"ወመልአ መንፈስ ቅዱስ ላእለ ኤልሳቤጥ"
…በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት…
ሉቃ. ፩፥፵፩
የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እናት የከበረች ቅድስት ኤልሳቤጥ ትውልዷ ከሌዊ ነገድ ከአሮን ወገን ሲሆን የእናቷ ስም ሶፍያ ነው እርሷም ከሌዊ ነገድ ከአሮን ወገን ለሆነ ለማጣት ልጁ ናት በዝምድና አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የእናቷ እህት ልጅ ናት። ይኸውም ማጣት ሶስት ልጆችን ወልዷልና የታላቂቱም ስም ማርያም ነው፦ እርሷም ወደ ግብፅ በተሰደደች ጊዜ እመቤታችንን ያገለገለች ሰሎሜን ወለደች፤ ሁለተኛዋም ሶፍያ ናት እርሷም የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን እናት ይህቺን ኤልሳቤጥን ወለደች፤ ሥስተኛዋና የታናሺቱም ስም ሐና ነው፦ እርስዋም የከበረች ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምን ወለደቻት በዚህ መሠረት ቅድስት ሰሎሜ፣ ቅድስት ኤልሳቤጥና፣ ቅድስት ድንግል ማርያም የእኅትማማች ልጆች ናቸው።
ቅድስት ኤልሳቤጥ ዕድሜዋ ለአቅመ ሄዋን በደረሰ ጊዜ በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ወገን የበራክዩ ልጅ ለሆነው ለካህኑ ዘካርያስ አጋቧት። የከበረ ቅዱስ ወንጌልም ስለ እነርሱ እንዲህ ብሏል፦"ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ" ሉቃ. ፩፥፮ እርሷም የካህኑ የዘካርያስ ሚስት ናትና ክብሯ ከፍ ያለ ነበር። ይሁን እንጂ "ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም" ሉቃ. ፩፥፯ በዚህም ዘወትር ወደ እግዚአብሔር የሚለምኑና የሚማልዱ ሆኑ፣ አርጅተውም የመውለጃቸው ዘመን በአለፈ ጊዜ ፍፁም መታገሳቸውን የተመለከተውና፣ የዘወትር ጸሎታቸውንና፣ ልመናቸውን የሰማ እግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ዘካርያስ ልኮ ጸሎታቸው፣ ልመናቸው እንደ ተሰማ ስለ ዮሐንስ መወለድና ከእርሱ ስለሚሆነው አስረዳው። ሉቃ. ፩፥ ፰–፲፰
የኤልሳቤጥም ማኅፀን የእውነትና የጽድቅ ማደሪያ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ለዮሐንስ መጥምቅ ንጹሕ የወርቅ ሳጥን አደረጋት። ቅድስት ኤልሳቤጥም በእርጅናዋ ወራት መጥምቁ ዮሐንስን ፀንሳ ወለደችው ከሰዎችም የሚደርስባት ሽሙጥ ተወግዶ እጅግ ደስ አላት ። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በቤተ መቅደስ ለካህኑ ዘካርያስ የነገረውን የልጇን ስም በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ስለአወቀች ስሙ ዮሐንስ ይባል አለች። ዮሐንስ መጥምቅን ከመውለዷ በፊትም ሆነ ከወለደችም በኋላ ሌላ ከመውለድም ሆነ ከመፀነስ የኤልሳቤጥ ማኅፀን የተጠበቀች ሆነች።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ወደ ዘካርያስ ቤት ገብታ ኤልሳቤጥን በተሳለመቻት ጊዜ በኤልሳቤጥ መንፈስ ቅዱስ ሞላባት ህፃኑም በማኅፀኗ ውስጥ ዘለለ እርሷም በታላቅ ቃል ጮኻ እንዲህ አለች "ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሸ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ ቡሩክ ነው፤ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ......ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብጽዕት ናት" ሉቃ...፩፥ ፴፱–፵፮ በማለት በትህትና ተናግራለች።
ከዚህም በኋላ ጌታችንን ተወልዶ አየችው በአምላክነቱም አመነች የሚያምኑበትም በመዳናቸው ደስ አላት ዕድሜዋንም በፈጸመች ጊዜ የሄሮድስ ጭፍሮች ልጇ ዮሐንስ መጥምቅን እንዳይገድሉባት ይዛ በሄደችበት /በተሸሸገችበት/ በረሃ ውስጥ ሳለች በዚህ በየካቲት ወር በ፲፮ተኛው ቀን አረፈች።
ለእግዚአብሔር ምሥጋና ይሁን! እኛንም በቅድስት ኤልሳቤጥ ጸሎት ይማረን!
በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን!
ሊቀ ብርሃናት ቀሲስ ሄኖክ ያሬድ
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር