ቁርባን ማለት ምን ማለት ነው?

ቁርባን ለሚለው ቃል ሁለት ፍች አለው፤

* አንደኛው ፍቺ ቁርባን ማለት ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ማለት ነው።

* ሁለተኛው የቁርባን ፍች ቁርባን ማለት የሚቀበሉት የሚያቀብሉት ማለት ነው።

 

ቁርባን ምንድነው?

* ቁርባን የክርስቶስ ሥጋውና ደሙ ነው፤ ኤፌ. ፭፥፪

 

አምላካችን፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሥጋውና ደሙ እንዲህ ብሎ ነበር፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው። ዮሐ. ፮፥ በመቀጠልም ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል።ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል ዮሐ. ፮፥

ጌታችን ይህን ነገር በቃሉ ሲነግራቸው መጀመሪያ ለሰሙት ሰዎች በሥራ እስኪያሳያቸው ድረስ ሊታመን የማይችል ረቂቅ ነገር ነበር። ኋላ ግን ሠርቶ ባሳያቸው ጊዜ ተረድተው አምነውበታል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጀመሪያ የሥጋውና የደሙን ምሥጢር ሲያሳይ እንዲህ ነበር ዓርብ ሊሰቀል ሐሙስ ማታ ማለት የሐሙስ ቀን አልፎ የዓርብ ማታ ሲገባ ዓልአዛር በተባለው ሰው ቤት ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር መጀመሪያ የኦሪትን መሥዋዕት ሠውቶ በልቷል። ወዲያው የበሉትን የኦሪት መሥዋዕት በተአምራት ከሆዳቸው አጥፍቶ ሰዎች ለእራት ካመጡለት ኅብስት አንዱን አንሥቶ ያዘና ወደ አባቱ ጸለየ። ኅብስቱንም በሥልጣኑ ለውጦ ሥጋውን አድርጎ ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነውና እንኩ ብሉ ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው መታሰቢያዬንም ይህ አድርጉት ብሎም አስተማራቸው። ቀጥሎም ወይን በጽዋ ቀድቶ ያዘና ጸለየ ወይኑንም ለውጦ ደሙ አድርጎ ይህ ስለእናንተ የሚፈስ ደሜ ነው እንኩ ጠጡ ብሎ ሰጣቸው፤ ሉቃ. ፪፥ ማቴ. ፮፥ ማር. ፬፥

 

ሳይሰቀል አስቀድሞ ምሥጢረ ቁርባንን ያሳየበት ምክንያት ዓርብ ዕለት በተሰቀለ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተገናኝቶ ሥራ ለመሥራት ስለማይቻል ነው፣ ዮሐ. ፮፥፳፪ ሐዋርያትም መታሰቢያዬን ይህን አድርጉ ባላቸው ትምህርት መሠረት ኅብስትና ወይን አቅርበው በጸሎት ሥጋውንና ደሙን እያደረጉ ያቆርቡ ነበረ። ፩ኛቆሮ. ፲፥፲፮ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሥጋውና ደሙ በቀሳውስት እጅ ይሰጠናል፤ የክርስቶስን ሥጋና ደም የምናገኝ በጸሎት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው።

የቤተ ክርስቲያን ማገልገያ ዕቃዎች ንዋየ ቅድሳት ይባላሉ በአማርኛም የክብር፣ የንጽሕና ዕቃዎች ማለት ነው፤ ከንዋየ ቅድሳትም ለሥጋውና ለደሙ ማቅረቢያና ማቀበያ የሆኑ ስት ንዋየ ቅድሳት አሉ እነርሱም፦ ጻሕልና፣ ጽዋ፣ ዕርፈ መስቀል/ማንኪያ/ ናቸው።

 

ከቀሳውስት የዕለቱ ቀዳሽ የሆነው ቄስ ኅብስቱን በጻሕል፣ ወይኑን በጽዋ አድርጎ አንዱ አካል አብ ቅዱስ ነው፣ አንዱ አካል ወልድ በእውነት ቅዱስ ነው፣ አንዱ አካል መንፈስ ቅዱስም በእውነት ቅዱስ ነው ሲሉ ሃይማኖትን ይመሰክሩበታል። የዕለቱ ልዑካን በቤተ መቅደስ ውስጥ ሁነው በመምራት ሕዝቡ በመቀበል ምሉዕ ጸሎተ ቅዳሴን ያደርሱበታል፤ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ሥጋውን ደሙን ተቀብሎ ከኃጢያት ፍርድ ይነፃል የዘለዓለምንም ሕይወት ወርሶ በመንግሥተ ሰማይ ለዘለዓለም ይኖራል። ስለዚህ ጌታችን እንዲህ ብሏል ሥጋዬን የበላ ደሜንም የጠጣ ለእርሱ የዘለዓለም ሕይወት አለው እኔም በኋለኛው ቀን አሥነሳዋለሁ፤ ሥጋዬ የእውነት መብል ነውና፣ ደሜም የእውነት መጠጥ ነውና ሥጋዬን የበላ ደሜንም የጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ አድራለሁ፤ የላከኝ አብ ሕያው እንደሆነ እኔም ስለ አብ ሕያው ነኝ የሚበላኝም ደግሞ እርሱ ስለ እኔ ሕያው ይሆናል። ዮሐ. ፮፥፶፬

 

ጥምቀት አንድ ጊዜ ነው ከተጠመቅን በኋላ በኃጢአት ብንሰነካከልም በንስ ከኃጢሓ,ት ፍርድ እንድናለን እንጂ ሁለተኛ ጥምቀት የለም፤ ዕብ. ፮፥ ፮። እንደምን ቢባል ጥምቀታችን የጌታ ሞት ምሳሌ ነውና። ጌታችን አንድ ጊዜ ሞተልን እንጂ ሁለት ጊዜ አልሞተምና በጌታችን ሞት ምሳሌ ጥምቀት አንድ ጊዜ ብቻ ሆነ። ሥጋውንና ደሙን ግን በየጊዜው እንቀበላለን ይኽ መኾኑ ግን አንድ ጊዜ የሆነው የጌታችን ሞቱ በየጊዜው ለምናምነው ምእመናንና በየጊዜው በድለን ለምንመለስ ኃጥአን ቤዛ በመሆን ሲሰጠን ይኖራልና ስለዚህ ነው።

 

ሥጋውንና ደሙን መቀበልም እግዚአብሔርን ፈርቶ ከሠሩት ኃጢአት ተጸጽቶ ማረኝ ብሎ አልቅሶ ለወደፊቱም ከኃጢአት ተለይቶ ነው፤ ፩ኛ ቆሮ. ፩፥፳፰። ያለፍርሃት በድፍረት ያለንጽሕና በኃጢአት ሆኖ ቢቀበሉት ማለት ከሟርት፣ ከስርቆት፣ ከዝሙት፣ ከሐሜት፣ ከፌዝና፣ ከቧልት ሳይለዩ ቢቀበሉት ግን የገሃነም ፍርድን ያመጣል እንጂ ከኃጢያት ፍርድ አያነፃም፤ ፩ኛ ቆሮ. ፩፥፳፯ ዕብ. ፲፥፳፱ ቸሩ እግዚአብሔር ኃጢአትን ድል የምንነሣበት ረድኤቱን ይስጠን የምስጢረ ቁርባንን ነገር በዚህ እናበቃለን።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

/ ቀሲስ አለማየሁ አሰፋ