- Written by አቶ ቤካ መገርሳ
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በዘመነ ሐዲስ ኪዳን ከእግዚአብሔር ተልእኮ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቅ የብሥራት ዜና ይዞ በመጣ ጊዜ የብሥራቱ መደምደሚያ ያደረገው ዓረፍተ ነገር «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና» የሚለውን ነበር። በስድስት ወራት ልዩነት ወደ ሁለት የተለያዩ ቅዱሳን ሰዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደተላከ እንረዳለን፤ በመጀመሪያ ወደ ጻድቁ ዘካርያስ፣ ቀጥሎም ወደ እመቤታችን።
ወደ ሁለቱም የተላከው ለተመሳሳይ የብሥራት ዜና ነው ፤ ለዘካርያስ ዮሐንስ የሚባል ቅዱስ ልጅ እንደሚወልድ እና የጌታን መንገድ እንደሚያሰናዳ ሲገልጽለት ለእመቤታችን ደግሞ ጌታን እንደምትወልድ አብሥሯታል። ሁለቱም ቅዱስ ገብርኤልን በጥርጣሬ መልክ ጥያቄ ጠይቀውታል።
ጻድቁ ዘካርያስ ሽማግሌ መሆኑን ሲያስረዳ እመቤታችን ደግሞ እንዴት ያለወንድ ልጅ መውለድ ይቻላል? በማለት ጠይቃለች። ለተመሳሳይ ብሥራት የተላከው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ግን አመላለሱ በጣም የተለያየ ነበር። "በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ፣ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፣ መናገርም አትችልም" ( ሉቃ ፩ ፤፳) በማለት ለጻድቁ ዘካርያስ በአንድ ግዜ ሲመልስለት ለጌታ እናት ግን መጀመሪያ ከሰላምታው ሁኔታ፣ ቀጥሎ ደግሞ ያለ ተፈጥሮ ህግ እንዴት ሰው ይወለዳል? የሚል ጥያቄም ብታስከትልበትም እንደ ትሁትና ቅን አስተማሪ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ እና ምሥጢረ ሥጋዌ ካስረዳት በኋላ በመጨረሻ ላይ " ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና" በማለት የሐሳቡ መቋጫ አድርጎታል።
- Written by አቶ ዳዊት ጌታቸው
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
“ነዋ ሚካኤል አሐዱ እመላእክት ቀደምት” ትንቢተ ዳንኤል ፲: ፲፫
በዚህ አጭር ሥነ ጽሑፍ ቆይታችን ስለ ኅዳር ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል ታሪክና በተጨማሪም ስለቤተሰባዊ ተአምር ስለተደረገልን እንነጋገራለን። ቅዱስ ሚካኤል የሚያደርገው ተአምር እልፍ አዕላፍ ቢሆንም በዚህ ዕለት ከሚታሰቡት እስራኤል ዘሥጋን ከምድረ ግብጽ እየመራ ማውጣቱን በተጨማሪም በዓለ ሢመቱን አያይዘን በመዘከር እናከብራለን። የእስራኤል ዘሥጋ ታሪክ ወደ ግብጽ መሄድ እንደምን ሆነ ብንል የዘር ሀረጉን ስንመለከት ጥሩ ግንዛቤ ይሰጠናል። አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ ይስሐቅ ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብ ይሁዳንና አሥራ-አንድ ወንድሞቹን ወለደ። አስራ አንደኛው ልጅ ዮሴፍ ይባላል።