- Written by አቶ አብርሃም ሰሎሞን
ኅዳር ፳፬ ቀን ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) ነውና የሰማይን ሥርዓት በምድር ያለማቋረጥ ቅዱስ! ቅዱስ! ቅዱስ! እግዚአብሔር በማለት ለሚያመሰግኑት ካህናት የተጻፈ ሥነ-ግጥም፦
ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ አምላክ ነህ እያሉ፣
መላእክት በሰማይ ያመሰግናሉ።
ግብራቸው ነውና እግዚአብሔርን ጠርተው፣
ቅዱስ ቅዱስ ማለት በምስጋና ቆመው።
- Written by መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ስንታየሁ ደምስ
፪/ ግበሩ እንከ ፍሬ (መልካም ፍሬ አፍሩ ሉቃ፣ ፫፥፰)
ቅዱስ ዮሐንስ ካስተማረው ትምህርት ሁለተኛው መልካም ፍሬ ማፍራት ነው። ከንስሐ ሕይወት ጋር ተያይዞ የሚሄደው ሁለተኛው መልካም ፍሬ ነው። ሰው አንድ ቀን ንስሐ መግባት ይችል ይሆናል፤ መልካም ፍሬ ለማፍራት ግን ረጅም ጉዞን የሚጠይቅ ነው። የንስሐ ሕይወትን መጀመር ቀላል ባይሆንም ግን ደግሞ በመልካም ፍሬ ለማደግና፣ ለመኖር ግን ቀላል የሚባል አይደለምና። እንግዲህ መልካም ፍሬን ለማፍራት በዙሪያው የተሰበሰቡትን እንደ ዕድሜያቸው፣ እንደ ሥራ ጠባያቸው፣ እንደ ሕይወት ልምዳቸው፣ እንደ አኗኗር ዘይቤያቸው የሚያስፈልጋቸውን እንዲያደርጉና ማፍራት እንዲችሉ በደረጃቸው አስተምሯቸዋል።
፪. መልካም ፍሬ ማፍራት ለፈሪሳውያንና፣ ሰዱቃውያን፤
"ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ የእፉኝት ልጆች ከሚመጣው ቁጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ" (ማቴ. ፫፥፯ ፈሪሳውያን ማለት ተመፃዳቂዎች ያለ እኛ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያውቅ የለም፣ ያለ እኛ ለጽድቅና ለቅድስና የተዘጋጀ የለም፤ እያሉ የሚለፍፉ የታይታ ሕይወት ላይ ያንጸባረቀ ኑሮ ይዘው የሚኖሩ የነበሩ ናቸው። ለዚህም ወግ አጥባቂዎች ይሰኛሉ። ምክንያቱም የሙሴን ሕግ እንጠብቃለን የሚሉ ናቸውና በወቅቱ በነበረውም ፖለቲካ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ነበሩና፤ በክህነት ውስጥ ብዙዎች ያገለግሉ ነበር።
ሰዱቃውያን በጣም ሀብታሞች የነበሩ፣ በገንዘብ እና በቁሳዊ ነገር ላይ ብቻ አትኩሮት የነበራቸው ሲሆኑ ደረጃቸውም በክህነት ውስጥ ሳይሆን በአማኝነት ብቻ ነበር። እነዚህ ወደ መጠመቂያው በመጡ ጊዜ ከሚመጣው ቁጣ እንድትድኑ ማን ነገራችሁ። በመመጻደቅ፣ በመተቸት፣ የሙሴን ሕግ እንጠብቃለን ብሎ በቃል በመናገር ብቻ የሚገኝ የጽድቅ መንገድ የለም መልካም ፍሬ በማፍራት እንጂ፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል እናንተም በንስሐ ተመልሳችሁ መልካም ፍሬ ካላፈራችሁ ትቆረጣላችሁ፣ ትጣላላችሁ እያለ አስተምሯቸዋል። ዛሬም አንዳንዶቻችን በእንደዚህ ዓይነት የምንመላለስ እንኖር ይሆናል። ግን በንስሐ ተመልሶ በመልካም ፍሬ መኖር ያስፈልጋል። በሥጋ ፈቃድ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት፣ በኃጢአት ሳይሆን በንስሐ በመመለስ፣ በክፋት ሳይሆን በንጽሕና፣ በቂምና በጥላቻ ሳይሆን በይቅርታ፣ በወንድማማች መዋደድ ይህ ከሆነ መልካም ፍሬ ማፍራት እንችላለን። ገላ፣ ፭፥፲፮
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ የተሰበሰቡ ታናናሽ ባለ ሥልጣናትን ብቻ ሳይሆን በዙፋናቸው፣ በእልፍኛቸው በታላላቅ ግርማ ሞገስና መፈራት ሕዝብ የሚያስተዳድሩትን ነገሥታቱን እና ሹማምንቶችን ሁሉ በግልጽና በድፍረት ሲያስተምር የነበረ ሐዋርያ ነው። የ፬ኛው ክፍል ገዢ የነበረው ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት በማግባቱና ስለሚሠራው ክፉ ሥራ በሕዝብ ፊት ይገስጸው ነበረ:: "የወንድምህን የፊልጶስን ሚስት ልታገባ አይገባህም በማለትና ስላደረገው ሌላ ክፋት ሁሉ ዮሐንስ ስለ ገሰጸው ዮሐንስን በወህኒ አገባው" ሉቃ፣ ፫፤ ፲፱፥፳ ከላይ እንዳየነው ዮሐንስ ስለ እውነት በመመስከሩ የጠበቀው መከበር፣ መወደስ፣ መመስገን፣ መሸለም ሳይሆን መታሰር ነው። እውነት የምታስከፍለው መሥዋዕትነት አለና፤ እውነትን ብቻ መናገር ሳይሆን ስለ እውነት የሚከፈለውንም መሥዋዕትነት ለመቀበል መዘጋጀት ያስፈልጋል።
ዕለቱ ንጉሡ ሄሮድስ የልደት በዓሉን በታላቅ ድምቀት የሚያከብርበት በመሆኑ ብዙዎች ተሰብስበው የንጉሡን ልደት በዓል እያከበሩ ባለበት ሰዓት ወለተ ሄሮድያዳ /የሄሮድያዳ ልጅ/ በንጉሡ ፊት አቀነቀነች /ዘፈነች/። ንጉሡም በዘፈኗ ተመስጦ ውስጥ ሆኖ “የምትይኝን ሁሉ አደርግልሻለሁ የመንግሥቴን እኩሌታም ቢሆን” አለና በቀኙና በግራው ባሉት ባለሥልጣናትና ሹማምንት ፊት የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት። ማቴ፣ ፲፬፥፯ እርሷም ሄዳ እናቷን አማከረቻት። ሄሮድያዳም “ብርና ወርቅ፣ የመንግሥቱስ እኩሌታ ምን ያደርግልናል ክብራችንን እያዋረደ፣ እኔን እያሸማቀቀ፣ ንጉሡን እያዋረደ ያለ ዮሐንስ በወህኒ ነው የእርሱን አንገት ስጠኝ በዪው” አለቻት የሄሮድያዳም ልጅ እናቷ እንዳለቻት ሄዳ ለንጉሡ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በወጭት ስጠኝ” አለችው። እርሱም እያዘነም መሐላውንም ለመጠበቅ የዮሐንስን አንገት በሰይፍ አስቆርጦ በወጪት እንዲያመጡ አዘዘ ጭፍሮቹም ሄደው የዮሐንስን አንገት በወጪት አድርገው ለሄሮድያዳ ልጅ ሰጧት። ይኽም የሆነበት ዕለት መስከረም ፪ ቀን ነው። የዮሐንስንም ሌላውን በድኑን ደቀ መዛሙርቱ ቀበሩት። መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት ዐረፈ።
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የነቢዩን፣ የሐዋርያውን፣ የሰማዕቱን፣ የካህኑን የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዓል በተለያዩ ቀናት ታከብራለች ይኸውም ሰኔ ፴ ቀን ልደቱን፤ መስከረም ፪ ቀን ሰማዕትነት የተቀበለበትን፤ ሚያዝያ ፲፭ ቀን አሥራ አምስት ዓመት ሙሉ ክንፍ አውጥታ እውነት እየመሰከረች የነበረችው ራሱ ያረፈችበት፤ የካቲት ፴ ቀን ራሱ የተገለጸበትን በማሰብ በደማቅ ሁኔታ ስታከብር ከእነዚህ ግን በሁለቱ ማለትም በሰኔ ፴ እና በመስከረም ፪ በልዩ ሁኔታ በዓሉን ታከብራለች። መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በአማላጅነቱ ሁላችንንም ይጠብቀን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣
ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር!
መ/አ/ቀሲስ ስንታየሁ ደምስ