የከበሮ ክፍሎች ትርጉም/ምሥጢር
፩) ሰፊው የከበሮ ጎን ፡- የመለኮት ምሳሌ ሲሆን የጌታችንን የባሕርይ አምላክነት ምሉዕ በኵለሄ መሆኑን እና ስልጣኑም ወሰን ድንበር እንደሌለው ሊያስታውሰን ነው። የአፉን መስፋት ስንመለከት በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ በህልውና ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተስተካከለ ሁሉን የያዘ ሁሉን የሚገዛ መሆኑን ለማሳሰብ ነው።
፪) ጠባቡ የከበሮ ጎን፡- የትስብእት ምሳሌ ነው በመዝሙር ጊዜ እየተቆረቆረ ድምጽ የሚሰጠው ጠባቡ የከበሮ ጎን የወልድ በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ መገለጥን የሚያመለክት ነው። ፍጥረታትን ሁሉ የሚገዛ እሱ በስልጣኑ ሽረት በመለኮቱ ኅልፈት የሌለበት ቢሆንም ሥጋን ተዋሕዶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ተገልጧል።
፫) ከበሮ የሚለብሰው ጨርቅ/ ግምጃ፡- ከበሮ የጌታችን ምሳሌ እንደሆነ ከላይ አይተናል። ከዚህ አንጻር የለበሰው ጨርቅ ደግሞ በዕለተ ዓርብ አይሁድ ጌታችንን ያለበሱት ጨርቅ (ቀይ ከለሜዳ) ምሳሌ ነው። ለመዘባበቻ አይሁድ ሸፍነው “መኑ ጸፍዓከ ወመኑ ኮርአከ ተነበይ ለነ ክርስቶስ፡ በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ ይጠይቁት ነበር።” ሉቃ. ፳፪፡፷፬ እያሉ የሸፈኑበት ግምጃ ምሳሌ ነው።
''ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት'' ማቴ. ፳፮፡፳፰
፬) ከበሮ ማሰሪያ ጠፍር፡- በጌታችን ጀርባ ላይ የታየው የግርፋት ሰንበር ምሳሌ ነው። ጠፍሩን በከበሮው ላይ ስንመለከት በጌታችን ጀርባ ላይ የታየውን ሰንበር እናስታውሳለን። ''እጆቼን እና እግሮቼን ቸነከሩኝ አጥንቶቼ ሁሉ ተቆጠሩ'' መዝ. ፳፩(፳፪)፡፲፮ እንዲል ጌታችን አጥንቱ እስኪቆጠር ጀርባው እስኪቆስልተገርፏልና የዚያ ምሳሌ ነው።
፭) የከበሮው ማንገቻ፡- ከበሮ ስንመታ አንገታችን ላይ የምናስገባው ማንገቻ ጌታችንን አስረው የጎተቱበት ገመድ ምሳሌ ነው። አይሁድ ጌታችንን ወደ ቀራንዮ ሲወስዱት የእጁ መጋፊያና መጋፊያ እስኪገጥም ድረስ በገመድ የእንግርግሪት አስረው ጎትተውታል ማገቻውን ከበሮው ላይ ስናይ ይኽንን ጌታችን የታሰረበትን ገመድ እናስታውሳለን።
፮) በከበሮ ውስጥ የሚደረጉ 3 ወይም 5 ጠጠሮች ፡- ሦስት ጠጠሮች ከሆኑ ምሥጢረ ሥላሴን አምስት ጠጠሮች ከሆኑ አምስቱን አዕማደ ምሥጢራትን ያስረዳል።
የከበሮ አጠቃቀም ምሳሌያዊ ትርጉም/ምሥጢር!
፩) ከበሮ ግራና ቀኝ መመታቱ፡-“ዘበእንቲአሃ ለቤተክርስቲያን ተጸፋእከ በውስተ ዓውድ ከመትቀድሳ“ ያለውን በማስታወስ የግራና የቀኝ ጉንጩ ምሳሌ ነው።
፪) መዘምራን ግራና ቀኝ እያሸበሸቡ ከበሮ መምታታቸው፡- ይህ የሚያሳየዉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐና ቀያፋ፣ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ ያደረገው እንግልት ነው።
፫) ከበሮ መጀመሪያ በርጋታ መመታቱ ከዚያም በፍጥነት መዘዋወሩ፡- ይህ ምሳሌነቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አይሁድ እንደያዙት መጀመሪያ በቀስታ እየዘበቱ እንደመቱት፣ በኋላም ጲላጦስ ተመራምሮ ነፃ ሳያወጣው፣ የሰንበት ቀን ሳይገባብን ኑ እንደብድበው የማለታቸው ምሳሌ ነው ።
፬) በማሕሌት ላይ ከበሮ መሬት ላይ ተቀምጦ መመታቱ፡- ምሳሌነቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሬት ላይ ወድቆ መንገላታቱን ለማሳሰብ ነዉ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን!
በዶ/ር ስሎሞን ፎሌ