ፍቅር፣ ቁልፍና ድልድይ
- Details
- Created on Tuesday, 30 September 2014 21:15
- Written by ዳንኤል ክብረት
በሜልበርን እምብርት እየተሽረከርን በያራ ወንዝ ዳርቻ ስንዋብ ወደ ሌላ አቅጣጫ የመሻገሪያ የእግረኞች ድልድይ ላይ ደረስን፡፡ የያራ ወንዝ ዓባይን በሰኔ መስሏል፡፡ እዚህ ወንዝ ዳር ነው የዛሬ 179 ዓም እኤአ 1835 የሜልበርን ከተማ የተቆረቆረችው፡፡ ከ242 ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዛል ያራ ወንዝ፡፡ የመሻገሪያው ድልድይ ወንዙ መካከል በአንዲት አነስተኛ ጀልባ በምትመስል ኮንክሪት መሬት ላይ ቆሟል፡፡ ሀገሬዎቹ ደሴት ብርቃቸው ነው መሰለኝ ‹ፖኒ ፊሽ ደሴት› ይሏታል፡፡ መቼም ፈረንጅ ትንሽን ነገር ታላቅ በማድረግ የሚተካከለው የለም፡፡
ይህንን ድልድይ እያቋረጥን ስንሄድ በግራና ቀኝ በድልድዩ መደገፊያ ላይ የታሠሩና የተቆለፉ ቁልፎችን አየሁ፡፡ ሙሉ የድልድዩን ብረት ከጫፍ እስከ ጫፍ ይዘውታል፡፡ አንዳንዶቹ በሀገራችን ለስታድዮም በር ብቻ ሊውሉ የሚችሉ ቁልፎች ናቸው፡፡ እነዚህ በፍቅራቸው ላይ ሥጋት ሳይኖርባቸው አይቀርም፡፡ አንዳንዶቹ ቁልፎችም ከቻይኖች ዓይን እንኳን ያነሱ ናቸው፡፡ ይህንን ዓይነት ነገር የገጠመኝ ፓሪስ ነበረ፡፡ በፓሪስ የሚገኙ ድልድዮች በዚያ ስማቸውን ጽፈውና ቁልፋቸውን ቆልፈው በሚያንጠለጥሉ ፍቅረኞች ምክንያት ለአደጋ መጋለጣቸውን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ቢጮህ እንኳን ሰሚ አላገኘም፡፡ በተለይ ፖንቴ ደስ አርትስ በዚህ የተቸገረ ድልድ ነው፡፡እዚህ ሜልበርንም ተመሳሳይ ሥጋት ከመዘጋጃ ቤቱ እየተሰማ ፍቅረኞች ግን ከድልድዩ ይልቅ ፍቅራቸው ያሳስባቸዋል፡፡ ድልድዩ ቢሰበር እኛ ደኅና እንሁን እንጂ መልሰን እንሠራዋለን፡፡ የኛ ፍቅር ከተሰበረ ማን ይጠግነዋል? ይላሉ፡፡
ይኼ ደግሞ ባልተጠገነ ፍቅር ምክንያት በልብ ሕመም የሞተችውን ሰርቢያዊቷን ናዳን ያስታውሳቸዋል፡፡ ናዳ በአንድ ትምህርት ቤት የምታስተምር ሴት ነበረች፡፡ ከሕይወት በአንዱ ቀን ሬልጃ ከተባለ የሰርቢያ የጦር መኮንን ጋር በፍቅር ወደቀች፡፡ ዘመኑ የአንደኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ነበርና ሬልጃ ለጦርነት ወደ ግሪክ ሄደ፡፡ በሄደበት ግሪክ ‹‹እኔስ በአገሬ እንኳን ሰው ወፍ አለምዳለሁ›› የምትል ቆንጆ አገኘና ከእርሷም ጋር በፍቅር ወደቀ፡፡ በዚህም ምክንያት ናዳና ሬልጃ ተለያዩ፡፡ ናዳ በዚህ የተነሣ ኀዘንተኛና በሽተኛ ሆነች፡፡ ኀዘኑ ባስከተለባት የልብ ችግርም ምክንያት ገና በወጣትነቷ ሞተች፡፡
ይህ የናዳ ታሪክ የሰርቢያን ወጣቶች አስደነገጣቸው፡፡ የመጀመሪያውና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አያሌ ወዳጆቻቸውን ያሳጣቸው የአውሮፓ ወጣት ፍቅረኞችንም ልብ ነካ፡፡ በዚህም የተነሣ የሚፋቀሩ ወጣቶች ላለመለያየት ብለው፣ የናዳም ዕጣ ፈንታ እንዳይደርስባቸው ፈርተው ቁልፍ እየቆለፉ ናዳና ራጃ አዘውትረው ይገናኙበት ነበር በተባለው ድልድይ ላይ ማንጠልጠል ጀመሩ፡፡ ከሺ ዘመናት በፊት በአውሮፓ የነበረው ይህ ባሕል በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ምክንያት እንደገና አገረሸና አያሌ ድልድዮችን አጥለቀለቀ፡፡
የፓሪሱ የፍቅር ድልድይ
|
ከቀድሞ ጀምሮ የሰውን ልጅ ሲያስጨንቁት ከኖሩት ሰብአዊ ጸጋዎች አንዱ ፍቅር ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው አፍቃሪ ፍጡር ሆኖ ነው፡፡ እንስሳት ይኼ የላቸውም፡፡ እንስሳት ለአንድ ነገር የሚኖር አዝማሚያ (affection) ነው ያላቸው፡፡ ፍቅር የአምላክ ጸጋ ነውና ይህ ሊኖራቸው የሚችለው ሰውና መላእክት ናቸው፡፡ ሰው ሥጋዊ ፍጡር ስለሆነ ነው ስሜትም የሚኖረው፡፡ ስሜት በመላእክት ዘንድ የለም፡፡ ፍቅር ግን አለ፡፡ ማሰብ ከሌለ ስሜት እንጂ ፍቅር አይኖርም፡፡ ፍቅር አንድን ነገር መፈለግ፣ ወደ አንድ ነገር መሳብና ከአንድ ነገር ጋር መቆራኘት ብቻ ሳይሆን አብሮ የሞራልና የእምነት ሕግጋትም አሉት፡፡ ለዚህ ደግሞ ማሰብን ይፈልጋል፡፡ ፍቅር በውስጡ ጽጌረዳ ብቻ ሳይሆን እሾህ፣ የዓሣ ሥጋ ብቻ ሳይሆን የዓሣ እሾህ፣ ማር ብቻ ሳይሆን የንብ ንድፊያ፣ አለው፡፡ አንዳንዴ ለመዳን መርፌን እንደምንወጋው፤ መርፌውም እንደሚያም፣ ነገር ግን መድኃኒቱ እንደሚያድነን፤ ለመድኃኒቱም ብለን የሚያመውን መርፌ እንደምንታገሠው፤ ፍቅርም እንዲህ ይሆናል፡፡ መድኃኒት የያዘ መርፌ ይሆናል፡፡ ይህንን ሁሉ ለማመዛዘንና ለመቀበል ደግሞ አሳቢ ፍጡር መሆን ግድ ነው፡፡ ስሜት የሚያውረውን ፍቅር ነው የሚያበራለት፡፡ ፍቅር ዓይናማ ነውና፡፡ ያውም የልቡና ዓይን፡፡
ሳውዝ ባንክ የእግረኞች ማቋረጫ |
ሰው ፍቅርንና ስሜትን መለየት እያቃተው፣ አንዳንድ ጊዜም ከፍቅር ይልቅ ስሜቱን እያስበለጠ ነው ራሱን መከራ ውስጥ የሚጥለው፡፡ ስሜት ለፍቅር አንዱ ግብዐት እንጂ ብቸኛው ነገር አይደለም፡፡ በፍቅር ውስጥ ከስሜት ሌላ ማሰብ፣ መታገሥ፣ ራስን መግዛት፣ መሸከም፣ ቆራጥ፣ ኃላፊነትን መውሰድ፣ ይቅር ማለትና ሌሎችም አሉበት፡፡ ስሜት ግን የፍቅር ማስጀመሪያ እና ፍቅር ማለስለሻ ነው፡፡ ለአንድ መኪና ባትሪው የሞተሩ ማስነሻ እንደሆነው ሁሉ፤ በባትሪ ብቻ ግን መሄድ እንደማይቻል፤ ያለ ባትሪም መሄድ እንደማይቻል ማለት ነው፡፡ ስሜት እንደ መኪና ቅባቶችና ዘይቶች ያለ ነው፡፡ ቅባትና ዘይት ያነሰው መኪና ችሎ ችሎ አንድ ቀን ወይ ይነጫነጫል፣ ወይ ይቆማል፣ ወይ እሳት ያስነሣል፣ ወይ ሞተር ይነክሳል፡፡ ስሜት ጠፍቶባቸው ሞተር የነከሱ ብዙዎች ናቸው፡፡
ቅባትና ዘይት ግን ለሞተሩና ለሌሎች ዕቃዎች ሕልውና ሲባል የሚደረግ እንጂ በራሱ ሕልውናውን ለብቻ የሚያስቀጥል አይደለም፡፡ ለዘይቱ አይደለም ሞተሩ፤ ለሞተሩ ነው እንጂ ዘይቱ፡፡ እንደዚሁም ነው፡፡ በፍቅር ውስጥ ለሚገኙት ወሳኝ ነገሮች ነው ስሜት የሚያስፈልጋቸው፡፡ እንጂ ለስሜቱ አይደለም እነርሱ የሚያስፈልጉት፡፡ ስሜት ብቻ የያዙ ‹‹ፍቅረኞች›› ናቸው እንደ ሬልጃ እዚህም እዚያም መሄድ፣ ያዩዋትንም ሁሉ መመኘትና እንደ ተረት ገጸ ባሕርይ ‹‹ሲሄዱ፣ ሲሄዱ፣ ሲሄዱ›› የሚኖሩት፡፡
ይኼ እንግዲህ የሰው ዘር ሁሉ ጭንቀት ነውና እስኪ በቁልፍ አሥረን እንሞክረው ብለው ነው ስማቸውን ጽፈው፣ ቁልፍ ላይ ለጥፈው፣ ቁልፉንም ቆልፈው ድልድይ ላይ የሚያስቀምጡት፡፡እንዲህ ዘወትር ሳንለያይ ያኑረን ብለው፡፡ በተለይ በዚህ እና ባለንበት ዘመን ሰው የሰውን ጸባይ ቀርቶ የራሱን ጠባይ መቻል እያቃተው፣ ሰው አንዳች መሥዋዕትነትን ለመክፈል እየሰሰተ ባለበት ጊዜ መሸከምንና መሥዋዕትነትን የሚፈልገው ፍቅር በስሜትና በጊዜያዊ ፍላጎት (ፈቲው) እየተተካ በመሄድ ላይ ነው፡፡ ለዚህ ነው የሰው ልብ መሸከም ያቃተውን ነገር ድልድዮችን ለማሸከም መከራ የሚያየው፡፡ ድልድዮች ደግሞ ‹እናንተ ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ›› አላሉም፡፡ በምን ዐቅማቸው ይሸከሙታል፡፡
ፍቅር ፍቅር አሉት ስሙን አሳንሰው
ከድንጋይ ይከብዳል ለተሸከመው ሰው
አለ የሀገሬ ገጣሚ፡፡
ሜልበርን፣ አውስትራልያ፡፡
Read more http://www.danielkibret.com/2014/10/blog-post.html