ዓ.ም. ሲካፈል ለ ፬ (በወንጌላውያን ብዛት) አንድ ቀሪ ስለሚኖረው ነው። ሁለት ቀሪ ሲኖር ዘመነ ማርቆስ፤ ሦስት ቀሪ ሲኖር ዘመነ ሉቃስ፤ ያለ ቀሪ ከተካፈለ ዘመነ ዮሐንስ ይባላል። ለምሳሌ የባለፈው ዓመት ፳፻፰ ለአራት ሲካፈል ያለ ምንም ቀሪ እኩል በመካፈሉ ዘመኑ ዘመነ ዮሐንስ ነበር።
ምንጭ:- መጽሐፍ ቅዱስ፤ ባሕረ ሐሳብ (ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ)፤ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሃይማኖታዊ የሕፃናት አስተዳደግ ሥርዓተ ትምህርት በሦስቱ ሕግጋት አምስቱ አዕማደ ምስጢር የበዓላት ቀኖና ( መምህር አባ ሉቃስ መርጊያ፤ ሰኔ ፲፱፻፺፱)
አብርሃም ሰሎሞን