ትንሣኤ ማለት ምን ማለት ነው? ትንሣኤ ማለት ነፍስና ሥጋ ተለያይተው ከኖሩ በኋላ ሁለተኛ ተዋሕደው መነሣት ማለት ነው። ትንሣኤ ለምን ሆነ? ሰው የተፈጠረው ነፍስና ሥጋው  ሳይለያዩ  በሕይወት ለመኖር እንጂ ለሞት አልነበረም፤ እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና። ኗሪ ይሆን ዘንድ ፍጥረትን ፈጥሮአልና የሰዎች ጥፋት ደስ አያሰኘውም። መፈጠራችን ለድኅነት ነውና ሕይወት የማታልፍ ስለሆነች ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "እግዚአብሔር ለሞት አላደረገነምና ለሕይወት እንጂ ፩ተሰ ፭፥፱ ይለናል።

ሰው ግን ኃጢአትን በመሥራቱ ማለት የፈጣሪውን ትዕዛዝ በመተላለፉ በራሱ ላይ ሞትን አመጣ፤ ሞት ከእግዚአብሔር ተፈረደበት። በአንድ ሰው ምክንያት ኃጢአትን ወደ ዓለም እንደገባ በኃጢአትም ሞት ገባ እንዲሁም በሰው ላይ ሞት አለፈ ሁሉ በድሏልና። ሮሜ ፭፥፪

ለመቃብርም በዚህ ዓለም ግዛት አልነበረውም።  እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎች ግን በቃል ጠሩት ባልንጀራም አደረጉት በዚህም ጠፉ። መጽሐፈ ጥበብ ፩፥፲፫ ኃጢአተኛው ሰው እንደ አጋንንት በድሎ አልቀረም። የፈጣሪውን ትዕዛዝ በማፍረሱ ተጸጸተና ማረኝ ሲል ፈጣሪውንም ለመነው፤ ፈጣሪውም ወልደ እግዚአብሔር ሰው ሆነለት። ሰው ኃጢአትን ሠርቶ የተፈረደበትንም ሞት ተቀብሎ (ሞቶ) ሰውን ከኃጢአቱ ፍርድ አዳነው። ሞትን አጥፍቶ ሕይወትን መለሰለት። ስለዚህ በተፈጠረበት በጥንት ሕይወቱ ለመኖር ለሰው ትንሣኤ ሆነለት (ተሰጠው)። ትንሣኤ ቀደም ብሎ በነቢያት ታውቆ ስለነበር ስለ ትንሣኤ የተናገሩት ነቢያት ብዙዎች ናቸው ። 

ከብዙዎችም ነቢያት የጥቂቶቹን ቃል ስንጠቀስ ከምዕራፍና ቁጥራቸው ጋር በዚህ መስመር በተጠቀሱት መጻሕፍት ቀጥሎ ያለውን ቃል እናገኛለን።  መዝ ፻፬፥፴ ኢሳ ፳፮፥፲፱  ዳን ፲፪፥፪ እስትንፋስን ትልካለህ ይፈጠራሉም፤ የምድሪቱንም ፊት ታድሳለህ። ሙታንም ሕያዋን ይሆናሉ፣ ሬሶችም ይነሣሉ። በመሬትም  የምትኖሩ ተነሡ አመስግኑ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና። ምድርም ሙታንን ታወጣለች በምድርም መሬትም ያንቀላፉ ብዙ ሰዎች  ይነቃሉ እኩሌቶች ወደዘለዓለም ሕይወት ሌሎችም ወደ ስድብና ወደዘላለም ኃፍረት። ከነቢያትም ቃል በላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ አታድንቁ በመቃብር ያሉት ሁሉ ቃሉን የሚሰሙበት ግዜ ትመጣለችና ቃሉንም ሰምተው መልካም የሠሩ ወደ ሕይወት ትንሣኤ ይወጣሉ፤ ክፉም የሠሩ ወደ ፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ ሲል ትንሣኤ ሙታን እንዳለ አስረድቷል። ዮሐ ፳፰፥፳፱

ትንሣኤም ለሰው ዘር ሁሉ ነው ማለት ለጻድቃንም ለኃጥአንም ሁሉ ነው ። ትንሣኤ ሙታን መቼ ነው? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ዓለምን ለማሳለፍ ወደ ደብረ ጽዮን ይመጣል ራዕ ፲፬፥፩ ሲመጣም ቀድሞ በዘመነ ሥጋዌው መጥቶ ሳለ በትህትና ይታይ እንደነበረ አይደለም፤ መላእክቱን አስከትሎ በግርማ መንግሥቱ  (በጌትነት ክብሩ)  በገሐድ ተገልጦ ይመጣል ማቴ ፲፮፥፳፯። የሙታን ትንሣኤ ጌታችን በሚመጣበት ጊዜ ነው። ትንሣኤ ሙታን እንደምን ነው? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመጣ መላዕክትን  የመለከት ድምፅ እንዲያሰሙ ያዛቸዋል። መላእክት ሦስት ግዜ የመለከትን ድምፅ ያሰማሉ ።  

የመጀመሪያው የመለከት ድምፅ በተሰማ ግዜ የዱር አውሬ፣ የባሕር አዞ ጉማሬ የበላው፣ ባሕር ያሰጠመው ፣ በእሳት የተቃጠለው ፣ በመቃብር የተቀበረው ሁሉ ሥጋ ራሱ ከወደቀበት ይሰበሰባል። ሁለተኛው የመለከት ድምፅ በተሰማ ጊዜ የተሰበሰበው የሰው ሥጋ ከራሱ ጀምሮ ይያያዝና ምሉዕ አካል ይሆናል። ሦስተኛው የመለከት ድምፅ በተሰማ ጊዜ ነፍስ ካለችበት መጥታ ተዋሕዳው ሕያው ሆኖ ፈጥኖ ይነሣል። ፩ቆር ፲፭፤ ፶፪ የመለከት ድምፅ የተባለው ምሳሌ ነው። እውነቱ ግን የጌታ ትዕዛዝ ነው። የምድር ንጉሥ ክተት ሲል ነጋሪት ያስጎስማል፣ መለከት ያስነፋል። ይህን ግዜ ሠራዊቱ ሁሉ በአንድ ጊዜ ይከታል።

የጌታም ትዕዛዝ ሁሉን የሚሰበስብ ስለሆነ በመለከት ድምፅ ተመስሏል። ትዕዛዙም «ንቃሕ መዋቲ ዘትነውም»  ማለትም «የሞት እንቅልፍ ያንቀላፋህ ሟች ሁሉ ንቃ፤ ተነሣ» የሚል ነው። ይህንን ትዕዛዝ የሚያሰማው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነው። ይህን ሲነግረን እርሱ ጌታ በዕልልታ በመላዕክት አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔር መለከት ከሰማይ ይወርዳል በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአንደኛ ተሰሎንቄ መልእክቱ በምእራፍ አራት ቁጥር አሥራ ስድስት ላይ ይነግረናል።  የመለከት ድምፅ በተሰማ ግዜ ይነሣል የተባለው የሞት እንቅልፍ ያንቀላፋህ ሟች ተነሣ የሚል ትዕዛዝ በተነገረ ግዜ ፈጥኖ ይነሣል ማለት ነው። ከሞት ድነን ስንነሣም በጎም ሆነ ክፉ ዛሬ ሰውረን የሠራነው ያን ጊዜ  ይገለጣል፤ ገልጸን የሠራነው ይነገራል።

¨ ያን ጊዜ መላእክት ኃጥአንን ከፃድቃን ይለዩአቸዋል ማቴ ፲፫፥፵፱

¨ ያን ጊዜ ኃጥአን ጠቁረው ይታያሉ፤ ፃድቃን እንደ ፀሐይ በርተው ይታያሉ ማቴ  ፲፫፥፵፪

¨ ያን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓርብ ዕለት በመስቅለ እንደተሰቀለ  እጁንና እግሩን እንደተቸነከረ ሆኖ ይታያል። ስለምን ? ቢባል «ለእናንተ ስል ይህን መከራ ተቀበልኩ ብሎ ፍቅሩን ለሰው ለማስታወስ፤ ላድናችሁ ብመጣ የሰቀላችሁኝ፣ የዘበታችሁብኝ እኔ ነኝ» ብሎ የሰቀሉትን፣ ሐዋርያት መምሕራን ተሰቀለ፣ ሞቶ፣ ዓለምን አዳነ ብለው ቢያስተምሯችሁ «አናምንም አንቀበልም» አላችሁኝ እኔ ነኝ ብሎ የኋላ ከሃድያንን ለመውቀስ ነው።

 

እንዲህ ሆኖ ባዩትም ጊዜ አስቀድመው የሰቀሉትና በችንካር የወጉት ያለቅሳሉ ራእ ፩፥፯

¨ ያን ጊዜ ፃድቃን በበጎ ምግባራቸው ይመሰገናሉ ማቴ ፳፭ ፤፵፩ ያን ግዜም  ኃጥአን  ያለቅሳሉ ማቴ ፳፬፥፴

¨ ያን ጊዜም ሁሉም እንደ ሥራው ተገቢውን ይቀበላል ማለት ፃድቃን የበጎ ምግባራቸውን ዋጋ ኃጥአንም የክፉ ምግባራቸውን ፍርድ ይቀበላሉ። ፪ቆሮ ፭፥፲፣ ሮሜ ፪፥፲፮ ፣ራእ ፳፥፲፪ ያን ግዜ ኃጥአን ወደ ዘላለም ስቃይ ይሄዳሉ፤ ፃድቃንም  ወደዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ። ማቴ ፳፭፥፵፮ ከዚህ በኋላም ሰማይና ምድር ያልፋሉ ፣ መላዕክትና ሰዎች ይቀራሉ ማቴ ፳፬፥፴፭ ከዚህም በኋላ ኃጥአንና አጋንንት ከአለቃቸው ከዲያቢሎስ ጋር በስቃይና በዋይታ በገሃነም  ይኖራሉ።

መላእክትና ፃድቃንም ከጌታቻው ከክርስቶስ በዕረፍትና በደስታ በመንግሥተ ሰማይ ይኖራሉ። ጌታችን የሚመጣው መቼ ነው?  ጌታ የሚመጣበት ዘመኑና ጊዜው አይታወቅም ማቴ ፳፬፥፴፯ ዕለቲቱ ግን ዓለም የተፈጠረባት እሑድ እኩለ ሌሊት ናት ሉቃ ፩፥፴፩ማቴ ፳፰፥፩-፭ እሑድንም ጌታችን ስለተነሣባትና እኛም ተነሥተን መንግሥተ ሰማይን ስለምንገባባት እንድናከብራት ታዝዘናል። ፍት ነገ አንቀጽ ፲፱  ድድስቅልያ  ፴፩

የምስጢረ ትንሣኤ ሙታንን ነገር በዚህ አበቃን። የከበረችው በረከታቸው፣ ድል የማትነሳ  ረድኤታቸው፣ ጥርጥር የሌለባት ኃይማኖታቸው ከእኛ ጋር ትሁን። ሥሉስ ቅዱስን ያለማጉደልና ያለመጨመር እናምናለን፤ ክፉ ሰዎች ከመከሯት ምክር፣ ከሰይጣን ጠላትነት ታድነን። ለዘለዓለሙ አሜን።

/ ቀሲስ አለማየሁ አሰፋ