ደብረ ጽጋጋ አቡነ አኖሬዎስ ገዳም
- Details
- Created on Tuesday, 24 September 2013 03:22
- Written by ቀዳሚ ገጽ
በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
የአቡነ አኖሬዎስ ገዳም ደሴ ዙሪያ በጽጋጋ የሚገኝ ሲሆን ከደሴ ወደ መካነ ሰላም በሚወስደው መንገድ በ12 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ገዳሙ የተመሠረተውም በ1317ዓ.ም በንጉሥ ዓምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት ሲሆን ግብፃዊው አቡነ ያዕቆብ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የደብረ ሊባኖሱን እጨጌ አቡነ ፊልጶስን አስጠርተው፤ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት “ኢትዮጵያ በአንድ ጳጳስ መወሰን የለባትም፡፡ ስለዚህ ዐሥራ ሁለት አበው መርጠን ክርስትና ይስፋፋ” ብለው ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት፤ አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ /ኤጲስ ቆጶስ/፣አቡነ አኖሬዎስ ዘሞረት፣አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋር፣ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘወረብ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፣ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ዘግድም፣ አቡነ መርቆሬዎስ ዘመርሐ ቤቴ፣ አቡነ አድኃኒ ዘዳሞት፣ አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል፣ አቡነ ኢዮስያስ ዘወጅ፣ አቡነ ዮሴፍ ዘእናርያን መርጠው ሀገረ ስብከት ተሰጥቷቸው ለሐዋርያዊ ተልእኮ ተሠማሩ፡፡
ዐሥራ ሁለቱን ንቡራነ ዕድ ለስብከተ ወንጌል በመላዋ አገሪቱ ሲሠማሩ፡፡ ለአቡነ አኖሬዎስ እንደ ግብጦን የተባለ ቦታ ደረሳቸው፡፡ ይህም ቦታ ከግንደ በረት እስከ ባሌ ያለውን አገር ያካትታል፡፡ እርሳቸውም ሰባት ታቦታት ይዘው በመሔድ አብያተ ክርስቲያናት ተክለው ክርስትናን አስፋፉ፡፡ በአካባቢው ስብከተ ወንጌልን ካስፋፉ በኋላ ባርጋባን የተባለ የአካባቢው ሰው ደግነታቸውንና ትምህርታቸውን ተመልክቶ በጽጋጋ ገዳም እንዲመሠርቱ ጋበዛቸው፡፡ አቡነ አኖሬዎስም በጽጋጋ ገዳም መሠረቱ፡፡
አቡነ አኖሪዎስ ከምነና ሕይወታቸው በተጨማሪ በዜማ፣ በመጻሕፍት፣ በቅኔና በስብከት አዋቂነታቸው የተነሣ በገዳሙ የሚሰበሰቡት መነኮሳት ቁጥር በየቀኑ ይጨምር ነበር፡፡ ከትውልድ አካባቢያቸው፣ ከመጀመሪያ ሀገረ ስብከታቸው፤ ከእንደግብጦን (ባሌ አካባቢ ገዳማቸው እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን ቦታውን ለማረጋገጥ ጥልቅ ጥናት ይፈልጋል) ብዙዎች ወደዚያው ይመጡ ነበር፡፡
አቡነ አኖሬዎስ በጽጋጋ ገዳማቸው እያሉ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን የአባቱን ዕቁባት በማግባቱ እንደ ዮሐንስ መጥምቅ በመገሰጹ ምክንያት ታስሮ ወደ ወለቃ ተጋዙ፡፡ ንጉሡ ሲሞት ሠይፈ አርዕድ ነግሦ የተጋዙት በሙሉ እንዲመለሱ ዐወጀ፡፡ አቡነ አኖሬዎስም ወደ በኣታቸው ጽጋጋ ተመለሱ፡፡ አቡነ አኖሪዎስ በነገሥታቱ ፊት ቆመው የወንጌልን ሕግ በመመስከራቸው እየታሰሩ ምድረ ጸወን ወደምትባል አገር /ደቡብ ወሎ፣ ቦረና/ ዝዋይ ደሴ ገማስቄ ግድሞ (ባሌ አካባቢ) ወደ ተባለው አገር ተጋዙ፡፡ ለብዙ ዓመታት ገዳም መሥርተው ቆይተው ወደ ጥንት በኣታቸው ተመልሰው ጽጋጋ መጡ፡፡ በ1471ዓ.ም/ በጽጋጋ ገዳማቸው ዐረፉ፡፡ ዐጽማቸው ወረብ በተባለው አካባቢ እንዳረፈ የሚያስረዱ አባቶችም አሉ፡፡
ጽጋጋ ገዳመ አኖሪዎስ እስከ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ድረስ ብዙ መነኮሳት የነበሩበትና በዐፄ ዮሐንስ ከፍተኛ ድጋፍ ይደረግለት የነበረ ገዳም ነበር፡፡ ኋላ ግን ገዳሙ በቅዱሳኑ የሚገለገል ቢሆንም ለዓመታት ተዝግቶ ቆይቶ በ1990ዎቹ መጨረሻ እማሆይ አስካለ (ዘጋራ መደኃኒዓለም) ወደ ግሸን ማርያም ሲሄዱ የአቡነ አኖሪዎስ ገዳም በደሴ ዙሪያ እንደነበር ተነግሯቸው ቦታውን አይተውና አልቅሰው ገዳሙን መልሰው ለማቋቋም ወሰኑ፡፡ የጻድቁ ጸሎት ረድቷቸው በአሁኑ ሰዓት ገዳሙ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ በተለይ በደሴ ከተማ ክርስቲያኖች፣ በግሸን ማርያም ተጓዦች እንዲሁም ታቦተ አኖሪዎስጋ ሲደርሱ እየሰገዱ ዑደት በሚያደርጉ አጃቢ ፈረሰኞች መስከረም 18 ቀን የዕረፍታቸው በዓል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡
በጽጋጋ ገዳመ አኖሪዎስ በአሁኑ ሰዓት በርካታ ተአምራት በመደረጋቸውና በእማሆይ አስካለ ጥረት መናኞች እየበዙ ገዳሙም እየሰፋ ይገኛል፡፡
- ምንጭ፡- ገድለ አቡነ አኖሬዎስ፣ ገድለ ተክለ ሃይማኖት፣ የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች
Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1326-2013-09-24-09-24-54