ጳጉሜን

ጳጉሜን 2/2006

ጳጉሜን ጭማሪ፣ ተወሳክ፣ አምስት ቀን ተሩብ” የሚል ትርጉም አለው፡፡ ጳጉሜን 13ኛ ወር ትባል እንጂ በውስጧ የያዘቻቸው ቀናት ቁጥር በአንድ ሳምንት ካሉ ቀናት ያነሱ ናቸው፡፡ ወርኀ ጳጉሜን የክረምቱ ጨለማ ሊያከትም ብርሃን ሊበራ የተቃረበበት በመሆኑ ፀዓተ ክረምት፤ የክረምት መውጫ ዘመን ትባላለች ፡፡ይህ ወቅት በሐምሌና በነሐሴ ደመና ተሸፍና የነበረችው ፀሐይ መውጫዋ የደረሰበት ጊዜ በመሆኑ ብርሃን፣ መዓልተ ነግህ፣ ጎህ ጽባህ ተብሎ ይጠራል፡፡

 

ወርኀ ጳጉሜን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ ከሌሎች ወራት ገዝፋና ጎልታ ትታያለች በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ወርኀ ጳጉሜን በጾምና በጸሎት /በሱባኤ/ ያሳልፏታል፡፡ ፡፡የጌታችን ምጽአት የሚታሰብባት በመሆኗ የሚዘመረው መዝሙር፣ የሚነበቡ ምንባባት ይህንኑ የሚገልጹ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከመ እንተ መብረቅ ዘይወፅእ እምጽባሕ ወያስተርኢ እስከ አረብ ከማሁ ምጽአቱ ለወልደ እግዚአብሔር ምስለ ኀይለ ሰማያት በንጥረ መባርቅት ምስለ አእላፍ መላእክት ወኲሎሙ ሊቃነ መላእክት አክሊለ አክሊላት ዲበ ርእሶሙ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንዲታይ በመባርቅት ፍጥነት፡ - ሰማያውያን ኀይላት ከብዙ መላእክትና የመላእክት አለቆች ጋር በካህናት ራስ ላይ ያሉት አክሊሎች መገኛ የሆነው የሾህ አክሊል ደፍቶ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሁ ይመጣል” እንዲል፡፡

 

ጳጉሜን ጳጉሜን 3 ቀን በቅዱስ ሩፋኤል ዕለት ሰማያት የሚከፈቱበት /ተርኅዎ ሰማይ/ መሆኑን በማመን ምእመናን ወደ ጸበልና አፍላጋት በመሄድና በጳጉሜን ቀናት በሚዘንበው ዝናብ በመጠመቅ በረከት ያገኛሉ ፡፡ ይህ ወቅት በሊቀ መልእክት ቅዱስ ሩፋኤል እጅ የጦቢያን ዓይን እንዳበራ የምእመናን ዓይነ ልቡና እግዚአብሔር እንዲያበራ ይጸለያል፡፡ በቤተ ክርስቲያንም ወቅቱ ይበሰራል፡፡


በየዓመቱ ጳጉሜን ሦስት ቀን የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በዓልም በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት፣ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ይህም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ከከበሩት ቅዱሳን መላእክት ሦስተኛው ነው፡፡ መጽሐፍ፡- “ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል፡፡ /ጦቢት 12፥15/ ሩፋኤል የሚለው የስሙ ትርጓሜ ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ ማለት ነው፡፡


ቅዱስ ሩፋኤል መልአከ ጥኢና ወሰላም የሰላምና የጤና መልአክ ይባላል፡፡ በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ሆነ ቁስል ይፈወስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ “በሰው ቁስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” መጽሐፈ ሄኖክ 6፥3 ፡፡ የሰው ልጆች ከተያዙበት የኀጢአት ቁስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የማይለይ መልአክ ነው፡፡ “በበሽታ ሁሉ ላይ በሰው ልጆችም ቁስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡” በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል፡፡ /ሄኖክ.10፥13/


ለሴቶች ረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ በማኅፀን ላለ ችግር ፣ሴት በፀነሰችበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም፡፡ ሕፃኑ ዐርባ ቀን ሞልቶት፣ በማሕፀን እያለ “ተስእሎተ መልክዕ” /በሥላሴ አርአያ መልኩ መሳል ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ/ ቅዱስ ሩፋኤል አይለየውም፡፡ በመውለጃቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀላል፡፡


ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነት ያለን ረቂቅ ርኩስ መንፈስ ያውቃል፡፡ አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በወለተ ራጉኤል ጭን ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሰቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል /ጦቢት.3፥8-17/፡፡


ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን፣ አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው” /ሄኖክ 3፥5-7/ በዚህ መሠረት ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ /ሄኖክ፤2፥18/

 

የጦቢትን ልጁ ጦቢያን በሰው አምሳል ተገልጦ ከተራዳው በኋላ ወደ ሰማይ በሚያርግበት ጊዜ ራሱን ሲገልጥ “የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ አላቸው” /ጦቢት.12፥15/፡፡

 

የዘመናት ጌታ እግዚአብሔር መልካም ዘመን ያሳየን የቅዱስ ሩፋኤል አማላጅነት አይለየን፡፡

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1553-2014-09-07-08-26-00