"መስቀል ኃይላችን ነው፤ መስቀል ጽንአታችን(ጥንካሬአችን)ነው፤ መስቀል ቤዛችን ነው፤ መስቀል የነፍሳችን መድኃኒት ነው፤ አይሁድ ካዱ፣ እኛ ግን አመን፣ ያመነውም በመስቀሉ ኃይል ዳን" በማለት የመስቀልን ኃይልነት፣ ፅንዕነት፣ ቤዛነትና፣ መድኃኒትነት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምራናለች።ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር ያድኅነነ እምፀር" በማለት መስቀል ከሁሉም ነገር በላይ እንደሆነና ከሥጋዊ(ዓለማዊ) ጠላትም ሆነ ከመንፈስ ጠላታችን ከዲያብሎስ ሊያድነን እንደሚችል አስተምሮናል።
በዚህም መሠረት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን ሁሉ ከኃጢአት፣ ከፍዳ፣ ከመርገም፣ ለማዳንና ነፃ ለማውጣት ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በለበሰው ሥጋ ተሰቅሎ ክቡር ደሙን ያፈሰሰበትን ቅዱስ መስቀል እናከብረዋለን፣ እንወደዋለን፣ እናገነዋለን፣ እንሳለመዋለን፣ በመባረክና በማማተብ ረቂቃን አጋንንትን እናርቅበታለን፣ በመታሸት ከደዌ ሥጋ፤ ከደዌ ነፍስ እንፈወስበታለን፣ የሰውነታችንን ልዩ ልዩ ክፍሎችም በመስቀል ቅርጽ በመነቀስና፣ በሌላውም ቦታ ሁሉ በእንጨትና፣ በድንጋይ ቅርጽ የመስቀል ምልክት በማድረግ የክርስትና እምነት ተከታዮችና፣ በመስቀሉ የምናምን መሆናችንን እንገልጽበታለን።
ክርስቲያኖች መስቀልን በዚህ መልኩ የምንሸከመውም የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፍለጋ ለመከተል ነው። ማቴ፥ ፲፣ ፴፰ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከታወቁት ዐበይት በዓላት አንዱ የመስቀል ደመራ በዓል ነው።
የደመራና፣ የመስቀል በዓል መስከረም ፲፮ እና ፲፯ በያመቱ በናፍቆት እየተጠበቀ ለዘመናት ሲከበር የኖረ ያለና የሚኖር ታላቅ መንፈሳዊ በዓል ነው። የመስቀል ደመራ በዓል የሚከበርበትን ምክንያት በአጭሩ ለማስታወስ ከጌታችን ዕርገትና፣ ትንሣኤ በኋላ ለ300 ዓመታት ያህል በአይሁድ ተቀብሮ የቆየው አዳኙ የክርስቶስ መስቀል በንጉሱ በቆስጠንጢኖስ እናት በንግሥት ዕሌኒ አማካይነት በተደረገ ፍለጋ የተገኘበትን ታሪካዊ ዕለት ለማስታወስ ነው። ደመራውም የሚደመረው ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ለማግኘት በእምነት ጽናት ባደረገችው ፍለጋና፣ ከደጋግ አበው በተሰጣት ምልክት ዕጣን በማጤስና፣ ደመራ በማስደመር የእግዚአብሔርን ረድኤት በጸሎት በጠየቀች ጊዜ የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ወጥቶ ተመልሶ ባመለከተው ቦታ ላይ ተቆፍሮ መስቀሉ መገኘቱን ከታሪኩ አኳያ ለማስታወስ ነው።
ከብዙ ፍለጋና ድካም በኋላ የተገኘው ቅዱስ መስቀል ከኃጢአት ጥላ፣ ከጥፋት ጨለማ የወጣንበት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት የነፍሳችን ብርሃን፣ የሕይወታችን መብራት ነው። በክርስቶስ ደም የከበረ መሆኑን ያመነበት ሁሉ ከክርስቶስ…በረከተ ሥጋ፣ በረከተ ነፍስ ያገኝበታል።
በዚህ መልኩ ለመስቀሉ ክብር ስንሰጥና፣ የደመራውን በዓል ስናከብር በመስቀሉ የተደረገው ዕርቅና፣ የተገኘው ሰላም በሁላችን ልብ መገኘት ይኖርበታል። መስቀል የትዕግሥት፣ የዕርቅና የሰላም ምልክት መሆኑን ዘወትር ማሰብ ያስፈልጋል። ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ያገኘችው በእምነት ፅናት፣ በብዙ ፍለጋ፣ ትዕግሥትና፣ ድካም ነው። እኛም ለጸሎታችን መልስ፣ ለፍለጋችን ምልክት እስከምናገኝ በእምነታችን መጽናት ይኖርብናል፤ በእምነት ጽናት የሚደረግ ፍለጋ ሁሉ ውጤት አለው "ለምኑ ይሰጣችኋል፣ ደጅ ምቱ ይከፈትላችኋል፣ ፈልጉ ታገኛላችሁ" የተባለው አምላካዊ ቃል የማይለወጥ ስለሆነ ፍለጋችን ከተግባር ጋር ያለማቋረጥ መቀጠል ይገባዋል።
"የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፤ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው"
፩ኛ ቆሮ፥ ፩፣ ፲፰
ሊ/ብ ቀሲስ ሄኖክ ያሬድ