ማኅበረ ቅዱሳን በጀርመን ዐውደ ርእይ አካሔደ።
- Details
- Created on Wednesday, 20 August 2014 00:17
- Written by ቀዳሚ ገጽ
ነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም.
በጀርመን ቀጠና ማእክል
በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ሐምሌ 26 እና 27 2006 ዓ.ም በጀርመን ካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ያሉበትን ሁኔታ፣ የማኅበረ ቅዱሳንን ታሪክ፣ አገልግሎትና በየጊዜው ያጋጠሙትን ችግሮች እንዲሁም የቤተክርስቲያን አገልግሎት በአውሮፓ በተለይም በጀርመን ያለበትን ሁኔታ፣ የአመሠራረት ታሪከ እና መንፈሳዊ እንቅስቃሴ የሚያስቃኝ ዐውደ ርእይ ተካሔደ።
ዐውደ ርእዩ በካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ በመጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርምያስ ተከፍቷል። ምእመናን ዐውደ ርእዩን ከተመለከቱ በኋላ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን አመሠራረት፣ ገዳማትና የአብነት ትምህር ቤቶችን ለመደገፍ እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ በቂ መረጃ ማግኘታቸውን ገልጠው የማኅበሩን አገልግሎት ለመደገፍ ፍላጎት እንደላቸው ገልጸዋል። መጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርምያስ በበኩላቸው ራሳቸው ያለፉበት የአብነት ትምህርት ቤት ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለሀገር ያበረከቱት አስተዋጽኦ ተመልካች ሊረዳው በሚችል መልኩ መቅረቡን አድንቀው ማእከሉ ዐውደ ርእዩን በደብሩ ስላካሔደ በስበካ ጉባኤው ስም ምሥጋና አቅርበዋል፤ የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት የቤተክርስቲያን አገልግሎት በመሆኑ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል::
ዐውደ ርእዩ ነሐሴ 3 እና 4 ቀን 2006 ዓ.ም በኮሎኝ ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ላይ በአጥቢያው ሰበካ ጉባኤና በሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሓላፊ ፈቃድ ለምእመናን ለመታየት በቅቷል። ዐውደ ርእዩን የከፈቱት ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርዓዊ ተበጀ ሲሆኑ በዕለቱ የቀረበው ዐውደ ርእይ ጥንታዊ ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ያሉበትን ሁኔታ ምእመናን እንዲረዱት የሚያደርግ በመሆኑ ማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእዩን በዚህ ቤተክርስቲያን ማካሔዱ ያስደሰታቸው መሆኑን ተናግረዋል። በመቀጠልም የድጓ እና የአቋቋም መምህር የሆኑት እና ከካርል ስሩህ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን የመጡት ሊቀ ጠበብት ተክሌ ሲራክ ስለአብነት ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት እና በአሁኑ ወቀት ተማሪዎች ስላሉባቸው ቸግሮች ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት አባቶች፣ ምእመናንና ማኅበራት ሊያደርጓቸው ይገባል ያሏቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች ጠቁመዋል::
በኮሎኝ ደ/ሰ/ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሚገኙ ምእመናን ዐውደ ርእዩን ከተከታተሉ በኋላ ማኅበረ ቅዱሳን በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ሥራ መሥራቱን የሚያሳይ መረጃ ሳያገኙ የቆዩ መሆናቸውን ገልጸው ወደ ፊት ግን ከማኅበሩ ጋር በመተባበር በጋራ ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶችን ለመርዳት ቃል ገብተዋል። ዐውደ ርእዩ ለሁለት ቀናት ክፍት ሆኖ በምእመናን የተጎበኘ ሲሆን ከ150 በላይ የሚሆኑ የአጥቢያው ምእመናን እንደጎበኙት የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ በነበሩ አንዳንድ ክፍተቶች ማኅበረ ቅዱሳን በአጥቢያው ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሳያደርግ የቆየ ቢሆንም ከዚህ በኋላ ግን በአዲስ መልክ ከደብሩ አስተዳዳሪ፣ ከሰበካ ጉባኤው እንዲሁም ከምእመናን ጋር ለመሥራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል። ከዚህ በፊት በማኅበሩ ላይ ቅሬታ የነበራቸው ምእመናንም ከዐውደ ርእዩ በኋላ ጥያቄና አስተያየት አቅርበው በቂ ማብራሪያና ምላሽ በማግኘታቸው በቀጣይ ከማኅበሩ ጋር ለመሥራት በጎ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ተመሳሳይ የዐውደ ርእይ ዝግጅቶች በግሪክ አቴንስና በቤልጂየም ብራስልስ አብያተ ክርስቲያናት የሚካሔድ መሆኑ ተጠቅሷል።
Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1541-2014-08-20-06-27-36