ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴ እና በምሥጢረ ሥጋዌ ለሚያምን ሁሉ የተሰጠ የኃጢአት መደምሰሻና ከእግዚአብሔር የመንፈስ ቅዱስ ልጅነትን መቀበያ ነው። ጥምቀት የኃጢአት መደምሰሻ እንደሚሆንም እግዚአብሔር አስቀድሞ በነቢያት ትንቢት አናግሯል። ትንቢቱም የጠራ ውኃ አፈስስባችኋለሁ። (ሕዝ. ፴፮፡፳፭) ተመልሶ ይምረናል፤ ክፋታችንንም ይጠቀጥቃል፥ ኃጢአታችንንም በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል። (ሚክ. ፯፡፲፱)
ኃጢአታችንን መደምሰሻና ልጅነትን መቀበያችን ጥምቀት እንዲሆን ያደረገ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጥምቀት ያስተማረውን ትምህርትና ያዘዘውን ትዕዛዝ ቀጥለን የምንጠቅሰው ነው፦ ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ እውነት እውነት እልኻለሁ ማንም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባ ዘንድ አይችልም። (ዮሐ. ፫፡፭) እንግዲህ ሂዱና በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ፤ አጥምቋቸውም። (ማቴ. ፳፰፡፲፱) ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። (ማር. ፲፮፡፲፮) ከእግዚአብሔር መወለዳችን የእግዚአብሔርን ርስት መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ነው።
መንግሥተ ሰማይን በጥምቀት እንጂ ያለ ጥምቀት ልንገባበት እንደማንችል ጌታችን በትምህርቱ እንደገለጸልን አውቀን መኖር ይገባናል። ይኽም የጌታ ትምህርት ስለ ጥምቀት ለነቢያት ትንቢት መፈጸሚያ፣ ለሐዋርያት ትምህርት መማሪያ ነው። የነቢያት ትምህርት በመጀመርያ የተጠቀሰ ነው። የሐዋርያት ትምህርት ቀጥሎ የምንገልጸው ነው፦ ሐዋርያት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከተማሩ በኋላ ጥምቀት ኃጢአት ማስተስረያና የልጅነት መቀበያ መሆኑን ሲያስተምሩ እንዲህ ብለዋል፦ ጴጥሮስም አላቸው፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። (ሐዋ. ፪፡፴፰)
ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ (ኤፌ. ፭፡፳፭) ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም። (ቲቶ ፫፡፬-፭) የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ስለ ጥምቀት እንዲሁ ሲሉ አስተምረዋል፦ ኃጢአትን ለማስተስረይ በምንጠመቃት አንዲት ጥምቀትም እናምናለን። (ሃይ. አበው ዘሠለስቱ ምዕት) ጥምቀት የኃጢአት መደምሰሻና የእግዚአብሔርን ልጅነት ማግኛ መሆኑን ስናምን ለዚህ እምነታችን መሠረቱ ከብዙ በጥቂቱ የጠቀስነው የነቢያት ትንቢትና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት፣ የሐዋርያትና የሊቃውንትም ትምህርት ነው። የምንጠመቅበት ውኃም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቀኝ ጎን የፈሰሰ ውኃ ነው። ይኽን ውኃ የምናገኘው በጸሎት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው። አጥማቂው ካህን በመጠመቂያ ውኃ ላይ መጽሐፈ ክርስትናን (ጸሎተ ክርስትናን) ይጸልይበታል፤ አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ብሎም በመስቀል ይባርከዋል። በዚህ ጸሎትና ቡራኬ የተጸለየበት ውኃ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተለውጦ ከጌታ ጎን የፈሰሰ ውኃ ሆኖ ይከብራል።
ሕፃናት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ወንዶች በአርባ ቀን ሴቶች በሰማንያ ቀን በጥምቀት ተወልደው ሁለተኛ ልጅነትን ያገኛሉ። አንዳንዶችም በተለያዩ ሁኔታዎች ሕፃን ሳሉ መጠመቅ ያልቻሉና እንዲሁም ደግሞ የክርስትና ሃይማኖትን ተምረው መጠመቅ የሚፈልጉ ወጣቶችና ዓዋቂዎች ሁኔታው በፈቀደበት ጊዜና የሃይማኖት ትምህርቱን እንደጨረሱ ይጠመቃሉ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ጥምቀት ሲከናወን በዚያው ዕለት ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ምሥጢራት ምሥጢረ ሜሮን እና ምሥጢረ ቁርባን ይፈጸማሉ። ይኽ የጥምቀት ምሥጢር ከበደል ነጻ ወጥተን ሕይወትን የምንቀበልበት እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስን በሞቱ እና በትንሣኤው የምንመስልበት በመሆኑ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆላስይስ ሰዎች እና ወደ ሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ እንዲህ ሲል ይነግረናል፦ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ በጥምቀት ደግሞ… ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። … ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። (ቆላ. ፪፡፲፪-፲፬) በማለት እና ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? (ሮሜ ፮፡፫) የጥምቀትን አስፈላጊነት አስተምሮናል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣
ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን!
ሊቀ ሥዩማን ቀሲስ ዓለማየሁ አሰፋ