በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት የተወለደው ዮሐንስ እጅግ አስገራሚ የሆነ ድንቅ ድንቅ ነገር የተከሰተበት አወላለድ በመወለዱ ለቤተሰቡና ለአካባቢው እንግዳ ምሥጢር ነበር። ሕፃኑ እስከሚወለድ ድረስ ዲዳ ትሆናለህ ተብሎ በመልአኩ አንደበት የተነገረለት ካህኑ ዘካርያስ ሕፃኒ ሲወለድ አንደበቱ ተፈትቶ መናገሩ ብቻ ሳይሆን ስለተወለደው ሕፃን የተናገረው ትንቢት ጊዜውን የተለየ ያደርገዋል። ካህኑ ዘካርያስ ስl መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የተናገረው ድንቅ ቃል ከቅዱስ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ይነበባል፦
¨ «ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል። ሕፃኑም አደገ በመንፈስም ጠነከረ፥ ለእስራኤልም እስከ ታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።» (ሉቃ ፩፥ ፸፮-፹)
የቅዱስ ዮሐንስ መንገድ ጠራጊነት በቅዱስ ገብርኤልና በአባቱ በዘካርያስ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ነቢያትም ትንቢት የተነገረለት ነበር፡- መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከና የእግዚአብሔርን ቃሉ በሙላት እየተናገረ በመምጣቱ ብዙዎች ቃሉን እየሰሙ ከእርሱ ዘንድ ይጠመቁ ነበር። በትምህርቱም ፊት ለፊት ተናጋሪ ስለነበር በዚያ ዘመን ነግሦ የነበረው ኄሮድስ የወንድሙን ሚስት አግብቶ ነበርና «የወንድምህን የፊልጶስን ሚስት ማግባት አይገባህም» (ማቴ ፲፬፥፬) እያለ በድፍረት ይገስጸው ነበር። ሄሮድስም የተነገረው ቃል እውነት እንደሆነ ቢረዳም ሥልጣኑን ተጠቅሞ ወደ እስር ቤት አስገባው።
ምንም እንኳን ኄሮድስ ሊገድለው ቢፈልግም ሕዝቡን በመፍራት ሳይገድለው ቀርቶ ወደ ወህኒ ቤት አስወስዶ አሳሰረው። ከእስር ያለፈም ቅጣት ለመቅጣት በመመኘት ሊገድለው ይፈልግ ነበር። ንጉሥ ሄሮድስ አስቀድሞም ሊገድለው ይፈልግ ነበርና ሁኔታው ተመቻችቶለት ልደቱን ባከበረበት ወቅት ወለተ ሄሮድያዳ በዘፈን ስታስደስተው የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት። እርስዋም እንዲሁ ትናደድበትና አጋጣሚ ስትጠብቅለት በነበረችው በእናትዋ ተመክራ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ አለችው። ንጉሡም ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት አዘዘ፤ ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው። ራሱንም በወጭት አምጥተው ለብላቴናይቱ ሰጡአት፥ ወደ እናትዋም ወሰደችው። (ማቴ ፲፬፥፯-፲፩)
ኄሮድስ የከበረች የቅዱስ ዮሐንስን አንገት በትእዛዙ በወህኒ ቤት አስቆርጦ አምጥቶ ለወለተ ሄሮድያዳ ሰጣት። እውነት በመናገርና በመስበክ የሚታወቀውን ታላቁን የእግዚአብሔርን አገልጋይ አንገት ከክቡር ሰውነቱ ለይተው ቢጥሉትም የዮሐንስ አንገት በእግዚአብሔር ድንቅ ተአምር ማስተማርዋን ቀጠለች። የካቲት ፴ ቀን የሚነበበው ስንክሳር እንደሚያስረዳን በኑሯቸው ደሃ በሃይማኖታቸው ግን ሀብታም የሆኑ ሁለት ነጋዴዎች አርባ ፆምን ለመፆም ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ ባደሩበት ቤት ቅዱስ ዮሐንስ በሕልም ተገልጦላቸው አንገቱ ከተቀበረችበት ቦታ ተገኝታለች።
ለብዙ ዘመናት የእግዚአብሔር ክብር እንዳይገለጥ ሰዎች በክፋት እየተነሣሡ እውነትን ሲቀብሩ ኖረዋል። የክብርን ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስን አይሁድ ያሸነፉ መስሏቸው ቢቀብሩት በሦስተኛው ቀን የሙታን በኩር ሆኖ ተነሣ። ጌታችን የተሰቀለበትን ግማደ መስቀል የዓለም ጥራጊ መጣያ አድርገው ቢቀብሩት ዘመን ተቆጥሮለት ወጣ። ይኽን ድንቅ ሥራ በየዘመኑ የሚያሳየን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን።
የመስከረም ሁለት ስንክሳር «በዚያችም ቀን የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ከሄሮድያዳ ከእጆቿ ላይ ወደ አየር ስለ በረረች ታላቅ ድንጋጼ ሆነ። ደግሞም ኄሮድስ ሆይ የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም» እያለች በመጮህ ዘልፋዋለች።
የየካቲት ሠላሳ ስንካሳር ደግሞ እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ጠቅሶ የሚከተለውን ይጨምራል። «ሄሮድስ በአዘዘ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ በእሥር ቤት ሳለ ራሱን በሰይፍ ቆርጠው በጻህል አድርገው ወደ ሄሮድስ አመጡለት። እርሱም ለሄሮድያዳ ልጅ ሰጣት እርሷም ለእናቷ ወስዳ ሰጠች። ይህችም የረከሰች አመንዝራ ሴት ልትዳስሳት በወደደች ጊዜ በወጭቱ ውስጥ ጠጉርዋ ተዘርግቶ ወደ አየር በረረች በአየርም ሆና የወንድምህን ሚሰት ልታገባ አይገባህም እያለች አስራ አምስት ዓመት ኖራ በአረቢያ ምድር አርፋ በዚያ ተቀበረች። ከብዙ ዘመናት በኋላ ያ ቦታ የነጋድያን ማደሪያ ሆነ።
በእግዚአብሔርም ፈቃድ ሁለት አማንያን ነጋዴዎች ወደዚያ ቦታ ደርሰው አደሩ። ቅዱስ ዮሐንስም በህልም ገለጠላቸውና የከበረች ራሱን ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው። እነርሱም አወጡአት። ከእርሳቸውም ጋር ወደ ቤታቸው ወስደው ታላቅ ክብርን አከበሩዋት። ለእግዚአብሔር ምሥጋና ይሁን እኛንም መለኮትን በአጠመቀ በከበረው በቅዱስ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን ይታደገን። ልዩ የሆነች በረከቱም ከእኛ ጋር እስከ ዘላለሙ ትሁን፤ አሜን።