የተወደዳችሁ የርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞች እና እኅቶች እንኳን በቤተ ክርስቲያናችን በታላቅ ድምቀት ለሚከበረውና ከታላላቅ በዓላትም አንዱ ለሆነው ለበዓለ ሆሣዕና አደረሳችሁ። የዚህ ታላቅ በዓል ምንነት ታሪክ በአራቱ ወንጌላውያን ተጽፎ ይገኛል። ይኽም በዓል የሚከበረው ጌታችን በአህያይቱና በውርንጭላዋ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ዕለት በማሰብ ነው። (ማቴ. ፳፩፡፩-፲፯) ጌታችን በእንዲህ ያለው ሁኔታ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱም በነቢዩ በዘካርያስ የተጻፈው ትንቢት እንዲፈጸም ነው። (ዘካ.፱፡፱)። ከወንጌሉ ታሪክ እንደምናነበውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን "በፊታችሁ ወዳለች ከተማ ሄዳችሁ የታሰረች አህያ ከነውርንጭላዋ ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ ማንም ስለዚህ ነገር ቢጠይቃችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ።" ብሎ ልኳቸዋል።
በአጭሩ ከታሪኩ የምንማረው አህያይቱ የተባለችው ኦሪት፤ ውርንጭላዋ ደግሞ ወንጌል ናት። በሌላ በኩል የአህያይቱና የውርንጭላዋ ምሳሌ የእስራኤል እና የአሕዛብ ምሳሌ ሲሆን ምሳሌነቱም የተለያዩትን ሁለቱን ወገኖች አንድ ለማድረግ የመጣ መሆኑን ለማስረዳት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ...ለተቀበሉት ሁሉ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው (ዮሐ. ፩፡፲፪) እንዳለ ጌታም “ፈትታችሁ አምጡልኝ” ማለቱ ሰው ሁሉ ከኃጢአት እስራት የሚፈታበት ጊዜ መድረሱን ሲያስረዳ ነው። ከዚህ በተጨማሪም “ፈትታችሁ አምጡልኝ” ማለቱ የሐዋርያትን ሥልጣነ ክህነትን ያሳያል። ለሐዋርያት የማሰርና የመፍታት ሥልጣን ሰጣቸው ሲል ሥልጣኑ በሐዋርያት እግር የተተኩ ጳጳሳትንና ቀሳውስትን ሁሉ ያጠቃልላል። የተወደዳችሁ ክርስቲያኖች፦ ልንረዳውና ልናጤነው የሚገባ የአምላካችንን ትህትናና ፍቅር ነው። እራሱን ዝቅ አድርጎ በአህያ ላይ የተቀመጠው የሰውን ልጅ ለማክበርና ለመቀደስ ነው። እኛ የእርሱ እውነተኛ ልጆቹ ነን ብለን ደፍረን ልንመሰክር የምንችለው ንስሐ ገብተን ኃጢአታችንን ተናዝዘን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ስንቀበል ነው።
ሌላው ላሳስባችሁ የምፈልገው ይኽች "ጽርሐ አርያም" የተሰኘችው ጋዜጣ የቤተሰብ መልእክት የያዘች፣ ሁለገብ የሆነችና የሁሉንም ሕይወት የምትዳስስ መስተዋት መሆኗን እንድታውቁ ነው። ሁላችን መልዕክቱን አንብበን እንድንጠቀም የልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ይሁን።
በዓሉን የበረከት የረድኤት በዓል ያድርግልን፤ ሳምንቱን በሰላም በጤና አሳልፎ ብርሃነ ትንሣኤውን ያሳየን አሜን !!!
መልአከ አርያም ቆሞስ አባ ኃይለሚካኤል ሙላት
እንኳን ለበዓለ ሆሣዕና አደረሳችሁ።