“አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” /መዝ.131፥8/

 

ነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም.


Emebetachin-Eriget ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሐ ምጡቀ ፤ በአእባነ ባህርይ ዘተነድቀ ፤ማርያም ደብተራ እንተ ኢትትከደኒሠቀ፤እመቤቴ ማርያም ሆይ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል ፡፡ ይኸውም ኅብሩ ሊመረምሩት በማይቻል ዕንቊ የታነፀ ሕንፃ ይገኝበታል፡፡


እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አዳም አባታችን እግዚአብሔርን በድሎ፣ ክብሩን አጥቶ፣ ሞተ ሥጋ ሞተ ነብስ ተፈርዶበት፣ ከገነት ሲባረር ፤ ምህረትና ቸርነት የባህሪው የሆነው አምላክ ይቅር ይለው፣ ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ ተማጽኗል፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የአዳምን ማዘን፣ መጸጸት ፣ ንስሀ መግባት ተመልክቶ 5500 ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ስደትህን በስደቴ፣ ሞትህን በሞቴ አጥፍቼ የቀደመ ክብርህን መልሼ ያጣኸውን ርስት ገነት መንግስተ ሰማያት አወርስሃለሁ፡፡ገላ4፡4 በማለት ቃል ኪዳን ገብቶለታል፡፡


አዳም አባታችን ቃል ኪዳን በተገባለት መሠረት የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ለእግዚአብሔር ወልድ ማደሪያነት የተመረጠች፣ ለአዳም እና ዘሩ መዳን ምክንያት የሆነች የልጅ ልጅ የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዳ 15 ዓመት ሲሆናት በቅዱስ ገብርኤል ብስራት የእግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ማደሪያ ሆነች፡፡ ልጇን በወለደች ወቅት የሰብዓ ሰገልን “የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት አለ” የሚለውን ዜና የሰማ ሄሮድስ የተወለደውን ህጻን ለመግደል አዋጅ አወጀ ፡፡ እመቤታችንም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማዳን ወደ ግብጽ ይዛው ተሰደደች ማቴ.2፡12፡፡


የስደት ዘመኑ አልቆ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ 30 ዘመን ሲሆነው ስለመንግስተ እግዚአብሔር ስለ ሰው ልጆች ነጻነት ይሰብክ ጀመር፡፡ ኃላም የአዳም ዘር ሞት ለማጥፋት ፣ባርነትን አጥፍቶ ነጻነትን ለማወጅ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ ፡፡ በሦስተኛው ቀን ተነስቶ ነጻነትን አወጀ፡፡ በዚህ ሁሉ የድኅነት ጉዞ ውስጥ ያልተለየችና ምክንያተ ድኂን የሆነችው እመቤታችን የሰው ልጆች ድኅነት ሲረጋገጥ በተወለደች በ64 ዓመቷ ጥር 21 ቀን አረፈች፡፡


a ergete mariam 2006 1 ሐዋርያት መጽናኛቸው እናታቸው ቅድስት ድንግል ማርያም ብታርፍባቸው ሥጋዋን ባጎበር አድርገው ወደ ጌቴ ሴማኒ ይዘዋት ሄዱ አይሁድ “ቀድሞ ልጇን ሰቅለን ብንገድለው ደቀ መዛሙርቱ ተነሣ፣ ዐረገ” እያሉ ሲያውኩን ኖሩ፤ ዛሬ ደግሞ እርሷን ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን? በእሳት እናቃጥላታለን” ብለው ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል የታውፋንያን ሁለት እጁን በሰይፍ መትቶ ቀጣው፡፡ በዚህም የታውፋንያ ሁለት እጁ ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ፡፡


ከዚያ በኋላ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌላዊውን ቅዱስ ዮሐንስ ጨምሮ በደመና ነጥቆ ከገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት፡፡ዮሐንስ ከገነት ሲመለስ ለሐዋርያት “ የእመቤታችንን ሥጋ ወደ ገነት መወሰድ ነገራቸው፡፡ “ዮሐንስ የእመቤታችንን ሥጋ ገነት ማረፍ አይቶ እኛ ሳናይ” ብለው፤ ከነሐሴ 1 ቀን - ነሐሴ 14 ቀን ጾመዋል፡፡ "ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሓ ወኑዛዜ፡ ኀበ ኢይሬእይዎ ለላህ ወኢይሔይልዎ ለትካዜ፡ ማርያም ህሉት ዉስተ ልበ ኣምላክ እምቅድመ ግዜ፡ ትፍሥሕትሰ ተፈሣሕኩ ብፍልሰትኪ ይእዜ፣ ገጸ ዚኣኪ እሬኢ ማዕዜ”ይላል መልክዓ ፍልሰታ፡፡


እግዚአብሔር ሀዘናቸውን ተመልክቶ መጽናናትን ይሰጣቸው ዘንድ ከነሐሴ 1 ቀን -ነሐሴ 14 ቀን ሐዋርያት በአንድ ልብ ሆነው ሱባኤ ያዙ (በጾም በጸሎት ተወስነው ) እግዚአብሔርም የልብ መሻታቸውን አይቶ ነሐሴ 14 ቀን ጌታ የእመቤታችንን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ትወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከዕፅ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን የማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ሐዋርያት ገንዘው በክብር ቀብረዋታል፡፡ ስለ ግንዘቷም "ሰላም ለግንዘተ ሥጋኪ ብእደ ሓዋርያት ኣርጋብ፤ ብአፈወ ዕፍረት ቅዱው ዘሐሳብ ሴቱ ዕጹብ፤ ማርያም ድንግል ውለተ ህሩያን ሕዝብ፤ ረሰይኩኪ እግዝእትየ ህየንተ እም ወኣብ፤ ይኅጽነኒ ከመ ጥብ ፍቅርኪ ሓሊብ።” ያለው ለዚህ ነው፡፡


ቅዱስ ያሬድ በዝማሬ ድርሰቱ “በስብሐት ውስተ ሰማያት መላእክት ወሊቃነ መላእክት ወረዱ ለተቀብሎታ፣ እብለኪ ወእሙ ለእግዚእየ እብለኪ ዳዊት አቡሃ ምስለ መሰንቆሁ ሙሴኒ እንዘ ይፀውር ኤፉደ መጽኡ ሃቤሃ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ሐዋርያት አጠኑ ሥጋሃ በማዕጠንተ ወርቅ፣ ሱራፌል ወኪሩቤል ሰፍሑ ከነፊሆሙ ላዕሌሃ፣ ወረደ ብርሃን እምሰማያት ወመብረቀ ስብሐት እምውስተ ደመናት፣ ተለዓለት እምድር ውስተ አርያም በስብሐት ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ” ብሏል፡፡


ጌታችንም ዘላለማዊ ወደሆነ መንግሥተ ሰማያት መላእክት እና ሰማዕታት እየሰገዱላት አሳረጓት፡፡ ንጉሥ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እንዳለ /መዝ 44¸9/፡፡ ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ተመልሶ ከሰማይ ወረደ፡፡ ሐዋርያት ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋም በታላቅ ክብር ማረጉን ነገራቸው፡፡


መላእክትና ሊቃነ መላእክት ቅዱስ ሥጋዋን ለማሳረግ በታላቅ ምሥጋና ከሰማይ ወረዱ፤ አባቷ ዳዊት ከመሰንቆው ጋር ሙሴም የአገልግሎት ልብሱን ለብሶ፣ ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስም ወደ እርሷ መጡ ሥጋዋንም በወርቅ ማዕጠንት አጠኑ፡፡ ሱራፌልና ኪሩቤልም በላይዋ ክንፎቻቸውን ዘረጉ /ጋረዱ/፡፡ ከሰማያት ብርሃን የምስጋና መብረቅም ከደመናት ውስጥ ወጣ፡፡ ከምድር ወደ ሰማያት በምስጋና ከፍ ከፍ አለች ከልጇ ጋርም በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች” ማለት ነው፡፡ ይህም “በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች፡፡” መዝ.44፥9 ተብሎ የተነገረላትን ቃለ ትንቢት የተፈጸመላት መሆኑን ያመለክታል፡፡


ከሐዋርያት ወገን የሆነው ቅዱስ ቶማስ ለወንጌል አገልግሎት ሄዶ በወቅቱ አልነበረም፡፡ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሕንድ ሲመጣ ስታርግ አገኛት፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” ይላል፤ ተበሳጨ፡፡ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁኝ” አለ፡፡ በዚህ ጊዜ የልቡናን ሐዘን የምታቀል እመቤታችን፡- አይዞህ አትዘን እኒያ ትንሣኤዬን ዕርገቴን አላዩም፡፡ አንተ አይተሃል፡፡ ተነሣች፣ ዐረገች ብለህ ንገራቸው፡፡” ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡


ከዚህ በኋላ ሄዶ፤ “የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?” አላቸው “ሥጋዋን አግኝተን ቀበርናት” አሉት፡፡ እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ተዉ ይህ ነገር አይመስለኝም” አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ እንጂ ልማድህ ነው፡፡ አንተ ብቻ ተጠራጥረህ አትቀርም፤ አንተ እየተጠራጠርህ ሰውን ሁሉ ስታጠራጥር ትኖራለህ” አለው፡፡ እርሱም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ ይሰማቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ ተቆጥቶ ሂዶ መቃብሩን ቢከፍተው የእመቤታችን ሥጋዋን አጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ደንግጦ ቆመ፡፡ ይህን ጊዜ ቅዱስ ቶማስ “አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሣች ዐረገች” አላቸው፡፡


a ergete mariam 2006 2 ቅዱስ ቶማስ የያዘውንም ሰበን እያሳያቸው፡- “ቅዱስ ሥጋዋን የገነዛችሁበት ጨርቅ /ሰበን/ ይህ አይደለምን” ብሎ ሰበኑን ሰጣቸው፡፡ ይህንንም ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ ከዚህ በኋላ በዓመቱ “ቶማስ ትንሣኤሽን ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ በማለት ጾም ጀመሩ፡፡


በ16ኛው ቀን አምልካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ እመቤታችንን መንበር ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ ቄስ፣ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ራሱ ቀድሶ አቁርቧቸዋል፡፡ሐዋርያት ከዚህ በኋላ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በብቃት ለመወጣት ቻሉ፡፡ ይህንን ዐቢይ ምሥጢር አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ተንሥአ እግዚኦ” ውስተ ዕረፍትከ፡፡ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” /መዝ.131፡8/፡፡


“ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” /መዝ.44፡9/ ሲል በ ቅዱስ ዳዊት የተናገረው ቃለ ትንቢት በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና የጸናች የቅድስት ድንግል እመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ እንዲሁም ፍለሰት /ዕርገት/ በምሥጢር ከማሳየቱም ሌላ ወላዲተ አምላክ በልጇ በወዳጇ በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት በክብርመኖሯንም ያስረዳል /ራእ.11፡19/፡፡

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1542--1318

Add comment


Security code
Refresh