በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲመሠረት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ለእግዚአብሔር ቤት ታምነውና በቅንነት ተነሣሥተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ በማድረግ በጊዜያቸው፣ በጉልበታቸው፣ በገንዘባቸውና በእውቀታቸው ሙሉ መሥዋዕት በመክፈል በየዕለቱ ሊታወስ የሚገባውን አኩሪ የሃይማኖት ድል ተጎናጽፈዋል። ካህናትና ዲያቆናት፣ ሰበካ ጉባኤና ሰንበት ትምህርት ቤት፣ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም ሕፃናት የቅድስት ሥላሴን ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት የሚያስፈልገውን ሁሉ ማድረጋቸው ለእኛ በውስጡ ላለነው ብቻ ሳይሆን ይኽንን ሁኔታ ለሚከታተሉ ሁሉ አስገራሚ ነበር። ጻድቅ ኢዮብ መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፤ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ፤ (ኢዮብ ፵፪፥፭) እንዳለ እኛም እግዚአብሔርን ፊት ለፊት በሥራው ስላየነው የዘመኑ ዕድለኞች እና ባለ ታሪኮች እንደሆንን ይሰማናል። ይኽ የእግዚአብሔርን የማዳን ክንድ ያየ ሕዝብ ቤቱን ከመሥራት ባሻገር የቤተ ክርስቲያኑም ዕዳ በአጭር ጊዜ ተከፍሎ እንዲያልቅ እያደረገ ያለው መነሣሣት እጅግ ያስደስታል። በጽዳት፣ በመስተንግዶ፣ በማዕድ ቤት አገልግሎት፣ በንግሥ በዓላት እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ አባላት በየመስኩ እያደረጉት ያለው ጥረት እጅግ አስገራሚ ነው።
እያንዳንዱን አገልግሎት እያነሣን በትንታኔ ብናቀርበው ማለቂያ ስለማይኖረው ዛሬ በዚህ መልእክት ልናስተላልፍ የምንወደው ነገር ቢኖር መላው የርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አባላት በተለያዩ ጊዜያት በሚኒሶታ ስቴድየም በመገኘት በቀን ለስምንት ሰዓትና አንዳንዴም ከዚያ በላይ በመሥራት ለዕዳ ማቃለያ የሚሆነውን ገንዘብ በሙሉ ፍላጎት በመሥራት የማሰባሰባቸውን ጉዳይ ነው። በጊዜያቸውና በጉልበታቸው ከማገልገላቸው ባሻገር ቦታው የሚያስፈልገውን የአለባበስ ሁኔታ ለማስተካከል ከኪሳቸው ገንዘብ በማውጣት የመለያ ልብስና ጫማ በመግዛት በፍጹም ልባቸው ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት መነሣታቸውን ለማመስገን ምን ዓይነት ቋንቋ ብንጠቀም ይበቃን ይሆን? ከስቴቴድየሙ ሥራ በኋላ በነጋታው ደግሞ የራሳቸውን ሥራ ለመሥራት ጊዜ እንዳይመሽባቸው አባላት ትራንስፖርት በማዘጋጀት ሠራተኞቹን በማመላለስ እየከፈሉት ያሉት አስተዋጽዖ እጅጉን አበረታች ነው። እንዲህ ያለው መተጋገዝ አባላቱን እርስበርስ እንዲዋደዱና እንዲከባበሩ ከማድረጉ በላይ ለአንድ አላማ በእውነተኛው የክርስቶስ ፍቅር መቆማቸውን ያረጋግጣል።
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከአንድ መቶ ሺህ ዶላር በላይ አሰባስቦ ለቤተ ክርስቲያን ከማስገባት በላይ ምን የሚያስደስት ነገር ይገኛል? አሁንም አባላት እንዲህ ያለው አገልግሎት በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ የሚያሰጥ መሆኑን አምናችሁ ዛሬም እንደ ትናንት ነገም እንደ ዛሬ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እራሳችሁን በማዘጋጀት የጊዜ መሥዋዕት እንድትከፍሉ እጠይቃችኋለሁ። ዕድሜያቸው አሥራ ስድስት ዓመት የሞላቸው ታዳጊ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ጋር በመሆን ለአንድ አላማ ተነሣሥተው አብረው ሲሠሩ ማየት ነገ የእግዚአብሔርን መንግሥት አብረው ለመውረስ መዛጋጀታቸውን ያሳያል።
መልአከ አርያም ቆሞስ አባ ኃይለሚካኤል
የደብሩ አስተዳዳሪ