የሰሜን አሜሪካ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ 14ኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ
- Details
- Created on Friday, 12 September 2014 05:23
- Written by ቀዳሚ ገጽ
መስከረም 2 ቀን 2006 ዓ.ም.
ከሰሜን አሜሪካ ማእከል
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ 14ኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤውን በአትላንታ መካነ ሕይወት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ እና በደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ወአቡነ አረጋዊ አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ት/ቤቶች አዘጋጅነት ከነሐሴ 23 – 25/2006 ዓ/ም (August 29 – 31/2014) አካሄደ።
በተለያዩ የሰሜን አሜሪካ ግዛቶች ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የመጡ የሰንበት ት/ቤት አባላት እና ተጋባዥ እንግዶች አርብ ነሐሴ 23 ረፋዱ ላይ አትላንታ የገቡ ሲሆን፣ ምሽት ላይ የጉባኤው መክፈቻ የጸሎት መርሐ ግብር በመካነ ሕይወት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ቤ/ክ ተከናውኗል። የደብሩ አስተዳዳሪ መላከ ሕይወት ቀሲስ እርገተ ቃል እና የአዘጋጆቹ ሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ ለጉባኤው ተጋብዘው የተገኙት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ የእለቱን ትምህርት አስተምረዋል። በመቀጠል የአንድነት ጉባኤው ሰብሳቢ ዲ/ን ኄኖክ ተዘራ ስለ ቀጣይ ሁለት ቀናት የጉባኤው መርሐ ግብር አጠቃላይ ገለጻ ሰጥተው የእለቱ መርሐ ግብር ተጠናቋል።
ቅዳሜ ነሐሴ 24 ጠዋት መርሐ ግብሩ በጸሎት ከተጀመረ በኋላ ለጉባኤው ከሜኒያፖሊስ ፣ ሜኒሶታ ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ ተጋብዘው የተገኙት መምህር ቀሲስ ስንታየሁ ወጣቶችን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚያነቃ እና የሚያንጽ ትምህርተ ወንጌል አስተላልፈዋል፡፡
በመቀጠልም የአንድነት ጉባኤው ሥራ አመራር እና የሦስት ክፍለ ግዛቶች የ2006 ዓ/ም የሥራ እንቅስቃሴ ጠቅላላ ሪፖርት እና ውይይት ተካሂዷል። ከቀረቡት ሪፖርቶች መካከል አንድነት ጉባኤው ከሰሜን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት እና ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ ጋር ያለው የጠነከረ ግንኙነት ወደፊት አንድነት ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ አገልግሎቱን እንዲያካሂድ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዳላቸው ያመለክታል።
በኢትዮጵያ ጎንደር ቤዛዊት ማርያም እና ደብረ ዘይት ደብረ መጽሔት ቅ/ኪዳነ ምሕረት ሰንበት ት/ቤቶች በ2006 ዓ/ም ያደረገው የ$8000.00 (ስምንት ሺህ ዶላር) እርዳታ አባላቱ የበለጠ ለአገልግሎት እንዲተጉ መነሳሳትን ፈጥሯል። በመቀጠልም ከሰባቱ የአንድነት ጉባኤው ክፍለ ግዛት መካከል በሰሜን ምዕራብ ክፍለ ግዛት ትምህርታዊ ጉባኤ ላይ ከቀረቡ ዝግጅቶች መካከል “የምንፈልገውን ወይስ የሚያስፈልገንን” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የምልከታ ጽሑፍ በዲ/ን ዳዊት ብርሃኑ አማካይነት ቀርቧል።
ከሰዓት በኋላ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ጥልቅ ምሥጢር ያለው ትምህርተ ወንጌል ካስተላለፉ በኋላ በዲሲ እና አካባቢው የሚገኙ “መስማት የተሳናቸው” ወንድሞች እና እህቶች በአይነቱ ልዩ የሆነ ዝግጅት አቅርበዋል። የቀረበው ዝግጅት መስማት የተሳናቸው ወገኖች ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ስላላቸው ትጋት፣ ከምእመናን እና ከቤተ ክርስቲያን አካላት ሊደረግላቸው ስለሚገባ ድጋፍ እና የወደፊት እቅዳቸውን የሚገልጽ ነበር።
የአንድነት ጉባኤው የ2007 ዓ ም በጀት ዓመት ዕቅድ እና ውይይት ከተካሄደ በኋላ “በክርስትና የሚገኝ ተስፋ” በሚል ርዕስ መላከ ሰላም ቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል። ጥናታዊ ጽሑፉ ቤተ ክርስቲያን ያሳለፈችውን ፈተናዎች፣ በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያናችን ያለችበትን ሁኔታ፣ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ያለፉበት እና አሁን ያሉባቸው ፈታናዎች፣ እንዲሁም በዚህ ሁሉ ፈተና መካከል ስላለ ክርስቲያናዊ ተስፋ የዳሰሰ ነበር። ከጥናታዊ ጽሑፉ በኋላ የሲያትል ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ የፍኖተ ሰላም ሰንበት ት/ቤት አባላት ልዩ ያሬዳዊ ጣዕመ ዜማ አቅርበዋል።
አብዛኛው የአንድነት ጉባኤው አባላት የተሳተፉበትና ሰፊ ውይይት የተካሄደበት የአንድነት ጉባኤው ሥልታዊ ዕቅድ (ከ2008 – 2012) መነሻ ሃሳብ በዲ/ን ብዙአየሁ ልመንህ ቀርቦ አባላቱ ለረጅም ሰዓታት በስድስት መሪ ነጥቦች ላይ ውይይት አካሂደዋል። ከአባላቱ የተሰበሰቡትን ሃሳቦች አጠቃሎ የያዘ የ4 ዓመት ሥልታዊ እቅድ በሚቀጥለው ዓመት (በ15ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ) እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።
ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የሚያገለግሉ የአንድነት ጉባኤው ሥራ አመራር አባላት አስመራጭ ኮሚቴ ከተመረጠ በኃላ ከ13ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ጀምሮ በጉጉት የሚጠበቀው በሰንበት ት/ቤቶች መካከል ከፍተኛ መንፈሳዊ ፉክክር የሚታይበት በአንድነት ጉባኤው የ14 ዓመት የጉዞ ሂደት ላይ ያተኮረ፣ ስለደንቡ ፣ መመሪያው እና ልዩ ልዩ ታሪኮች ዙሪያ የተዘጋጀ የጥያቄ እና መልስ ውድድር በቤካ መገርሳ መሪነት ተከናውኖ የዕለቱ መርሐ ግብር በጸሎት ተጠናቋል።
እሁድ ጠዋት የአንድነት ጉባኤው አባላት አትላንታ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ቅዳሴ ከተሳተፉ በኋላ የከሰዓቱ መርሐ ግብር አዘጋጆቹ ሰንበት ት/ቤቶች ለዓመታዊ ጉባኤው በሚገባ እንደተዘጋጁበት በሚያሳይ የምሳ መስተንግዶ ተጀምሯል። በማስከተልም “ቤተ ክርስቲያን እና ቴክኖሎጂ” በሚል ርዕስ አሁን ያለው የቴክኖሎጂ ምጥቀት እና ቤተ ክርስቲያናችን ልትጠቀምባቸው ስለሚገባ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሰፊ ጥናታዊ ዝግጅት በዲ/ን ዮሴፍ አዱኛ ቀርቧል። ዝግጅቱ የቴክኖሎጂን ጥቅም እና ጉዳት፣ በአንድነት ጉባኤው እስካሁን የተሰሩ እና ሊተገበሩ ስለሚገቡ ሥራዎች በስፋት ተገልጿል። የወደፊቱንም ሥራ ሊያግዙ የሚችሉ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር የተገናኘ ሙያ ያላቸው ሰባት የአንድነት ጉባኤው አባላትም ተመርጠዋል። ዲ/ን ዮሴፍ አዱኛ የ debelo.org የአብነት ትምህርት ቤት ድረ-ገጽ አዘጋጅ ናቸው።
ከጥናታዊ ዝግጅቱ በኋላ የቀጣይ ሁለት ዓመታት የአንድነት ጉባኤው ሥራ አመራር አባላት ምርጫ ተካሂዶ የአትላንታ እና አካባቢው ሰ/ት/ቤት አባላት የመድረክ መዝሙር አቅርበዋል። በመቀጠልም ከማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል እና ከማኅበረ ባለ ወልድ በሰሜን አሜሪካ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ቀርቧል፡፡
ከዓመታዊ የሀገረ ስብከት ስብሰባ ቆይታ በኋላ በዓመታዊ ጉባኤው ላይ ለመገኘት ቅዳሜ ምሽት አትላንታ የገቡት የዲሲ እና ካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ከአትላንታ ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ የተክለ ሃይማኖት በዓለ ንግስ በኋላ አትላንታ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ጋር በመሆን እሁድ ከሰዓት በኋላ በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል። ብፅዕነታቸው ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ለተመረጡት የሥራ አመራር አባላት ጸሎት ካደረጉ በኋላ ቃለ ቡራኬ አስተላልፈዋል። አንድነት ጉባኤው አገልግሎቱን አጠናከሮ መቀጠል እንደሚገባው፣ ወጣቱ ወደፊት ብዙ አገልግሎት እንደሚጠብቀው እና ሁል ጊዜ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ እንደሚገባው አባታዊ ምክርና ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል።
በ2006 ዓ/ም ለአንድነት ጉባኤው አገልግሎት መሳካት ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ እና በበዓሉ ላይ ለሚቀርቡ ዝግጅቶች ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን ላበረከቱ አባቶች፣ ሰንበት ት/ቤቶች፣ ወንድሞች፣ እና እህቶች የማበረታቻ የምስክር ወረቀት ከብፅዕነታቸው እንዲቀበሉ ተደርጓል።
የእለቱን የማጠቃለያ መርሐ ግብር ታሪካዊ ካደረጉት ዝግጅቶች አንዱ የሆነው በኢትዮጵያውያን ሰዓሊያን የተሳለ የቅዱስ ያሬድ ስዕል በአንድነት ጉባኤው ልማት ክፍል አማካይነት ለጨረታ ቀርቦ ለጉባኤው የመጡ ሰ/ት/ቤቶች ከፍተኛ ፉክክር አድርገውበታል፡፡ በመጨረሻም መስማት የተሳናቸው ወንድሞች እና እህቶች አሸንፈዋል።
በዕለቱም በአብርሃም ሰሞሎን እና በቤዛ ኃይሉ የተዘጋጁ መንፈሳዊ ግጥሞች የዝግጅቱ አካላት ነበሩ። ዲ/ን ዳዊት ፋንታዬ፣ ጋሻው ታደሰ እና ሲሳይ ደንቦባ የሁለቱን ቀናት መርሐ ግብር በመምራት ዓመታዊ ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ አድርገዋል። በጉባኤው በተገኙ ዘማርያን እና አጠቃላይ አባላት በአንድነት በመሆን መዝሙር ከተዘመረ በኋላ የዓመታዊ ጉባኤው መርሐ ግብር በጸሎት ተፈጽሟል።
ሰኞ እለት አትላንታ የነበሩ ወንድሞች እና እህቶች በአትላንታ ሊጎበኙ የሚችሉ ታሪካዊ ቦታዎችን ሲጎበኙ አርፍደው ወደ ምሽት ላይ በመካነ ሕይወት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ በተዘጋጀው ልዩ የእራት እና አዝናኝ የውይይት መርሐ ግብር ላይ አምሽተዋል።
የመካነ ሕይወት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ እና የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ወነቡነ አረጋዊ ቤ/ክ ሰንበት ት/ቤት ካህናት፣ ሰበካ ጉባኤ እና ሰንበት ት/ቤት አባላት መስተንግዷቸው፣ ፍቅራቸው እና ለጉባኤው መሳካት ያደረጉት ልዩ ጥረት ፍጹም ከልብ የማይጠፋና ዘወትር በጉባኤው ተሳታፊዎች ሲታሰብ የሚኖር ነው።
እግዚአብሔር ቢፈቅድ 15ኛው ጠቅላላ ጉባኤ በዳላስ ቴክሳስ ፣ 16ኛው ጉባኤ ደግሞ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል።