በመስቀል በዓል መጨመር ወይም መቀነስ የሌለበት የትኛው ነው?

 መስከረም 20 ቀን 2006 ዓ.ም.


በዲ/ን ፍቃዱ ዓለሙ


meskel 001 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ታሪካዊት እንደ መሆኗ፣ ሁሉም ሃይማታዊ በዓላት ከመንፈሳዊ ባህላዊ ሥርዓቶች ጋር ተሣሥረው እንዲከበሩ መሠረት ናት፡፡ ለዚህ ነው ከሀገራዊና ከሃይማታዊ በዓላት ጋር ተያይዘው የሚከናወኑት መንፈሳዊና ባሕላዊ ሥርዓቶች ምንጫቸው/መነሻቸው/ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ናት የምንለው፡፡ ቀድሞም በኦሪቱ በኋላም በሐዲሱ ሕግጋት ጸንታ የቆየች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ ተዟዙራ አስተምራለች፡፡ ለመስቀሉም ሆነ ለሌሎች ሃይማታዊ በዓላት መነሻቸው የቀደሙት አባቶቻችን ከ4ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የዘሩት የወንጌል ዘር ነው፡፡


ለዕንቁጣጣሽ (ዐዲስ ዓመት)፣ ለልደት፣ ለጥምቀት እና ለፋሲካ በዓላት ብቻ ሳይሆን ለመስቀል በዓልም ባህላዊ መሠረቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የመስቀል በዓልን የተመለከትን እንደሆነ በሰሜኑ፣ በደቡቡ፣ በምሥራቁ፣ የሀገራችን ክፍሎች የሚከናወኑት ማናቸውም ባህላዊ ሥርዓቶች መሠረታቸው ፍጹም ሃይማኖታዊ ነው፡፡ ይህም ከላይ እንደተገለጠው የቀድሞ አባቶቻችን በዐራቱም የኢትዮጵያ መዓዝናት እየተዘዋወሩ ወንጌልን የመስበካቸው ውጤት ነው፡፡


የመስቀል በዓል በማይታዩ ወይም በማይዳሰሱ ቅርሶች በዓለም አቀፍ ቅርስነት በዩኔስኮ ከተመዘገበ እነሆ አንድ ዓመት ሞላው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመሆን ይህን ሃይማኖታዊና ታሪካዊ በዓል በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ስታስመዘግብ ከዚህ በፊት በበዓሉ ላይ ሲከናወኑ የነበሩ ሃይማታዊና መንፈሳዊ ባህላዊ ሥርዓቶችን አካታ ነው፡፡ የቀነሰችው ወይም የጨመረችው አንዳችም ምዕራባዊ ባዕድ ነገር የለም፡፡


meskel 002 በዓሉን ስናከብርም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በማጉላት ሊሆን ይገባል፡፡ በስመ ዓለማቀፋዊነት ከሃይማኖታዊና ከባህላዊ ሥርዓቶች ውጭ ያሉትን እንደ ርችት መተኮስ፣ ጭፈራና ጩኸት ያሉ ሰርጎ ገብ ድርጊቶችን ወይም ልማዶችን መተው ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ድርጊቶች የበዓሉን ሃይማኖታዊ ይዘት ከመሸርሸራቸው ባለፈ የሀገራችንንም መልካም ገጽታ ስለሚያጎድፉ ነው፡፡


ባዕድ ልማዶችን ከመከላከል አንጻር ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ብዙ ይጠበቃል፡፡ በበዓሉ ቀን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ ሀገራችን የሚጎርፉ ቱሪስቶች /ጎብኝዎች/ የኛ የሆነውን ሥርዓት እንጂ እነርሱ የሰለቻቸውን ለማየት አይመጡምና ነው፡፡ ስለዚህ በዓሉን አስመልክቶ በሚቀርቡ ትርኢቶች ላይ የውጭው ዓለም የባሕል ተፅዕኖ እንዳያድርብን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡meskel 003


ይልቁንስ በብዙ ምእመናን ዘንድ የሚዘወተሩ ለምሳሌ የደመራውን አመድ በትእምርተ መስቀል አምሳል ግንባር ላይ መቀባት፣ ትርኳሹን ወደ ቤት መውሰድ፣ በዕለቱ ከወዳጅ ከዘመድ ጋር መሰባሰብን የመሳሰሉ ከእናት አባቶቻችን የወረስናቸው መንፈሳዊ ድርጊቶች ሊበረታቱና ሊቀጥሉ ይገባል፡፡


ለወደፊትም የበዓሉን ጥንታዊ፣ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ይዘት ሊያዳክሙ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች እንዳይከሰቱ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ የምንኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች እና ምእመናን እንደ ባለቤት በጋራ በመሆን ለመስቀል በዓል ሥርዓት መጠበቅ የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባናል፡፡ ባሕላዊው የበዓል አከባበር ሥርዓት ለሃይማታዊው የበዓል አከባበር ሥርዓት መገለጫ ነው እንጅ የሚጨመር ወይም የሚቀነስ ሥርዓት አይኖረውም፡፡

 

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1566-2014-10-01-05-49-19

Add comment


Security code
Refresh