ጨረቃና ጨለማ

ጨረቃና ጨለማ
በ1768 እኤአ የተጻፈና ጥንታዊ አባባሎችን የያዘ አንድ ‹‹AN ETHIOPIAN SAGA›› የተሰኘ መጽሐፍ ሳነብ ‹‹ጨረቃዋን እያየህ፣ ጨለማውን ግን እየተጠነቀቅ ተጓዝ›› የሚል ጥንታዊ ብሂል አየሁ፡፡ ይህ ለጥንቱ መንገደኛ የተሰጠ የጠቢብ ምክር ነው፡፡
የጥንቱ ተጓዥ ጤፍ በምታስለቅመው ጨረቃ መጓዙ ሁለት ጥቅሞች ይሰጡት ነበር፡፡ በአንድ በኩል በቀን ከሚገጥመው ሙቀትና የፀሐይ ቃጠሎ ይድናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንገዱን በሩቁ ስለማያየው ‹ለካ ገና ብዙ መንገድ ይቀረኛል› እያለ መንፈሱ እንዳይደክም ያደርገዋል፡፡
በተለይም ደግሞ መንገደኞቹ በዛ ካሉ፣ ሰብሰብ ብለው በአንድ ቤት ታዛ ሥር ወይም በአንድ ዛፍ ጥላ ሥር ያርፉና በአራተኛው ክፍለ ሌሊት(ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በኋላ) ተነሥተው የጨረቃዋን ብርሃን እየተከተሉ መጓዝ ነው፡፡ ያን ጊዜ  ነው እንግዲህ ‹ከጨለማው እየተጠነቀቁ፣ ነገር ግን ጨረቃዋን እያዩ›› የሚጓዙት፡፡
 

መንገደኞቹ ጨረቃዋን የሚያዩዋት ለሁለት ነገር ነው፡፡ በአንድ በኩል ጨረቃዋ መጀመሪያ እየደመቀች፣ በኋላ ደግሞ እየደበዘዘች መጓዟ የሌሊቱን ማለፍና የቀኑን መምጣት ይነግራቸዋል፡፡ በተለይ የበረሐ መንገደኞች ከሆኑ የጨረቃዋ እየደበዘዘች መሄድ ለእነርሱ መልካም ዜና አይደለም፡፡ የሙቀቱን መምጣት እያረዳቸው ነውና፡፡ የፀሐዩን ግለትም እነርሱም ሆኑ የጭነት ከብቶቻቸው አይቋቋሙትም፡፡ በሌላም በኩል የጨረቃዋን ብርሃን እየተከተሉ የሚጓዙት፣ በአካባቢው ሌላ ብርሃን የለምና፣ አንዳንድ ጊዜ ጨረቃዋን ደመና ሲጋርዳት ተግ እያሉ፣ በጠራ ሰማይ ላይ ፍንትው ብላ ስትወጣ ደግሞ መንገዱን ያዝ ያዝ እያደረጉ ስለሚገሠግሡ ነው፡፡
በዚህ ጉዟቸው የሚከተሉት የሚያተኩሩት በጨረቃዋን ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን ጨረቃዋ መንገዱን ብታሳያቸውም ጫካው፣ ሸለቆውና ገደላ ገደሉ ደግሞ በተቃራኒው ድቅድቅ የሆነ ጨለማን ይፈጥራል፡፡ ጥጋጥጉ ሁሉ ከጨረቃዋ ደማቅ ብርሃን ተጋርዶ አንዳች መርግ የመሰለ ጽልመት ይጋርደዋል፡፡ ይኼ ደግሞ የጨረቃዋ ብርሃን ላጋለጣቸው አራዊት ዋና መደበቂያ፣ ለሽፍቶች ዋና መሸሸጊያ ነው፡፡ አንዳንዴም ጨረቃዋ ፍንትው ብላ ስትወጣ ከተገለጠው አካባቢ ግራና ቀኝ ያለው አስፈሪና ምን እንደያዘ የማይታወቅ ሥርቻ ይሆናል፡፡
የጨረቃ ብርሃን እንደ ፀሐይ አይደለም፡፡ የፀሐይ ብርሃን ከሙቀቱ ጋር ስለሚመጣ አካባቢውን ይቀይረዋል፡፡ የብርሃኑ ወገግታም መከለያዎችን እንኳን ተሻግሮ የብርሃን ፍንጣቂ ይለቅበታል፡፡ የፀሐይ ብርሃን ከጨረቃ የተሻለ ምለክዐት አለው፡፡ ጨረቃ ግን ድምቀት ነው ያላት፡፡ አካባቢውን ታስውበዋለች እንጂ አታሞቀውም፡፡ በዚህ የተነሣ ለጨረቃ መንገደኞች ግራ ቀኙ አስፈሪ ነው፡፡  ከሆነ ርቀት በላይም በጨረቃ ብርሃን መንገዱን ማየት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ጨለማውን ተጠንቀቅ›› የተባለው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ሕይወት የጨረቃ መንገድ ትሆናለች፡፡ ብርሃንና ጨለማ፣ ድምቀትና ፍርሃት አብረው የሚገኙባት፡፡ መንገድህን ታውቀዋለህ፤ ነገር ግን ከመንገድህ ግራና ቀኝ የሚጠብቅህን ወጥመድ በሚገባ ላታውቀው ትችላለህ፡፡ ቀና ስትል እንደምታያት ጨረቃ እጅግ የደመቁ ተስፋዎችን፣ ድሎችንና አጋጣሚዎችን ታገኛለህ፡፡ ነገር ግን ጨረቃ ጨረቃዋን ብቻ ስታይና ነፍስህን በሐሴት ስታጥለቀልቅ ደግሞ ከግራና ቀኝህ ከሚገኙት ጉድባዎች፣ ሸለቆዎች፣ ጥሻዎችና ጥጋጥጎች  የደበተ ጨለማ፣ የሚያስፈራም አውሬ፣ የሸመቀም ጠላት ያጋጥምሃል፡፡
መንገደኛው ጨረቃዋን ለማድነቅ በቂ ዕድልን አያገኝም፡፡ መጓዝ ስላለበት፡፡ አንድ ቦታ ቆሞ፣ በደስታ ተደሞ፣ በፍቅሯ ተውጦ፣ በብርሃንዋ ተመስጦ ‹ጨረቃ ድንቡል ቦቃ፣ ዐጤ ቤት ገባች ዐውቃ›› እላለሁ ቢል፣ እርሱ በጨረቃዋ ውበት በተመሰጠበት ጊዜ ከማያውቀው ጥሻ ብቅ የሚል አውሬ ወይም ጠላት አይጠፋም፡፡ አለበለዚያም ደግሞ የሚጣላ ባይሆንም የሚያስደነግጥ ኮሽታ አያጣም፡፡ ስለዚህም በአንድ ልቡ ቀና ብሎ ውበቷን እያየ፣ በአንድ ልቡም መንገድ መንገዱን እያስተዋለ፡፡ አልፎ አልፎም ደግሞ ግራና ቀኙን እየገላመጠ ይጓዛል፡፡
ሕይወት እንደ ጨረቃዋም የምታምር፣ የምትስብ፣ ኑሩብኝ ኑሩብኝ የምትል፣ አንዴ እየጎደለች ሌላ ጊዜ ብትሞላም፣ የምትፈነጥቅና መንገድ የምታሳይ፣ በተስፋና በጉጉትም የተሞላች ናት፡፡ ሕይወት እንደ ጨረቃዋ ፍስስ የምትል፣ የሚዜምላትና የምትናፈቅም ናት፡፡
በሌላም በኩል ደግሞ ሕይወት ተስፋና ደስታ፣ ርካታና ሰላም ብቻ አይደለችም፡፡ መንገደኛው ጨረቃዋን ብቻ እያየና በእርሷም እየተደሰተ ብቻ መጓዝ እንደማይችለው፡፡ ሕይወት ጥሻዎችና ገደሎች፣ ጫካዎችና ጉድባዎችም አሏት፡፡ የጨረቃዋ ብርሃን እንደሚያስደስተው ሁሉ የጫካዎቹ ጥላ፣ የጥሻዎቹ ዝምታ፣ የገደሎቹ ድብታና የገደሎቹም ጨለማ ያስፈራል፡፡ አንድም እዚያ ምን እንዳለ አለመታወቁ፣ አንድም ደግሞ እዚያ አውሬና ጠላት ሊኖር መቻሉ፡፡ የጨረቃዋን ብርሃንና ድምቀት ምን ብንወድደው፣ ጊዜ ሰጥተን ልናጣጥመውም ብንፈልግ እንኳን በግራ በቀኝ ያለው ጨለማና ፍርሃት ግን በቂ ጊዜም በቂ ልብም አይሰጠንም፡፡ ደግሞ እርሱንም እናስባለን፤ ደግሞ እርሱንም ማየት እንፈልጋለን፤ ደግሞ የእርሱንም ዝምታና ጨለማም ማጥናት እናስባለን፤ ምን ሊኖር እንደሚችል፣ ከማናውቀው ምንም ውስጥ ምን ሊወጣ እንደሚችል እንገምታለን፡፡ ከግምታችን ተነሥተንም እንሠጋለን፡፡
ያለፈውን እናስታውሳለን፡፡ ያለፉትንም እናስባለን፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ ስለተጓዙ ሰዎች የተነገረውንም ታሪክና ትርክት እናስታውሳለን፡፡ ተረቶቹንና ንግሮቹን እናመጣለን፡፡ ለጨለማውና ለዝምታው ትርጉም እንሰጣለን፡፡ እንጠረጥራለን፡፡ ኮሽታዎችንና ንቅናቄዎችን ሁሉ እናዳምጣለን፡፡ ለእያንዳንዱ ድምጽ ትርጉም እንሰጣለን፡፡ እንዲህ እያልንም በጨረቃ ድምቀት ተደስተን፣ በግራ ቀኙ ጨለማ ደግሞ ሠግተን እንጓዛለን፡፡ እንዲህ ናት ሕይወት፡፤ ተስፋ ብቻ አይደለችም ሥጋት አላት፣ ደስታ ብቻም አይደለችም ኀዘን አላት፤ የምትታይ ብቻ አይደለችም የማይታይም ክፍል አላት፡፡ የሚታወቅ ብቻ አይደለችም የማይታወቅም አካል አላት፡፡ ለዚህም ነው ቀደምቶቻችን ‹ጨረቃዋን እያየህ፣ ጨለማውን ግን እየተጠነቀቅክ ተጓዝ› ያሉን፡፡
ጨረቃዋን ለማያዩ ሰዎች ሕይወት ጎምዛዛ ብቻ ናት፡፡ ድብርትና ሥጋት የሞላባት፡፡ ምንም ዓይነት የደስታ ፍንጣቂ የማይታይባት፡፡ ከንቱ ብቻ ናት፡፡ ችግርና ጉስቁልና ብቻ የሰፈነባት፡፡ ጨለማውን ለማያዩ ሰዎች ደግሞ ሕይወት ደስታና ፈንጠዝያ፣ ሰላምና እርካታ፣ ፌሽታና ዝላይ ብቻ ናት፡፡ ሁለቱም ግን ይጎዳሉ፡፡ ጨረቃን የማያዩ ሰዎች ሕይወትን ለማጣጣም ዕድል አያገኙም፡፡ ምንም ዓይነት በጎ ነገርንም ከሕይወት አይጠብቁም፡፡ ምንም ዓይነት ደግ ነገር አይታያቸውም፡፡ ምንም ዓይነት ውበት አይገለጥላቸውም፡፡ ሁሉም ጨለማ ብቻ ነው፡፡ ጨለማውን የማያዩ ሰዎች ደግሞ ምንም ዓይነት ዝግጁነት፣ ጥንቃቄና ችግርን የመፍታት ጥበብ የላቸውም፡፡ ሣር ሣሩን ብቻ ሲያዩ ገደል ውስጥ የመግባት ዕጣ ይገጥማቸዋል፡፡ ማሩን እንጂ የንቧን መናደፍ፣ ጽጌረዳውን እንጂ እሾሁን አያዩም፡፡ ሕይወት መዝለልና መዘነጥ፣ መብላትና መተጣት፣ መሳቅና መጫወት ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህም በተወጉና በተነደፉ ጊዜ ይደናገጣሉ፡፡ በቶሎም ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡
በሕይወት በጤነኛ መንገድ ለመጓዝ የተሻለው ጥበብ ጨረቃዋን ማድነቅና በብርሃኗ መሄድ፣ ጨለማውንም መጠንቀቅ ነው፡፡ ሕይወት በጨረቃ ብርሃንና በጨለማው መካከል የተሠመረች ስላች መንገድ ናትና፡፡ እዚህ ላይ ጠቢብ ሰው ሚዛኑን ይጠብቃል፡፡ እዚህ ላይ ጠቢብ ሰው አንድ ዓይኑን በጨረቃዋ ሌላውንም ዓይኑን በጨለማው ላይ ተክሎ ይጓዛል፡፡ ጠቢብ ሰው ሁለቱን ዓኖቹን አንድ ነገር ላይ አይተክልም፡፡ ብዙ ጊዜ አንድን ነገር በሁለት ዓይኖቻችን ነው የምናየው፡፡ ማየት ያለብን ግን የዚያን ነገር ጨረቃና ጨለማ ነው፡፡ ጨረቃዋን በአንድ ዓይን ጨለማውን ደግሞ በሌላው ዓይን፡፡ ሕይወት በጨለማና በጨረቃ መካከል መጓዝ ነውና፡፡
ሜልበርን፣ አውስትራልያ

Read more http://www.danielkibret.com/2014/09/blog-post_25.html

Add comment


Security code
Refresh