ኢዛናና የነገረ ክርስቶስ እምነቱ


በኢትዮጵያ ታሪክ ክርስትናውን በይፋ ያወጀው ንጉሥ ኢዛና ነው፡፡ ኢዛና ክርስትናውን በይፋ በማወጅ ብቻ ሳይሆን በድንጋይ ላይ የጦርነት ታሪኩን መዝግቦ በማቆየትም ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን የታሪክ ሊቃውንት በኢትዮጵያ ክርስትና የተሰበከበትን ጊዜ ከ4ኛው መክዘ ቢጀምሩትም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ግን ከጃንደረባው መጠመቅ አንሥተው ይቆጥሩታል፡፡
በኢትዮጵያ የክርስትና ትምህርት ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም ኦፊሴላዊ እምነት የሆነውና መሠረት ባለው ጽኑ ዐለት ላይ የተተከለው ግን በ4ኛው መክዘ የፍሬምናጦስን ስብከትና ሹመት፣ የኢዛናንም ወደ ክርስትና መመለስ ተከትሎ ነው፡፡ ንጉሥ ኢዛና ከክርስትና ጋር የነበረውን ታሪክ በተመለከተ የሚነግሩን አራት ዓይነት የድንጋይ ላይ ጽሑፎች አሉ፡፡ ሁለቱ በግሪክና በግእዝ፣ ሦስተኛው በግእዝ ብቻ፣ አራተኛው ደግሞ በግሪክ ብቻ የተጻፉ ናቸው፡፡
የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ኢዛና በመንግሥቱ ላይ ያመጹ ሕዝቦችን(ቤጃዎችን) ለመውጋት ያደረገውን ዘመቻ የያዙ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ሲሆኑ ሁለቱ ጽሑፎች[1](ግሪኩና ግእዙ) ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸው ናቸው፡፡ ይሄ የኢዛና የድንጋይ ላይ ጽሑፍ በአንዱ ገጽ በግሪክ የተጻፈ ሲሆን በሌላው ገጽ ደግሞ በግእዝና በሳባውያን(ግእዝን በሳባውያን ፊደል) የተጻፈ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ ኢዛና በአምልኮ ጣዖት ውስጥ እንደነበረ ያሳያል፡፡ ራሱንም የሚጠራው ‹ወልደ መሕረም ዘኢይትመዋዕ ለጸር - ለጠላቱ የማይደፈረው የመሕረም ልጅ› ብሎ ነው፡፡ ሦስተኛው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ በኖባ ሕዝቦች ላይ ስለተደረገው ዘመቻ የሚገልጥ ሲሆን[2]በዚህ ጽሑፍ ላይ ኢዛና አምላኩን የሚጠራው ‹በኀይለ እግዚአ ሰማይ፣ ዘበሰማይ ወምድር መዋኢ - በሰማይና በምድር አሸናፊ በሆነው በሰማዩ ጌታ ኀይል› ብሎ ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ‹በኀይለ እግዚአ ኩሉ - የሁሉ ጌታ በሆነው ኀይል› ይለዋል፡፡

ኢዛና ይህንን የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ባስጻፈበት ጊዜ በአንድ አምላክ ወደማመን መጥቶ እንደነበር አምላኩን የጠራበት አጠራር አመላካች ነው፡፡ በዚህ የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ‹እግዚአ ሰማይ› የሚለው ሰባት ጊዜ ተጠቅሷል[3]፡፡ ‹አረስ/ ማሕረም› የሚለው ስም እዚህኛው ጽሑፍ ላይ የለም፡፡ በሌላ በኩልም ደግሞ ‹እግዚአብሔር› የሚለው ስምም አልተገለጠም፡፡ በኋለኛው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ የምናገኘው ስመ ሥላሴም አልተገለጠም፡፡ 
ሊቃውንቱ ይሄኛው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ሲጻፍ ኢዛና የነበረው አምልኮ ‹በአንድ አምላክ ማመን› መሆኑን ቢስማሙበትም ‹ማንን› የሚለውን በተመለከተ ግን ልዩ ልዩ ሐሳብ አላቸው፡፡ ኮንቲ ሮሲኒ፣ አንቶኒዮ ጉይዲ፣ ሥርግው ሐብለ ሥላሴና ባይሩ ታፍላ በዚህ ጊዜ ኢዛና ክርስትናን ተቀብሏል የሚለውን ሐሳብ ሲቀበሉ ሌሎቹ ግን ክርስትናን የሚያመለክት ነገር የለውም ብለው የተለያየ አመለካከት ሰንዝረዋል፡፡ ሩሲያዊው ዩሪ ኮቢችቻኖቭ በደቡብ ዓረቢያ ከነበሩት ‹በአንድ አምላክ ማመን›ን ከሚመስሉ እምነቶች ጋር ሲያያይዙት ኤ.ዜድ. አስኮሊ ደግሞ ኢዛና ይሁዲ ሆኗል ብለዋል፡፡ ኤፍሬም ይስሐቅ ‹እግዚአ ሰማይ› የሚለው አጠራርና በኋላ ዘመን ኢዛና በሳንቲሞቹ ላይ የተጠቀማቸው መስቀሎች በኢትዮጵያ ለሚታየው ብሉይ ኪዳን ጠቀስ ለሆነው ክርስትና ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ሥርግው ሀብለ ሥላሴ ስለ ጥንታዊና መካከለኛው የኢትዮጵያ ታሪክ በጻፉት መጽሐፍ ላይ ይሄ የኢዛና ገለጻ ክርስትናን ንጉሡ መቀበሉን የሚያመለክት ነው ይላሉ፡፡ ‹የአሬስ/መሕረም ልጅ› የሚለውን ትቶ ‹በኃይለ እግዚአ ሰማይ - በሰማዩ ጌታ ኀይል› ማለቱ በሀገሪቱ የመጣውን የሃይማኖት ለውጥ የሚያመለክት ነው ብለዋል[4]፡፡ ኢዛና ይህንን ባስጻፈበት ዘመን ክርስትና ቢሰበክም ነገር ግን ሃይማኖትን የሚገልጡ መግለጫ ቃላት ገና ያልዳበሩበት ጊዜ ይሆናል፡፡ ኢዛና በአንድ የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ሰባት ጊዜ ‹የሰማይ ጌታ› እያለ መግለጡ በክርስትና ወሳኝ የሆነውን በአንድ አምላክ የማመን ነገር ማጽናቱ መሆኑን የሚገልጡ ሊቃውንት አሉ[5]፡፡
ከኢዛና የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ክርስትናን በተመለከተ ወሳኝ የሚባለው አራተኛው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ነው፡፡ ይህ የድንጋይ ላይ ጽሑፍ የተገኘው በቅርቡ ሲሆን የተጻፈው በግሪክ ነው፡፡ የድንጋይ ላይ ጽሑፉን ያገኙት አለቃ ዘሩ ገብረ እግዚእ ሲሆኑ በአኩስም እንዳ ስምዖን በተባለ ቦታ ቤት ለመሥራት ሲቆፍሩ ነው፡፡ ነገሩ ከተሰማ ቤት እንዳልሠራ እከለከላለሁ ብለው ያሰቡት አለቃ ነገሩን በምሥጢር ይዘውት ቆይተው ነበር፡፡ በኋላ ሲያርፉ ግን ሐውልቱ ወደ አኩስም ጽዮን እንዲዛወር ሐሳብ ነበራቸው፡፡ እርሳቸው በ1961 ዓም ሲያርፉ በግንቦት 1962 ጉዳዩ ወደ አርኬዎሎጂስቶች ዘንድ ደርሶ ሊታወቅ ችሏል፡፡ ሐውልቱ በጀርባው በኩል በሰባውያን ፊደል የተጻፈ ጽሑፍ ሲኖረው በጽሑፉ መጨረሻ የመስቀል ምልክት ተቀርጾበታል፡፡
የድንጋይ ላይ ጽሑፉ ሲጀምር እንዲህ ይላል፡-
በእግዚአብሔር ባለ እምነት በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል፣ መንግሥቴን ባዳነልኝ በእርሱ፡፡ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ባለኝ እምነት፣ በረዳኝ፣ ዘወትርም በሚረዳኝ›
ጥቂት እልፍ ብሎ ደግሞ ‹የአልሜዳ ልጅ፣ የክርስቶስ አገልጋይ› ይላል፡፡
ቀጥሎም ….‹ለእኔ ያደረገልኝን ታላላቅ ነገሮችን አንደበቴና ልቡናዬ ለመናገር የማይቻላቸው ናቸው፡፡ እርሱ ጠናካራና ኃያል አድርጎኛል፤ በማምንበት በልጁም በኩል አዲስ ስም ሰጥቶኛል፡፡ የመንግሥቴም ሁሉ ገዥ አድርጎኛል፤ በክርስቶስ ባለኝ እምነት የተነሣ፣ በእርሱ ፈቃድ፣ በክርስቶስ ኃይል፤ ምክንያቱም የሚመራኝ እርሱ ራሱ ነውና፤ በእርሱ አምናለሁ፤ እርሱ ራሱም መሪዬ ነው› ይላል፡፡
አለፍ ብሎ ደግሞ ‹…በእግዚአብሔር ክርስቶስ ኃይል ተነሣሁ፤ በእርሱ አምናለሁ፣ እርሱም ይመራኛል›› ይላል፡፡
ነገረ ሥላሴ
በዚህ የኢዛና የድንጋይ ላይ ጽሐፍ አሚነ ሥላሴና ትምህርተ ሥላሴ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መመሥረት ጋር አንድ ሆኖ የተሰበከ ትምህርት መሆኑን ያሳያል፡፡ ኢዛና ‹በእግዚአብሔር ባለ እምነት በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል› ብሎ ነው ጽሑፉን የጀመረው፡፡ ይሄ በስመ ሥላሴ ነገርን መጀመር በኋላ ዘመን የታወቀና የተረዳ ትውፊት ሆኖ የጸሎትም፣ የመጽሐፍም፣ የሥራም፣ የደብዳቤም መጀመሪያ ሆኗል፡፡ ነገሥታተ ኢትዮጵያ በጻፏቸው ደብዳቤዎች ሁሉ ይህንን ስመ ሥላሴ እናገኘዋለን፡፡  
ነገረ ክርስቶስ
ኢዛና በዚህ ጽሑፉ በክርስቶስ ላይ ያለውን እምነት በግልጽ አሳይቷል፡፡
1.      ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ‹በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ባለኝ እምነት፣ በረዳኝ፣ ዘወትርም በሚረዳኝ›
2.     ክርስትና የክርስቶስ አገልጋይነት ነው ‹የአልዓሜዳ ልጅ፣ የክርስቶስ አገልጋይ›
3.     ክርስቲያን የሆነው በልጁ በክርስቶስ በማመን ነው ‹በክርስቶስ ባለኝ እምነት የተነሣ፣ በእርሱ ፈቃድ፣ በክርስቶስ ኃይል፤ ምክንያቱም የሚመራኝ እርሱ ራሱ ነውና፤ በእርሱ አምናለሁ፤ እርሱ ራሱም መሪዬ ነው›
4.     ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው ‹በእግዚአብሔር ክርስቶስ ኃይል ተነሣሁ›
ኢዛና ክርስትናን የመንግሥቱ ሃይማኖት ያደረገው በአውሮፓና በእስያ በነገረ ክርስቶስ የተነሣ ከባድ ክርክር በነበረ ጊዜ ነው፡፡ በ325 ዓም የተወገዘው የአርዮስ ትምህርት ምንም እንኳን በጉባኤ ኒቂያ ቦታ ቢያጣም ቤተ መንግሥቱን እየቦረቦረ በመኳንንቱና በነገሥታቱ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ ነበር፡፡ አርዮስ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር አይደለም፤ ከአብም ጋር በህልውናም ሆነ በአሪና አይተካከልም የሚል ትምህርት ነበረው፡፡ ከ332 ዓም ጀምሮም አርዮሳዊነት በባዛንታይን ቤተ መንግሥት በኦፊሴል ተቀባይነት አግኝቶ እስከ 378 ድረስ ዘልቆ ነበር፡፡ በኋላ ይሄው የኒቂያ ትምህርተ ሃይማት በ381 በጉባኤ ቁስጥንጥንያ እንዲጸና ተደረገ፡፡
በዚህ አርዮሳውያን የባዛንታይንን ቤተ መንግሥት በተቆጣጠሩበት ዘመን የኒቂያን ትምህርተ ክርስቶስ አቋም በማስጠበቅ ተጠቃሹ ሐዋርያ ቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ (328- 373 ዓም) ነበር፡፡ በልጅነቱ እለስክንድሮስን ተከትሎ ወደ ኒቂያ በመሄድ በጉባኤው ተገኝቶ አርዮስን ተከራክሮታል፡፡ የጉባኤ ኒቂያ ጸሎተ ሃይማኖት የአትናቴዎስ ሥራ መሆኑን የሚገልጡም አሉ፡፡ ከኒቂያ መልስ በ3ኛው ዓመት የእስክንድርያን መንበር የተረከበው ቅዱስ አትናቴዎስ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፣ ከአብና ከወልድ ጋር በእሪና የተካከለ ነው፤ በህልውናም አንድ ነው የሚለውን ትምህርት አጽንቶ ያስተምራል፡፡
ፍሬምናጦስ ጵጵስናን የተቀበለው ከአትናቴዎስ በመሆኑ የኒቂያን ትምህርተ ሃይማኖትና የአትናቴዎስን የምሥጢረ ሥጋዌ አቋም አጽንቶ ይዟል፡፡ ፍሬምናጦስ በትምህርተ ሃይማኖት በርትቶ ማስተማሩንና ለነገረ ክርስቶስ ትምህርት ከመጀመሪያው ትኩረት መስጠቱን በኢዛና ጽሑፍ እናየዋለን፡፡ ኢዛና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አጽንቶና ደጋግሞ ይናገራል፡፡ በተለይም ‹ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው› የሚለውን የአትናቴዎስን የነገረ ክርስቶስ እምነት በተረዳ ነገር መስክሯል፡፡
ኢዛና ሲጀምር ኃይልን ለአብ፣ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ነው የሰጠው፡፡ ይህም ወልድን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል አድርጎ የገለጠበት ነው፡፡ ክርስቶስንም ‹እግዚአብሔር ክርስቶስ› ብሎ ነው የገለጠው፡፡ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተካከለ እግዚአብሔር ወልድ እንጂ አርዮስ እንዳስተማረው ከእግዚአብሔር ያነሰ(ፍጡር) አለመሆኑን ሲመሰክር ነው፡፡ ስለ ኃይል በገለጠባቸው ሦስት አንቀጾች፡-
·         ‹በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል›
·         ‹በክርስቶስ ባለኝ እምነት የተነሣ፣ በእርሱ ፈቃድ፣ በክርስቶስ ኃይል›
·         ‹በእግዚአብሔር ክርስቶስ ኃይል ተነሣሁ›
መጀመሪያ ‹ኃይል› የሚለውን ለሥላሴ ሰጥቶ ተናግሯል፤ ቀጥሎ ለክርስቶስ ሰጥቶ ተናግሯል፣ በመጨረሻም ለእግዚአብሔር ክርስቶስ› ሰጥቶ ተናግሯል፡፡ በዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥላሴ አንዱ፣ በሥልጣን የተካከለ፣ የሚያመልኩት አምላክ መሆኑን የሚገልጥ ነው፡፡
በተለይም ኢየሱስ ክርስቶስን ‹እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር ቃል፣ ጌታ እግዚአብሔር› ማለት እንጂ ‹እግዚአብሔር ክርስቶስ› ብሎ መጥራት የተለመደ አይደለም፡፡ እስካሁን በተገኙት በቅዱስ አትናቴዎስ ድርሰቶች ውስጥም ይሄ አገላለጥ የለም፡፡ የኢዛና ክርስቶስን ‹እግዚአብሔር ክርስቶስ› ብሎ መጥራቱ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ከመጀመሪያውም ‹ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው› የሚለውን በትምህርት ይዘትነቱ ብቻ ሳይሆን በስም አጠራርም አጽንተው እንዳስተማሩት የሚያሳይ ነው፡፡
ይህንን የኢዛና የሃይማኖት መግለጫ አስደናቂ የሚያደርገው ሌላው ነጥብ ደግሞ በሮም ግዛት ውስጥ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን የአርዮስን ትምህርት እንድትቀበል ከቤተ መንግሥቱ ግፊት እየተደረገባትና የኒቂያ ትምህርተ ሃይማኖት ጠበቃው አትናቴዎስ ከመንበሩ በተደጋገሚ እየተሰደደ እያለ ኢዛና ግን በመንግሥቱ ላይ የሚመጣውን ነገር ሁሉ ተቀብሎ በእምነቱ መጽናቱ ነው፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከሮም ግዛት ውጭ ብትሆንም ዙሪያዋ ግን በሮም ተጽዕኖ ሥር ነበር፡፡ የንግድ መሥመሮቹንና ዋና ዋና የሀብት ምንጮችን ሮማውያን ነበሩ የሚቆጣጠሩት፡፡ ኢትዮጵያም አንደኛዋ የንግድ አጋሯ ሮም ነበረች፡፡ ይህ ሁሉ ግን ኢዛናን እምነቱን በይፋ ከመመስከር አላገደውም፡፡
ሌላው አስደናቂ ነገር ኢዛና ይህንን እምነት ሲያንጸባርቅ ቆስጠንጢኖስ 2ኛ ለኢዛናና ሳይዛና አትናቴዎስን የሚቃወምና አርዮስን የሚደግፍ ደብዳቤ ሁለት ጊዜ ልኮለት ነበር፡፡ በዚህ ደብዳቤ ላይ ፍሬምናጦስ ወደ እስክንድርያ ተመልሶ ከአርዮሳዊው ጳጳስ ከጊዮርጊስ እንደገና ጵጵስና እንዲቀበል የሚገልጥ ነው፡፡ አትናቴዎስንም ይከሳል[6]፡፡ ኢዛናና ሳይዛና ለዚህ የሰጡት መልስ አልታወቀም፡፡ በተዘዋዋሪ መንገድ ግን ኢዛና ባስጻፈው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ የአርዮስ ትምህርት እንዳልተቀበለውና ለኒቂያ ጉባኤ ውሳኔና ለቅዱስ አትናቴዎስ ትምህርት ያለውን ጥብቅና ገልጧል፡፡  
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዚህ የኢዛና አቋም ባትጸና ኑሮ ይሄ አርዮስን የሚቃወመው የኢዛና አገላለጥ በኋላ ዘመን እንዲጠፋ በተደረገ ነበር፡፡ እንዲያውም ‹አርዮስ› ትምህርቱ ብቻ ሳይሆን ስሙ ሳይቀር የክፉ ነገር መግለጫ ሆኖ ነው የቀረው፡፡ ይህም ከ1400 ዓመታት በላይ ሥር የሰደደ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ሀገሪቱም እንኳን ፍሬምናጦስን መልሳ ወደ አርዮሳውያን ልትልከው ቀርቶ ‹ከሣቴ ብርሃን› ብላ ክብሩን ከፍ አድርጋ ገልጣዋለች፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያላትን የጠራና የነጠረ ትምህርትና እምነት ይዛ እስከዛሬ እንድትዘልቅ አድርጓታል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለስብከት ሲባል የምትጠራው ስም ሳይሆን ዋጋ የከፈለችበት አዳኟ ነውና፡፡ ይህንን ታሪኳንና ጠባይዋን የማያውቁ ብቻ ናቸው ‹ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን አታውቀውም› የሚለውን የማይም ድፍረት የሚደፍሩት፡፡


የበለጠ ለማንበብ የዚህ ጽሑፍ ዋና ምንጭ የሆኑትን Stephen L. Black, In the Power of God Christ; Greek inscriptional evidence for anti- Arian of Ethiopia’s first Chrstian king. Bulletin of the School of Oriental and African Studies, University of London.Vl. 71.No.1(2008),pp. 93-110
Stephen Kaplan, ‘’ Ezana conversion reconsidered’’, Journal of Religion in Africa. Vol. 13, 1982

ያንብቡ


[1]Deutsche Aksum – Expedition 4 and 4 bis
[2]Deutsche Aksum – Expedition 11
[3]Stephen Kaplan, Journal of Religion in Africa, , 13, 1982, 103
[4]Ancient and Medieval Ethiopian History, 102
[5] Stephanie L. Black, “In The Power of God Christ”: Greek inscriptional Evidence for the Anti-Arian Theology of Ethiopia’s First Christian King, p.107
[6]Defense before Constantius.

Read more http://www.danielkibret.com/2015/12/blog-post.html