ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ኃላፊና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በዘንድሮው በ፳፻፱ ዓ.ም. የመስቀል ደመራ አከባበር በዓል ተገኝተው «በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር» ከሚለው ዮሐንስ ወንጌል ፲፱፣፳፭ ኃይለ ቃል ተነሥተው ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል። መስቀል የክርስትና ዓርማ ሰለመሆኑ እና በሕይወትም ይሁን በሞት ለክርስትናችን ምልክት ስለመሆኑ አስተምረው ልክ እንደ እመቤታችን በጭንቅ ቀን ሳይቀር ከመስቀሉ ስር መጥፋት እንደማይገባም በሰፊ ምሳሌ አስተምረዋል። በተለይ በአሁኑ ሰዓት አገራችን ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና አሳልፎ ፍጹም ሰላምን ለማግኘት ከመስቀሉ ሥር ሆኖ ማልቀስ ያስፈልጋል፤ መከራዎች ሁሉ የሚመጡት ከመስቀሉ ስንርቅ ነውና ብለዋል። መቆሚያችን ጠፍቶን ሌላ መስቀል አጠገብ ስንቆም ነው ችግሮች የበለጠ የሚወሳሰቡት። «ሊያገለግለኝ የሚወድ ጨካኝ እና ቆራጥ ሆኖ ይከተለኝ» እንዳለ ጨክኖ መከተል ያስፈልጋል። ፈሪ ሰው የመስቀል በዓል አያከብርም። ምክንያቱም መስቀል ውስጡ ያለው ታሪክ ለፈሪ ሰው አይመችምና። የመስቀል ሕይወት መከራ፣ ጅራፍ ፣ ግንድ መሸከም፣ ሐሞት መጠጣት፣ ልብስን መገፈፍ እና መደብደብ ስለሆነ ፈሪ ሰው መስቀሉ አጠገብ አይኖርም። በዕለተ መስቀል እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ቅዱስ ዮሐንስ እና ከተወሰኑ እናቶች ሲቀሩ ሁሉም ተበተኑ ዓይናቸው የበራው፣ ጆሯቸው የሰማው፣ ኅብስት አበርክቶ ያበላቸው ሁሉም ተበተነ። እኛም መስቀል የምናከብረው ይህንን ሁሉ ካመንን በኋላ ነው አለበለዚያማ «ይቤሎሙ ኢየሱስ» ሊሆን ነው ማለት ነው።
መስቀል ማለት ጥሪ ማለት ነው - የአገልግሎት ጥሪ። ለዚህ አገልግሎትም መመዘኛውን ማሟላት ግድ ነው - ይኸውም “ሊያገለግለኝ የሚወድ ጨካኝ ይሁን የሚሞትበትንም መስቀል ይሸከም” ይላል። መስቀልን መሸከም ስንልም ራስን መካድ፣ ራስን መስጠት፣ ራስን መጥላት ማለት ነው። ራስን መካድ ማለት ለሌላው መቆም ማለት ነው። ለሌላው መሞት እንጂ ሌላውን መግደል አይደለም። መከራ ሲመጣ እስከ መጨረሻው መጽናት ማለት ነው። «እሞታለሁ!» ያለው ጴጥሮስ ሳይቀር እዚያች ቀራንዮ ሲደርስ ያልቻለበት ዓይነት ፈተና ሲደቀን መጽናት ማለት ነው፣ ዕለተ አርብ ክፉ ናትና። የተከተሉና የጸኑት ግን «በመስቀሉ አጠገብ ቆመው ነበር» ተባለላቸው። የጸና ከመስቀሉ አጠገብ ይገኛልና። በዚህ መስቀል ስር ከታየ ጽናትም በኋላ ነበር «እነሆ ልጅሽ - እነኋት እናትህ» የሚለው የመስቀል ቃል የተፈጸመው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንወዳታለን የምንል እኛ ኦርቶክሳዊያን ማስተዋል ያለብን ፈተና በጸናበት በዕለተ አርብ እመቤታችን ከምን አጠገብ ነው የተገኘች ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባናል። ሁሉ ሲበተን፣ ሁሉ ሲሸሽ እና ሁሉ ሲርቅ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መስቀሉ አጠገብ ተገኘች! ለቅዱሳንም ክብርን የምንሰጠው ኑሯቸውን ሕይወታቸው መስቀሉ ስር ስለሆነ ነው። አሁን አሁን እኛ የተጎዳነው በዓሉን እንደ ባሕል በምግቡና በልብሱ ብቻ እያከበርን ከመስቀሉ ርቀን በመኖራችን ነው። ቅዱስ ጳውሎስ «መስቀሉን በሥጋዬ እሸከማለሁ» እንዳለ በባሕሩ በየብሱ መከራን እንደተቀበለ ሁሉ በሕይወታችሁ የሚደርስ ፈተና መገስ፣ ትዳር እንዳይፈርስ በትዳር ውስጥ መከራ መቀበል ይህ መስቀልን መሸከም ነው።
በመስቀል ላይ በፈሰሰው ደሙ ሰላምን አደረገ፣ በሰማይም በምድርም ላሉ» እንዳለ የፍጹም ሰላም ምንጩ እና ምልክቱ መስቀል ብቻ እንደሆነ ልናስተውል ይገባናል። ሰላም የሚገኘው እና የተገኘው በዚህ እንደሆነ እየታወቀ ዛሬ ዓለም ራሱ ያጣውን ሰላም ለእኛ እንዲሰጠን ያለ ቦታው ሰላምን ፍለጋ እንባዝናለን። ፍጹም ሰላም ከእግዚአብሔር ብቻ ነው። ሰላም ከባለሥልጣኖች ፈጽማ አትገኝም። ክርስቲያን ሆኖ የሰላሙን ባለቤት እግዚአብሔርን መጠየቅ ሲገባ ሰላም ያጣውን ዓለም ሰላም ይሰጠናል ብለን ሰላምን ያለቦታዋ ስንሻት እንታያለን። ሰላም ማለት ከመስቀሉ አጠገብ መቆም ማለት ነው። «እግዚአብሔርን እወዳለሁ የሚል ባልንጀራውን ግን የሚጠላ እርሱ ውሸታም ነው» እንዳለ የምናየውን ወንድማችንን ሳንወድ የማናየውን እግዚአብሔርን እወዳለሁ ማለት ውሸታምነት እንደሆነ የጻፈልን በመጨረሻዋ በፈተናዋ ቀን በዕለተ አርብ መስቀሉ አጠገብ የተገኘው የፍቅር እና የሰላም ትርጉሙ የገባው ቅዱስ ዮሐንስ ነው። እኛ ግን ዛሬ ሰዎችን እየሰቀልን መስቀልን እናክብር እንላለን።
የአንድ የአዳም እና የሔዋን ዘር መሆናችንን ዘንግተን እኛ «ኑ እንውረድ ቋንቋቸውንም እንደባልቀው» በተባለለትና የኃጢአት ውጤት በሆነው በቋንቋ ተለያይተን እየተገዳደልን እንገኛለን። የክርስቲያን ቋንቋ በሆነ በእግዚአብሔር ፍቅር፣ በመስቀሉ ፍቅር ፣ በጾም እና ወንድምን እና እኅትን በመውደድ ልንኖር ይገባናል። ፍቅር ከሌለ ተራራ የሚያፈልስ፣ ዛፍ የሚነቅል ሃይማኖት ቢኖረን ከንቱ ነውና።
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በማጠቃለያቸውም ቅዱሳን ሐዋርያት «ሁሉን ትተን ተከተልንህ» እንዳሉ ሁሉ ርስት መንግሥተ ሰማያት የምትወረሰው ሁሉን ትቶ ከመስቀሉ ስር በመገኘት ነው። ልጅ እናቷ አጠገብ ሆና፣ ሐብታም ገንዘቡ አጠገብ ሆኖ፣ ባለሥልጣንም ወንበሩ አጠገብ ሆኖ የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ አይቻለውም። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ሁሉን ጥለን ተከተልንህ” እንዳለ ሁሉን ጥለን መስቀሉ ሥር ስንገኝ ብቻ ነው የመንግሥቱ ወራሾች የምንሆነውና ሁላችንንም ይህንን ተገንዝበን የሰላም አርማ የሆነውን የመስቀልን በዓል ስናከብር ከምን አጠገብ እንደቆምን በማስተዋል ፍጹም ሰላምን ወደሚያድለው ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር በፍጹም ልባችን ልንመለስ ይገባናል ብለዋል።
የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ለብፁዕ አባታችን ረዥም የአገልግሎት ዘመን ከሙሉ ጤንነት ጋር እንዲሰጥልን እንመኛለን።
ሠናይ ምንውየለት (ዘጋቢ)