የማቴዎስ ወንጌል

መስከረም 6 ቀን 2007 ዓ.ም.


ምዕራፍ 8


በማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ ስምንት ላይ የሚከተሉትን ነገሮች እናገኛለን፡፡ እነዚህም በተአምራቱ ከደዌ ሥጋ በትምህርቱ ደግሞ ከደዌ ነፍስ መፈወሱን የሚገልጡ ናቸው፡፡

  1. ለምጻሙን ስለ መፈወሱ፤

  2. የመቶ አለቃውን ብላቴና ስለመፈወሱ፤

  3. የስምዖን ጴጥሮስን አማት ስለ መፈወሱ እና አጋንንት ያደረባቸውን ስለማዳኑ፤

  4. “ለሰው ልጅ ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” ስለማለቱ፤

  5. ነፋሱንና ባሕሩን ስለ መገሰጹ፤

  6. በጌርጌሴኖን ሁለቱን ሰዎች፣ ከአጋንንት ቁራኝነት ስለ ማላቀቁ፤

1ኛ. ለምጻሙን ስለ መፈወሱ

ጌታችን ከአንቀጸ ብፁዐን ጀምሮ በዓለት እና በአሸዋ ላይ እስከ ተሠራው ቤት ድረስ ያለውን የአንድ ቀን ትምህርት ካስተማረ በኋላ ጉባኤው ተፈትቶ ከተራራው ሲወርድ ብዙ ሕዝብ ተከተለው፡፡ የተከተሉትም ቢራቡ ስለሚመግባቸው፣ ቢታመሙ ስለሚፈውሳቸው፣ ቢሞቱም ስለሚያስነሣቸው ነው፡፡ ከሕዝቡም መካከል አንድ ለምጻም ስው ቀርቦ እየሰገደለት “ጌታ ሆይ ብትወድስ ልታነጻኝ ይቻልሃል” አለው፡፡ ጌታችንም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰው፡፡ መዳሰሱም በሁለንተናው ሕይወት እንደ ሆነ፣ ምትሐት እንዳይደለ እና ኦሪትን እንዳሳለፉት ለማጠየቅ ነው፡፡ ምክንያቱም በኦሪቱ ለምጽ የርኩሰት ምልክት በመሆኑ ለምጻም አይዳሰስም ነበርና፡፡ ዘሌ.13፣ ዘኁ.12፡10፣ 2ኛ ዜና.26፡16-23፣ ከዳሰሰውም በኋላ “እወዳለሁ ንጻ” አለው፡፡ ወዲያውም ከለምጹ ነጻ፡፡ ጌታችን በሐልዮ ፈውሶ በነቢብ አዳነው፡፡


በመጨረሻም “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፡፡ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፣ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባዕ አቅርብ” አለው፡፡ ጌታችን “ለማንም እንዳትናገር እወቅ” ማለቱ ለአብነት ነው፡፡ ነገ ተነገወዲያ እኛ የሠራነውን ሥራ ሁሉ ሰው ካላወቀልን እንዳንል እና ውዳሴ ከንቱን ሸሽተን እንድንኖር ነው፡፡ “ራስህን ለካህን አሳይ፣ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን” ማለቱ ደግሞ ለመፈራረጃ እንዲሆንባቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ከለምጹ የነጻውን አይተው መባውን ባይበሉ ኖሮ “የሆነውንም ያልሆነውንም ለምጻም አዳንኩ እያለ ምኩራባችንን ቢያሳድፍብን ከሞቱ ገባንበት፤” ባሉ ነበርና ነው፡፡


በኦሪቱ ፍጹም ለምጻም ለሆነ ሰው ሥርዓት ይሠሩበታል፤ አትከናነብ፣ አፍህን ሸፍን ወገብህን አትታጠቅ፣ ጫማ አታድርግ ይሉታል፡፡ አትከናነብ ማለታቸው፡- ለጊዜው ደዌው በእስትንፋሱ ወደ ጤነኞቹ እንዳይተላለፍ ነው፤ ለፍጻሜው ግን ማስተማር አይገባህም ሲሉት ነው ኢሳ.6፡5፡፡ ወገብህን አትታጠቅ ማለታቸው፡- ለጊዜው ሰውነቱ ልህሉህ ስለሆነ እንዳይሰማው ነው፤ ለፍጻሜው ግን ንጽሕና የለህም ሲሉት ነው፡፡


ጫማ አታድርግ ማለታቸው ደግሞ ምግባር የለህም ሲሉት ነው፡፡ ጌታችን ከተራራው መውረዱ ከልዕልና ወደ ትሕትና ማለትም ከሰማየ ሰማያት ለመውረዱና ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፈስ ነሥቶ ለመወለዱ ምሳሌ ነው፤ ለምጻሙም በኃጢአት ለምጽ ለተመታ ለአዳም ምሳሌ ነው፡፡ ለምጻሙ “ብትወድስ ከለምጼ ልታነጻኝ ትችላለህ” ማለቱ አዳም እግዚአብሔርን “ፈቃድህስ ከሆነ ከፍዳ እና ከመርገም ልታድነኝ ይቻልሃል” የማለቱ ምሳሌ ነው፡፡ ጌታ እጁን ዘርግቶ ለምጻሙን ማንጻቱ ደግሞ በቀራንዮ በመስቀል ላይ እጁን ዘርግቶ በመስቀል አዳምን ከፍዳ እና ከመርገም የማዳኑ ምሳሌ ነው፡፡

 

ከዚህም ሌላ “ለማንም አትናገር ራስህን ለካህን አሳይ” ማለት ኃጢአትህን ለማንም ለማን አትናገር ለንስሐ አባትህ ንገር እንጂ ማለት ነው፡፡ “ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ” ማለትም ካህኑ ያዘዘህን ቀኖና ስግደትም ሆነ ጾም ፈጽም ማለት ነው፡ “ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን” ማለት ደግሞ ለኢተነሳሕያን ማለትም ንስሐ ለማይገቡ ሰዎች መፈራረጃ ይሆንባቸው ዘንድ ማለት ነው፡፡ እኛም ከኃጢአት ለምጽ እንድንፈወስ ንስሐ እንግባ፡፡ ሥርየተ ኃጢአትን እንድናገኝ ንስሐ ካልገባን ግን ልዕልና ሃይማኖት አይኖረንም፡፡ የተሸፈነ አፋችንን መግለጥ ማለትም ቃሉን ማስተማር አንችልም፡፡ ወገባችንን ልንታጠቅ ማለትም ንጽሕናን ገንዘብ ለማድረግ አንችልም፡፡ ጌታችን በወንጌል “ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን” ያለው ንጽሕናን ገንዘብ አድርገን በጎ ሥራ እንድንሠራ ነው፡፡ ሉቃ.12፡35፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም “ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁ እና በመጠን ኖራችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ተስፋ አድርጉ” ብሏል፡፡ 1ኛ ጴጥ.1፡13፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ጫማ ልናደርግ ማለትም ምግባረ ወንጌልን ልንሠራ በሕገ ወንጌልም ልንጸና አንችልም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን “እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤” ሲል መክሮናል ኤፌ.6፡14-15፡፡


2ኛ. የመቶ አለቃውን ብላቴና ስለመፈወሱ፤

ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃው ወደ እርሱ ቀርቦ “ጌታ ሆይ ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሰቃየ በቤት ተኝቷል፤ አንድም ደዌ ጸንቶበት ከቤተ ሕሙማን ተኝቷል፤” አለው፡፡ በሀገራቸው የደውያን ቤት አንድ ነው፡፡ ይኸውም ስለ ሦስት ነገር ነው፡፡ 1. ለባለጸጋው የመጣው ምግብ ለድሃው እንዲተርፈው፣ 2. ደዌ ከሕሙማን ወደ ሕያዋን እንዳይተላለፍ፤ 3. ያልጸናበት የጸናበትን አይቶ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግን ነው፡፡


ጌታችንም “እኔ መጥቼ አድነዋለሁ፤” አለው፡፡ የመቶ አለቃው ግን “ጌታ ሆይ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፤ እኔም አንተን ለመቀበል የበቃሁ ሰው አይደለሁም፤ ቃል ብቻ ተናገር፣ ብላቴናዬም ይፈወሳል፡፡ እኔም እኮ እንዳቅሜ ገዥ ነኝ፣ በስሬ የምገዛቸው ጭፍሮች አሉኝ፡፡ ደጅ ሲጠና የሰነበተውን ሂደህ እረፍ ስለው ይሄዳል፡፡ አርፎ የሰነበተውን ደግሞ መጥተህ ደጅ ጥናኝ ስለው ይመጣል፡፡ አገልጋዬንም የቆመውን ቁረጥ የተኛውን ፍለጥ ብለው ያዘዝሁትን ሁሉ ያደርጋል፡፡ ደዌያትስ ባንተ ዘንድ ምን ቁም ነገር ናቸው ግቡ ብትላቸው የሚገቡ፣ ውጡ ብትላቸውስ የሚወጡ አይደሉምን” ሲል መለሰ፡፡ ጌታችንም ይህን ሰምቶ አደነቀ፡፡ ያደነቀውም ሦስት ነገር አግኝቶበት ነው፡፡ እነዚህም ሃይማኖት ጥበብና ትሕትና ናቸው፡፡ መቶ አለቃው ጌታ ያድንልኛል ብሎ መምጣቱ ሃይማኖት፣ ምሳሌ መስሎ መናገሩ ጥበብ፣ አይገባኝም ማለቱ ደግሞ ትሕትና ነው፡፡


ጌታችን ወደ ቅፍርናሆም ገባ የሚለው ቃል ከልዕለና ወደ ትሕትና መምጣቱን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ መወለዱን የሚያጠይቅ ነው፡፡ መቶ አለቃው ለአዳም ምሳሌ ሲሆን በሽተኛው ደግሞ ለነፍሱ ምሳሌ ነው፡፡ በበሽተኛው ላይ ደዌ እንደጸናበት፣ የአዳምም ነፍስ ፍዳ ጸንቶበት፣ የአዳምም ነፍስ ፍዳ ጸንቶባት ነበረና ነው፡፡ መቶ አለቃው “ብላቴናዬን አድንልኝ” ማለቱ አዳም “ከፍዳ ነፍስ አድነኝ” ለማለቱ ምሳሌ ነው፡፡ ቤተሕሙማንም ለቤተኃጥአን ለሲዖል ምሳሌ ነች፡፡

ይቆየን

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 4ኛ ዓመት ሰኔ 1989 ዓ.ም.

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/---mainmenu-27/1558-2014-09-16-11-53-22