ጾመ ፍልሰታ
- Details
- Created on Monday, 04 August 2014 08:24
- Written by ማሕበረ ቅዱሳን
ሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም.
መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
ጾመ ፍልሰታ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገቷ የሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡ እመቤታችን በተለያዩ ጊዜያት ሞትና ትንሣኤዋን ለሐዋርያት የገለጸችበትን ምስጢር ከነሐሴ 1-16 ድረስ ምእመናን በጾም በጸሎት ተወስነው የልጇን ቸርነት የእርሷን አማላጅነት በሱባኤ ይማጸናሉ፡፡ የሱባኤው ወቅት ሲፈጸም “እመቤታችን በእውነት ተነሥታለች” ብለው በደስታ የጾሙን ወቅት ይፈጽማሉ፡፡ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን ቅዱስ ያሬድ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የሐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው፡፡ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል” በማለት ገልጾታል፡፡
በኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ 64 ዓመታት ያህል ቆይታ አርፋ ተነሥታ በክብር አርጋለች፡፡ ይህንን የትንሣኤና ዕርገት ዐቢይ ምሥጢር ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ተንሥአ እግዚኦ” ውስተ ዕረፍትከ፡፡ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፡፡ አንተና የመቅደስህ ታቦት” /መዝ.131፡8/፤ እንዲሁም “ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” /መዝ.44፡9/ ሲል የተናገረው ቃለ ትንቢት በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና የጸናች የቅድስት ድንግል እመቤታችንን ዕረፍት፣ ትንሣኤ፣ ፍለሰት /ዕርገት/ ያስገነዝባል፡፡ /ራእ.11፡19/
እመቤታችን ታቦተ እግዚአብሔር መሆኗን አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ሲገልጽ “ከመ ታቦት ሥርጉት በወርቀ ዓረብ ወተርሴስ በድንግልና ማርያም ሥርጉተ ሥጋ ወነፍስ” ሲል አመስግኗታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በትርጓሜያቸው ይህንን ቃለ ትንቢት ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ከገለጣት “ንግሥተ ሰማይ፤ የሰማይ ንግሥት” /ራእ.12፡1/ ጋር በማገናዘብ የእመቤታችንን ሁለንተናዊ ክብርና ልዕልና አምልተውና አስፍተው ገልጸውታል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ “… በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው፡፡….. ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ሥራቸውም ይከተላቸዋል” /ራእ.14፡13/ ብሎ እንደመሰከረው እመቤታችን ከዕረፍቷና ዕርገቷ በኋላ የመጨረሻ ወደ ሆነው ክብር መሸጋገሯ ያስረዳል፡፡
ይህንን ክብርዋን በመረዳት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር “ወበእንተዝ ናዐብየኪ ኩልነ ኦ እግዝእትነ ወላዲተ አምላክ ንጽሕት ኩሎ ጊዜ፡፡ ንስአል ወናንቀዐዱ ኀቤኪ ከመ ንርከብ ሣህለ በኀበ መፍቀሬ ሰብእ፤ ሁልጊዜ ንጽሕት የምትሆኚ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ ስለዚህ ነገር እናከብርሻለን፣ እናገንሻለን፡፡ ሰውን ከሚወድ ልጅሽ ዘንድ የቅርታንና ምሕረትን እናገኝ ዘንድ ሁል ጊዜ ዓይነ ልቡናችንን ወደ አንቺ እናነሣለን፡፡ በማለት ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ ሁል ጊዜ ዓይነ ልቡናችንን ወደ አንቺ እናነሣለን፡፡ በማለት ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣትን ልዩ የቃል ኪዳን ጸጋና አምላካዊ ክብር እያመሰጠሩ ያመሰግኗታል፡፡ ሊቁ “ቀስተ ደመና ማርያም ትእምርተ ኪዳኑ ለኖኅ፣ ዘእግዚአብሔር ሤመኪ ለተዝካረ ምሕረት ወፍትሕ፣ ህየንተ ቀስፍ ለምድር ወአማሰና አይኅ፡፡ ብሎ እንዳመሰገናት፡፡
እመቤታችን በአጸደ ሥጋ ሳለች ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ በመዋዕለ ሥጋዌ ላደረገው የድኅነት ዓለም ጉዞ ምክንያት ነበረች፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ባርነትና ስደት ለማጥፋት ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ የሰው ልጆችን ያሳደደ ሠይጣን በሄሮድስ አድሮ ሲያሳድደው ልጇን ይዛ በመሰደድ ለድኅነታችን ምክንያት ነበረች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በራእዩ እንዳየው፤ “ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች፡፡ እርስዋም ፀንሳ ነበር፡፡ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጨንቃ ጮኸች፡፡ ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ፡፡ አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔር ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ፡፡ ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስልሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች ”/ራእ.12፡1-6/
“ዘንዶውም ወደ ምድር እንደተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት፡፡ ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፣ ዘመሃትም፣ የዘመን እኩሌታ ወደምትመገብበት ወደ ሥፍራዋ፣ ወደ በረሀ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የትላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት፡፡ እባቡም ሲቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተኋላዋ አፈሰሰ፡፡ ምድሪቱም ሴቱቱን ረዳቻት፡- ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው፡፡ ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ፡፡” /ራእ.12፡13-17/ ሲል መስክሮአል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያውን አምላካዊ ድንቅ ተአምር ባደረገበት በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤት እመቤታችን ከልጇ ከወዳጇ ጋር እንደነበረችና ለተአምሩም ምክንያት ነበረች፡፡ በገሊላ ቃና የተፈጸመው ታላቅና ድንቅ አምላካዊ የቸርነት ሥራ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ የፈጸመውን የቤዛነት ሥራ ሲያደርግ ምክንያት የነበረችው እመቤታችን ነች፡፡ ይኸውም በቀራንዮ አደባባይ በተሰቀለባትና ማየ ሕይወት የሆነውን አማናዊ ወይን ደሙን ባፈሰሰባት ዕለት ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ከእግረ መስቀሉ አጠገብ ነበረች፡፡ በዚህም አዲሲቷ ሔዋን እመቤታችን በክርስቶስ ቤዛነት ለዳነውና በወርቀ ደሙም ለተዋጀው አዲሱ የሰው ዘር ማለትም የክርስቶስ ምሥጢራዊ አካል /ቤተ ክርስቲያን/ መንፈሳዊት እናት ሆና በጸጋ ተሰጥታናለች /ዮሐ.19፡26-27/
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ ነገረ ማርያም፣ ስንክሳርና ተአምረ ማርያም እንደሚያስረዱት፤ ጥር 21 ቀን ዐርፋለች፡፡ እረፍቷን ቅዱስ ዳዊት ሲናገር “አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” መዝ.136፡8 ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ ሲል ቅዱስ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ ዓለም ከኖረች በኋላ ነብሷ ከሥጋዋ ተለይቶ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው፡፡ ታቦት ያላትም ማደሪያው ስለሆነች ነው፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን “ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነይ እነሆ ክረምት አለፈ ዝናቡም አልፎ ሄደ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፡፡ የዜማም ጊዜ ደረሰ የቀረ… ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጐመራ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፡፡ ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነይ” ሲል ስለ እመቤታችን በምሳሌ ተናግሮአል፡፡ መኃ 2፡1አ-13
ወዳጁን ውበቱን ተነሺ ነይ እያለ የተጣራው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ተጠሪዋም እመቤታችን ናት፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ ማለት በስደት በአይሁድ የዘወትር ጠላትነት በልጅዋ መከራና ስቅላት ስምዖን በቤተ መቅደስ እንደተናገረ ልቧ በሀዘን ሠይፍ የተከፈለበት በሀዘን ፍላጻ የተወጋበት የመከራ ክረምት /ወቅት/ አልፎ የክርስቶስ ሕማሙ ፣ ሞቱ፣ ቤዛነቱ ተፈጽሟል፡፡ ትንሣኤው በምድር ላይ ተገልጧል፣ ተሰብኳል ማለት ነው፡፡ በምድራችን አበባ ታይቷል ማለት የሐዋርያት ድምፅ በምድር ሁሉ ደርሷል ማለት ነው፡፡
ነቢዩ ዳዊት ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ ብሎ ስለ ሐዋርያት የተናገረው በዓለም ያለውን መከራ ስድት ሲገልጽ ነው፡፡ /መዝ 18¸4/ የዜማም ጊዜ ደረሰ ያለው የመከራን ጊዜ ነው፡፡ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ በደስታ ይጮሃሉ፣ ይዘምራሉም ተብሏል፡፡ መዝ 14፡13 የመከር ጊዜ ደረሰ የተባለው መከር የፍሬ ጊዜ በመሆኑ ክርስትና አፍርቷል ማለት ነው፡፡ በለሱ ጐመራ ማለት ደግሞ በጐ ምግባረ ፍሬ ሳያፈሩ የነበሩ ሰዎች በጐ ምግባር መሥራት መጀመራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በመጨረሻም ወይኖች አብበዋል፣ መዓዛቸውንም ሰጥተዋል እንደተባለ በመላው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት በሃይማኖት ማበብ መዓዛ ምግባራቸውን ማቅረብ ከጀመሩ በኋላ እመቤታችን አረፈች፡፡
እመቤታችን ጥር 21 ቀን እረፍት በሆነበት እለት ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ ለማሳረፍ ወደ ጌቴሰማኒ መካነ እረፍት ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንዓት መንፈስ ተነሣሥተው “ቀድሞ ልጅዋን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሳ፡፡ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ አረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል" እያሉ በማስተማር ሕዝቡን ፈጽመው ወስደውታል፡፡ አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷንም እንደ ልጅዋ ተነሣች አረገች እያሉ በማስተማር ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን; ኑ ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት ብለው ተማክረው መጥተው ከመካከላቸው ታውፋኒያ የተባለው ጐበዝ አይሁዳዊ ተመርጦ ሄዶ የእመቤታችንን ሥጋ የተሸከሙትን አልጋ ሽንኮር ያዘ፡፡ የአልጋውን ሽንኮር በያዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሠይፍ ሁለት እጁን ስለ ቆረጣቸው ከአልጋው ሽንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ ታውፋንያ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ወደ እመቤታችን ስለተማጸነ በተአምር የተቆረጡ እጆቹን እንደ ቀድሞ አድርጋ ፈውሳዋለች (ስንክሳር ዘጥር፡፡)
የእግዚአብሔር መልአክ የእመቤታችን ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ተድላ ደስታ ወደ አለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቁ፡፡ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ትወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከእፅ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን የማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ጌታችንም ዘላለማዊ ወደሆነ መንግሥተ ሰማያት መላእክት እና ሰማእታት እየሰገዱላት አሳረጓት፡፡ ንጉሥ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እንዳለ፡፡ መዝ 44፡9
ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ተመልሶ ከሰማይ ወረደ፡፡ ሐዋርያት ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋም በታላቅ ክብር ማረጉን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ፡፡ የነሐሴም ወር በባተ /በገባ/ ቀን ዮሐንስ እንዲህ አላቸው፡፡ የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት ኑ፤ ሁለት ሱባኤ በመጾም እንለምን አለ፡፡ በጾም በጸሎት ሱባኤ ያዙ፤ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴና በምሕላ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ እረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡
የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቶማስ አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ትንሣኤዋን ሌሎቹ ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተበሳጭቶ “በመጀመሪያ የልጅሽን ትንሣኤ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ” ብሎ ከማዘኑ የተነሣ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ ቃጣው፡፡ እመቤታችንም ከእርሱ በቀር ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሳኤዋን እንዳላዩ ነግራው አጽናንታው ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ምልክት ይሆነው ዘንድ ሰበኗን - መግነዟን ሰጥታው አረገች፡፡
ሐዋርያው ቶማስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” አላቸው፡፡ “አንተ እንጂ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንምን;” ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ እመቤታችን መካነ መቃብር ይዘውት ሄደው መቃብሩን ቢከፍቱ ሥጋዋን አጡት፡፡ ደነገጡም፡፡ ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችን ተነሥታ አርጋለች” ብሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ ለማረጋገጫ ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሰበኗን - መግነዟን ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄደዋል፡፡
ሐዋርያትም ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እኛ እንዴት ይቀርብናል ብለው በቀጣዩ ዓመት ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በሱባኤው መጨረሻ በነሐሴ አሥራ ስድስት ቀን ጌታችን ጸሎታቸውን ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ ረዳት ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ ዋና ዲያቆን አድርጐ ቀድሶ ሁሉንም ከአቆረባቸው በኋላ የእመቤታችንን እርገቷን ለማየት አብቅቷቸዋል፡፡
ቤተክርስቲያናችንም ሥርዓት ሠርታ ከሰባቱ ዓበይት አጽዋማት ተርታ አስገብታ ይህን ታላቅ የበረከትና የምሥጢር መግለጫ ጾም እንድንጾም አድርጋናለች፡፡ ሐዋርያት ያዩትን ድንቅ ምሥጢር የእመቤታችንን ትንሣኤና ዕርገት ለማየትና ከሐዋርያት አበው በረከት ለመሳተፍ ጌታችን “ልጆቼ” ይላቸው ለነበሩ ሐዋርያት አምሳል ሕፃናትና ወጣቶች፣ ሴቶችና ወንዶች፣ አረጋውያንም የጾመ ፍልሰታን መድረስ በናፍቆት እየጠበቁ በየዓመቱ በጾም በጸሎት ያሳልፉታል፡፡
ጾመ ፍልሰታ በሕፃናት፣ በምእመናንና በካህናት ዘንድ በተለየ ፍቅር የምትታይና ታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚከናወንባት ወቅት ናት፡፡ ካህናት ሌሊት በሰዓታት ቀን በቅዳሴ፣ መዘምራን በስብሐተ ነግህ /የጠዋት ምስጋና/ ሕፃናት በመዝሙር ያሳልፏታል፡፡ እናቶች ደግሞ ጠዋት ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ሲያዳምጡ፣ ቀን ቅዳሴ ሲያስቀድሱ ውለው ማታ መብራት አብርተው መዝሙረ ፍልሰታን ይዘምራሉ፡፡ በመዝሙሩ የቅድስት ድንግል ማርያምን ስደት፣ የደረሰባትን መንገላታትና አማላጅነት በማንሳት የተማኅጽኖ ጸሎት ያቀርባሉ፡፡ በምግባር በሃይማኖት መጽናት የሚሰጠውን ጸጋ ይናገራሉ፡፡ እናቶች ከመዘምሩት መዝሙር መካከል፤-
ወፌ ሰንበታ ሰንበታ
መጣች ለፍልሰታ
አገርሽ የት ነው ኤፍራታ
አሳድሪኝ ማታ፡፡
ይናፍቀኛል ሌሊት
የሰማይ እልፍኝ መብራት
ወፌ የኔ እመቤት /2/
ከሁሉ ከሁሉ ጤፍ ታንሳለች
ከጭቃ ወድቃ ታነሣለች
ከዚያች ጤፍ ከዚያች ጤፍ
የአዳም ልጅ ሁሉ አትስንፍ
የአዳም ልጅ ሁሉ ሰነፈና
የኑሮ ቤቱን ረሳና
ተው አትርሳ
ተው አትርሳ
ተሠርቶለሃል የእሳት አልጋ
ያን የእሳት አልጋ
የእሳት ባሕር
እንደምን ብለህ ትሻገር
ተሻገሩት አሉ በሠሩት ምግባር
እኔ ባሪያሽ ወዴት ልደር
/እንደምን ብዬ ልሻገር/
ሰላም ሰጊድ እያሉ ሌሊቱን በሙሉ እሳት አንድደው ያመሰግኗታል፡፡ ይማጸኗታል፡፡
የእመቤታችን ትንሣኤና እርገት መታሰቢያ - ጾመ ፍልሰታ ብዙዎች ከቤታቸው ተለይተው በመቃብር ቤት ዘግተው፣ አልጋና ምንጣፍ ትተው፣ በመሬት ላይ ተኝተው ዝግን ጥሬ እፍኝ ውኃ እየቀመሱ በጾምና በጸሎት በመትጋት በታላቅ ተጋድሎ ይሰነብታሉ፡፡ በሰሙነ ፍልሰታ ምእመናን ለእመቤታችን ያላቸውን ጽኑና ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩበት ነው፡፡
ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሙስና መቃብር ሳያገኘው፣ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ እንደተነሣ እርሷም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን በኃይልና በሥልጣን መነሣት የመለኮት ኃይል ቢሆንም እመቤታችን የተነሣችው በልጇ ኃይልና ሥልጣን ነው፡፡ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ” ነው ተብሎ ሲከበርላት የሚኖረውም ለዚህ ነው፡፡
Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1528-2014-08-04-14-29-15