ትንሣኤ የሚለው ቃል የተገኘው “ተንሥአ” ከሚለው የግእዝ ግሥ ሲሆን ትርጉሙም ተነሣ ማለት ነው፡፡ ትንሣኤ ሙታን ስንልም የሙታንን መነሣት እና አዲስ ሕይወት ማግኘት ማለት ይሆናል፡፡ የትንሣኤ በኵር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በእርሱ ትንሣኤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋገርን፤ ኃጢአታችንና በደላችን ተደምስሶ አዲስ ሕይወት አገኘን፤ ከሞት በኋላ ሕይወት ከመቃብር በኋላ ትንሣኤ እንዳለ በእውነት ተረዳን። ነቢዩ ኢሳይያስ “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ። በምድር የምትኖሩ ሆይ፥ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፥ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም” (ኢሳ. ፳፮፡፲፱) በማለት ታላቅ መልዕክት አስተላልፎልናል። እኛም አማናዊ እንደሆነ ሁሉ ትንሣኤን እንደሚሰጠን አምነን ለተሰጠን ሕይወትና ታላቅ ተስፋ እንዘምር። በትንሣኤው የሰጠንን ሕይወት ጠብቀን፤ በሃይማኖት ጸንተን ለክብር ትንሣኤ ከሚነሡት ጋር ዕድልና ፈንታ አግኝተን በዘላለም መንግሥት ከቅዱሳኑ ጋር ክብሩን ለመውረስ ያብቃን። አሜን!
በመልአከ አርያም ቆሞስ አባ ኃይለሚካኤል ሙላት (የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ)