ንሥር (ክፍል ሁለት)

ንሥር (ክፍል ሁለት)
ንሥር ሳይፈትን አያምንም፤ አይተማመንምም፡፡ ሴቷ ንሥር ባል ማግባት ስትፈልግ አንድ እንጨት ታነሣና ወንዱ እየተከተላት ወደ ላይ ትመጥቃለች፡፡ እስከ ሰማይ ጥግ ከደረሰች በኋላም ያንን እንጨት ትለቀዋለች፡፡ ያን ጊዜ ወንዱ እንጨቱ መሬት ከመድረሱ በፊት በፍጥነት በመወርወር መያዝና ለሴቷ መልሶ ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡ ሴቷም እንጨቱን ተቀብላ እንደገና ወደ ቀጣዩ ከፍታ ትመጥቅና እንጨቱን መልሳ ትጥለዋለች፡፡ አሁንም ወንዱ ንሥር ከእንጨቱ የውድቀት ፍጥነት ቀድሞ ያንን እንጨት በመያዝ ለሴቷ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ እንዲህ ያለው ፈተና ወንዱን ለሰዓታት ያህል ይጠብቃዋል፡፡ ከፍታው እየጨመረ፣ እንጨቱም ይበልጥ እየተወረወረ ይሄዳል፡፡ ሴቷ ንሥር ወንዱ ንሥር ፈጣንና የተወረወረለትን ለመያዝ ያለውን ቆራጥነት እስክታረጋግጥ ድረስ ፈተናው ይቀጥላል፡፡ በመጨረሻም ቆራጥና ፈጣን፣ ማንኛውም ችግር የማይበግረው መሆኑን ስታረጋግጥ ባልነቱን ትፈቅድለታለች፡፡
 
ንሥርም እንዲህ ትልሃለች፡- በግላዊ ሕይወትህ፣ በንግድህም ሆነ በሌላው ኑሮህ ከሰዎች ጋር መወዳጀት፣ አብሮ መሥራትና መንገድ መጀመር ያለብህ ለዓላማቸው ምን ያህል ጽኑና ቆራጥ፣ ትጉና አይበገሬ መሆናቸውን አረጋግጠህ መሆን አለበት፡፡ ሳታረጋግጥ መግባት ትርፉ ፀፀት ነው፡፡ እንኳን ሌሎችን ራስህንም ለአዲስ ተልዕኮ ከማሠማራትህ በፊት ፈትነው፡፡
ንሥር በሕይወቱ የሚመጡ ለውጦችን እንደመጡ በአጋጣሚ አይቀበላቸውም፡፡ ተዘጋጅቶና ዐቅዶ እንጂ፡፡ ሴቷ ዕንቁላል የመጣያ ጊዜዋ ሲደርስ ባልና ሚስቱ ዕንቁላል ለመጣያ ምቹና ተስማሚ የሆነውን ቦታ ያፈላልጋሉ፡፡ ያ ቦታ ማንኛውም ዓይነት ጠላት የማይደርስበት፣ ከከፍታዎች ሁሉ በላይ የሆነና ከማንኛውም ዓይነት አደጋ  ራስንና ልጆችን ለመከላከል የሚመች መሆን አለበት፡፡ ቦታው በባልና ሚስቱ ከተመረጠ በኋላ ወንዱ ወደ መሬት ወርዶ እሾህ ለቅሞ ወደ ተራራው ንቃቃት ያመራል፡፡ በዚያም ይደለድለዋል፡፡ ከዚያም ለሁለተኛ ጊዜ ወርዶ አስፈላጊ የሆኑትን እንጨቶች ሰብስቦ ወደ ንቃቃቱ ይመጣና በእሾሁ ላይ ይረመርመዋል፡፡ እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ምድር ይመለስና እሾህ ሰብስቦ ወደ ጎጆው ያመራል፤ በእንጨቱም ላይ ይረበርበዋል፡፡ ለአራተኛ ጊዜ ወደ መሬት ተመልሶም ለስላሳ ሣር ያመጣና በእሾሁ ላይ ያነጥፋል፡፡ በአምስተኛ ጉዞውም እሾህ አምጥቶ በሣሩ ላይ ያደርጋል፡፡ በስድስተኛ ጉዞውም በእሾሁም ላይ ሣር ይነሰንሳል፡፡ በመጨረሻውና በሰባተኛ ሥራው ላባዎቹን በመካከል ላይ ያደላድላቸዋል፡፡ በጎጆው ዙሪያ የተደረገው እሾህም ዙሪያውን ከጠላት ያጥርለታል፡፡
እነሆ ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ምንጊዜም ለለውጥ ራስህን አዘጋጅ፡፡ ነገሮች ድንገት እንዲደርሱብህ ዕድል አትስጣቸው፡፡ አስበህ፣ ተዘጋጅተህ፣ ወስነህ፣ ሂሳብ ሠርተህ እንጂ፡፡ ኑሮህ በድንገቴና በአጋጣሚ የተሞላ አይሁን፡፡ የቻልከውን መጠን ያህል ተዘጋጅ እንጂ፡፡ መጽሐፉስ ‹ተዘጋጅታችሁ ተቀመጡ› አይደል የሚለው፡፡ ለማደግ ተዘጋጅ፣ ለመማር ተዘጋጅ፣ ለጓደኝነት ተዘጋጅ፣ ለማግባት ተዘጋጅ፣ ለመውለድ ተዘጋጅ፣ አዲስ ሥራ ለመሥራት ተዘጋጅ፣ ቤት ለመሥራት ተዘጋጅ፣ መኪና ለመግዛት ተዘጋጅ፣ ለምትለውጣቸው ነገሮች ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ይኑርህ፡፡
ንሥር ትዳሩን በእኩልነት ነው የሚመራው፡፡ ወንዱ ንሥር ጎጆውን ሠርቶ ሲጨርስ ሴቷ ወደ ጎጆው ትገባና ዕንቁላል መጣል ትጀምራለች፡፡ ትዳርን በእኩልነት ነው የሚመሩት፡፡ እርሷ ዕንቁላል ስትጥል እርሱ ደግሞ አካባቢውን ከጠላት ይጠብቃል፡፡ ወደ መሬት እየተመላለሰም ምግብ ይሰበስባል፡፡ ልጆችን መመገብ፣ ማሳደግ፣ በረራ ማለማመድ፣ ከጎጇቸው ርቀው እንዲያድኑ ማሠልጠን የሁለቱም የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡ ድርሻ ይካፈላሉ እንጂ አንዱ የበላይ አንዱ የበታች አይሆኑም፡፡
ስለዚህም ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ትዳር የእኩልነት ጉዞ ነው፡፡ የሥራ ድርሻ ክፍፍል እንጂ የበታችና የበላይ ክፍፍል አይኖረውም፡፡ ሁሉም የችሎታውንና የተፈጥሮውን የሚያደርግበት፣ የጋራ ኃላፊነት የሚወሰድበት ቤት ነው ትዳር፡፡
ንሥር ልጆቹን ደስታንም መከራንም ያስተምራቸዋል፡፡ የንሥር ጫጩቶች አምሮና ደኅንነቱ ተጠብቆ በተሠራው ጎጆ ይፈለፈሉና ወላጆቻቸው እየመገቧቸው እዚያ ጥቂት ያድጋሉ፡፡ ለዐቅመ ንሥር ሲደርሱ የምቾቱ ድልቅቂያ ያበቃና ሴቷ ንሥር ጫጩቶቹን ከጎጆዋ እያወጣች ዐለቱ ላይ ትጥላቸዋለች፡፡ ጫጩቶቹ በፍርሃት ይዋጡና ተመልሰው ወደ ጎጆው እየዘለሉ ይገባሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ማደፋፈሪያ ነው፡፡ የማያድሩበት ቤት አያመሻሹበትም ይባል የለ፡፡‹ሰው እናትና አባቱን ይተዋል› የሚለው በእነርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሊኖር ይችላል ማን ያውቃል፡፡ ለጥቂት ጊዜያት እንዲህ ታለማምዳቸውና በቀጣዩ ጊዜ ከጎጆው አውጥታ ወደ ዐለቱ በመጣል የጎጆውን ለስላሳውን ክፍል ታነሣባቸዋለች፡፡ እነርሱም እንደለመዱት ወደ ጎጆው ሮጠው ዘለው ሲገቡ እሾሁ ይቀበላቸዋል፤ ያቆስላቸዋል፣ ያደማቸዋልም፡፡ እነርሱም እንዲያ የሚወዷቸው እናትና አባታቸው ለምን እንደሚያሰቃዩዋቸው ግራ እየገባቸው ወደ ዐለቱ ተመልሰው ይወጣሉ፡፡
ከጎጆው ውጭ በአድናቆት መቆማቸውን የምታየው ኣናታቸው ከዐለቱ ገፋ ታደርጋቸውና አየር ላይ እንዲንሳፈፉ ትለቃቸዋለች፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ አየሩን የቀዘፉት ጫጩት ንሥሮች በፍርሃትና በድንጋጤ ተውጠው ወደ ታች ሲወረወሩ አባታቸው ይመጣና ከመውደቃቸው በፊት ቀልቦ በትከሻው ተሸክሞ ወደ ዐለቱ ያወጣቸዋል፡፡ እነርሱም በደስታ ይዋኛሉ፡፡ እናት ስትወረውር፣ አባት በአየር ላይ ሲቀልብ፣ ልጆችም ሲወረወሩና ሲጨነቁ፣ አባታቸው ሲቀልባቸው ሲደሰቱ ጥቂት ጊዜያት ያልፋሉ፡፡ በአካል እየጠነከሩ፣ ከመከራውም ከደስታውም እየተማሩ፣ አካባቢውንም እየለመዱት ይሄዳሉ፡፡ በመጨረሻም ራሳቸውን ችለው ይበራሉ፡፡ ከወላጆቹ ጋር ኖሮ የሚያረጀውን ቢያዩ ኖሮ ንሥሮች ምን ይሉ ይሆን?
ለዚህ ነው ንሥር እንዲህ የሚለው፡- ለልጆቻችን ከልክ ያለፈ ክብካቤ መስጠት የትም አያደርሳቸውም፡፡ መከራውንም፣ ችግሩንም፣ ፈተናውንም፣ ትግሉንም፣ ተግዳሮቱንም እንዲለምዱት ማድረግ አለብን፡፡ አፈር አይንካህ፣ የፈሰሰ ውኃ አታቅና፣ ማንም በክፉ አይይህ፣ እንደ ዕንቁላል ትሰበራለህ፣ እንደ መስተዋት ትሰነጠቃለህ እያሉ ነገ በእውኑ ዓለም የማያገኙትን ቅንጦትና ምቾት ብቻ ማሳየቱ የትም አያድርሳቸውም፡፡ እሾሁንም፣ ዐለቱንም፣ መወርወሩንም፣ መውደቁንም፣ መታገሉንም፣ ማሸነፉንም ይልመዱት፡፡ ነገን በጥቂቱ ዛሬ እናሳያቸው፡፡ የሚወዱን ሰዎች ማለት የሌለ ገነት ፈጥረው የሚከባከቡን ማለት ብቻ አይደሉም፡፡ ሰው መሆን ለሚያጋጥመው ተግዳሮት ሁሉ ዝግጁ እንድንሆን የሚያደርጉን እንጂ፡፡ ቤት ሣርና ላባ ብቻ ሳይሆን እሾህም ሊኖረው ይገባል፡፡
ንሥር ሲዳከም የት መሄድ እንዳለበት ያውቃል፡፡ ንሥር ሲዳከም ላባዎቹ ደካሞች ይሆናሉ፡፡ እንደቀድሞው በፍጥነት እንዲበር፣ ወደ ላይም እንዲመጥቅ አያስችሉትም፡፡ እንደ በረቱ መዝለቅ የለ፡፡ ጉልበቱ ሲደክም፣ ላባው ሲነጫጭና የሞት ሽታ ሲሸተው፣ ጉልበቱ ሳይከዳው በፊት ወደ አንድ ማንም ወደማይደርስበት የተራራ ጫፍ ያመራና በንቃቃቶቹ መካከል ጎጆ ሠርቶ ይቀመጣል፡፡ እዚያ ምግቡን አከማችቶ ያርፋል፡፡ የጽሞና ጊዜም ይወስዳል፡፡ የተረፉትን ላባዎቹን እየነጨ መለመላውን ይቀራል፡፡ ቀስ በቀስም አዲስ ላባ ያበቅላል፡፡ ኃይሉም እንደ ጥንቱ ይታደሳል፡፡ ያን ጊዜ ወደ ቀድሞ ኑሮው በአዲስ ጉልበትና በአዲስ መንፈስ ይመለሳል፡፡
እናም ንሥር እንዲህ ይልሃል፡- ጉልበትህና መንፈስህ፣ ሐሳብህና የማመንጨት ዐቅምህ ሲዳከም ዝም ብለህ አትናውዝ፤ እስክትደከርትም አትሟዘዝ፡፡ ነገሮች እንጨት እንጨት ሲሉህ፣ የማስቲካው ቃና ሲያልቅ፣ የሸንኮራው ጣዕም ሲሟጠጥ ‹ደኅና ነኝ› እያልክ ራስህን አትሸንግል፡፡ ይልቅ የት መሄድ እንዳለብህ አስብ፡፡ የጽሞና ጊዜ ውሰድ፤ ለአእምሮህ ምግብ የሚሆኑህን ሰብስብና መንን፡፡ የማሰቢያ፣ የማሰላሰያም ጊዜ ውሰድ፡፡ የድሮ ሐሳቦችህን እንደ ላባዎቹ ነቃቅል፡፡ በቃኝ በል፡፡ ጊዜ ወስደህ ካሰብክ፣ ካነበብክ፣ ከመረመርክ፣ ካሰላሰልክ፣ ካወጣህና ካወረድክ አዳዲስ መንገዶች፣ አዳዲስ ሐሳቦች፣ አዳዲስ ነገሮች፣ አዳዲስ አመለካከቶችን ማብቀል ትችላለህ፡፡ ያን ጊዜ በአዲስ ጉልበት እንደገና ለመመለስ ትበቃለህ፡፡
እንደ ሰው ብትፈጠርም እንደ ንሥር ኑር፡፡
(መረጃ የሰጠኝን የሲያትሉን ኃይለ ኢየሱስ አመሰግነዋለሁ)
 
© ሁለቱም ክፍሎች በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ወጥተዋል

Read more http://www.danielkibret.com/2014/08/blog-post_7.html