ቅዱስ መስቀል ፍቅር ነው
- Details
- Created on Tuesday, 25 September 2012 03:18
- Written by ቀዳሚ ገጽ
መስከረም 14 ቀን 2007 ዓ.ም.
ወሶበ ርእዮሙ እግዚእ ኢየሱስ ለእሙ ወለረድኡ ዘያፈቅር ይቀውሙ፤ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወደውን ደቀ መዝሙርና እመቤታችንን ከእግረ መስቀል ቁመው ባያቸው ጊዜ፣ ወይቤላ ለእሙ ኦ ብእሲቶ ነዋ ወልድኪ፤ አንቺ ሆይ ልጅሽ ይርዳሽ ያጽናናሽ አላት፡፡ ውሉድኪ ሲል ነው በዮሐንስ እኛን ለርስዋ መስጠቱ ነውና፡፡ ወይቤሎ ለውእቱኒ ረድ ነያ እምከ፣ ደቀ መዝሙሩንም እነኋት እናትህ ታጽናህ አለው እምክሙ ሲል ነው፡፡ በዮሐንስ እርስዋን ለኛ መስጠቱ ነውና፡፡(ዮሐ. 19: 26-27)
የመስቀል በዓል ሲከበር ከትውፊታዊው ውብና ደማቅ አከባበር ባሻግር መሠረታዊ ትርጉሙን፣ የትመጣውን ከነ ኀይለ ቃሉ ጥቅሙን መረዳት ዋናው ጉዳይ መሆን ይገባዋል፡፡ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ልብዋ በመሰቀሉ ፍቅር የነደደ እሌኒ አምላኳ በመሰቀል እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተስሎ እንደ ኢየሩሳሌም ሴቶች ከድንግል ጋር ሆነው እነሆ እናታችሁ እንዳላቸው ሁሉ እሌኒም ከሦስት መቶ ዘመን በኋላ በረከቱን ታገኝ ዘንድ መስቀሉን ከተደበቀበት ለማውጣት ተነሣች፡፡ የመስቀሉን ማንነት የተረዳች ቅድስት እሌኒ እንዳሰበችው ተሳክቶላት፣ በመስቀሉ ተመክታ መስቀሉን ለዓለም ሁሉ ብርሃን ይሆን ዘንድ ከተቀበረበት እንዲወጣ አድርጋለች፤ በመስቀሉ የሚመካ አያፍርምና፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ”ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልኩበት ከጌታችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ” (ገላ. 6: 14) እንዲል፡፡ ገና ሳታገኘው በልብዋ እያሰበችው ሳለ ልጅዋ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በሰማይ ላይ የመስቀል ምልክት የተጻፈ ሆኖ ”በዚህ ምልክት ድል ታደርጋለህ” ተብሎ የአምላክ ፈቃድ ተገልጾለታል፡፡ ምክንያቱም ቅድስት እሌኒ በዘመኑዋ ሁሉ መስቀሉ በአይሁድ ክፉ ቅናትና ተንኮል ተሰውሮ በመኖሩ ሁል ጊዜ ስታዝን ስለኖረችና ከተሰወረበት ለማውጣት በብርቱ ምኞት ከትጋሃ ጸሎት ጋር ለአምላኳ ተስላ ስለነበር የድሉ ምሥራች በመስቀል ምልክት ኀይል ተገለጠ፡፡ ይህ ድል በዓለም ላሉ ክርስቲያኖች ሁሉ የድል ትምክህት ነበርና፡፡
በጊዜው የኢየሩሳልም ከተማ በሮማዊው ጥጦስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ70 ዓመት መጥፋት ተያይዞ ሮማውያን ክርስቲያኖችን እያጠፉ ስለነበር፤ በተለይ ዲዮቅልጢያኖስ በነገሠ ጊዜ ያወጣቸው አዋጆች፣ አብያተ ክርስቲያናት ይዘጉ የጣዖት ቤቶች ይከፈቱ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ይቃጠሉ፣ የቤተ ክርስቲያን ንብረት ይወረስ፣ ክርስቲያን የሆነ ከሥራ ይባረር፣ ክርስቲያኖች በደል ቢደርስባቸው በፍርድ እንዳይታይላቸው ወዘተ የሚሉ ነበሩ፡፡ ለቆስጠንጢኖስ በሰማይ ላይ የታየው የድል ምልክት መስቀል ከላይ የተጠቀሰው የግፍ አዋጅ የተጫናቸውን ክርስቲያኖች ሁሉ ነጻነትን ያጎናጸፈ ነው፡፡ ቆስጠንጢኖስ በሮም ግዛት ከርሱ ጋር በዙሪያው ነግሠው የነበሩትን ሌሎች የአሕዛብ ነገሥታት በመስቀሉ ኀይል አሸንፎ የጥፋት አዋጅን በነጻነት አዋጅ ሽሮ ከላይ በጠቀስነው የርኲሰት አዋጅ ተቃራኒ የምሥስራች ቃል የቤተ ክርስቲያንን ክብር ከመለሰ በኋላ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን ከግብር ነጻ እንድትሆንና ከመንግሥት ገቢ ድርሻ እንዲኖራት፣ ዕለተ እሑድ ክብረ በዓል ሆና እንዲከበር፣ ቤተ ክርስቲያን ከተናዘዙ የመውረስ መብት እንዲኖራት፣ ኤጲስ ቆጶሳት በክርስቲያኖች ላይ ሙሉ ዳኝነት በመሥጠት ቤተ ክርስቲያን ነጻነቷን አግኝታ እንድትኖር አድርጓት ነበር፡፡
ቅድስት እሌኒ ደግሞ በመስቀል ፍቅር ተስባ እንደ እመቤታችንና እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ቀራንዮ በማቅናት፣ ኪራኮስ በተባለው ሰው የእግዚአብሔር መልእክት
- ደመራ እንድታስደምር፣
- እጣን በደመራው እሳት ውስጥ እንድታስጨምር፣
- ጸሎተ ምህላ እንዲደርስ፣
- በደመራው ጭስ ስግደት ምልክት እንድታስቆፍር ተነግሯታል፡፡ በመሆኑም የተባለችውን በማከናወን የቦታውን ጥቆማ መስከረም 16 በደመራው ጭስ አመልካችነት ተረድታ የፍለጋው ቁፋሮ ከመስከረም 17 እስከ መጋቢት 10 ተከናውኖ መስቀሉን ለዓለም አብስራለች፡፡ ከዚያ ቀጥሎም ከመስቀሉ ተያያዥ የሆኑ ብዙ ተአምራዊ ሥራ እንደተደረገ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንረዳለን፡፡
አገራችንም የመስቀሉ ብርሃን ታሪክ ተካፋይ ናትና ግማደ መስቀሉም ወደ ኢትዮጵያ በአፄ ዳዊት ዘመን ከጌታችን የሾህ አክሊልና ሉቃስ ከሣላት ከእመቤታችን ሥእለ አድህኖ ጋር መስከረም 10 ቀን ገብቷል፤ በዚህም ቀን የተቀጸል ጽጌ በዓል ይከበራል፡፡ (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ አቡነ ጎርጎሪዎስ ካልዕ)
ከላይ ባጭሩ እንዳየነው የመስቀሉ ፍቅርን የተረዱ እንደ እሌኒ ያሉ መስቀሉን በልዩ ሁኔታ ያውም መሥዋዕትነትን በሚጠይቅ መልኩ አይሁድ ሦስት መቶ ዓመት ቆሻሻ በላዩ በመጣል ከሸሸጉበት ለማግኘት ለስድስት ወር እልክ አስጨራሽ የቁፋሮ ፍለጋ በኋላ በማግኘት ዛሬ እኛ በደስታ እንድንዋብበት ልዩ ሽልማት አድርገው አቆይተውልናል፡፡ በዚህ ወቅት የክርስትና ባለቤት ሆነን ክርስትናን የተረከብን ክርስቲያኖች ሁሉ ይህንን ጥልቅ ፍቅር ተረድተን ይሆን የምናከብረው? ወይስ ሌላውን ለማጀብ ይሆን? እዚህ ላይ ነው ወቅቱ የሚጠይቀንን የክርስትና ዋጋ ልብ ልንለው የሚገባን፡፡ አሁንም እስቲ ቆም ብለን እናስተውል፤ ምንአልባት የዚህ ዓለም አዚም አፍዝዞን በትክክል እንደ እነ ቅድስት እሌኒ በመስቀሉ ፍቅር ተስበን እዳልሆነ ወይም እንደሆን እንመርምር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይለናል ”... ሰዎች ሆይ በዐይኖቻችሁ ፊት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተስሎ ነበር ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” (ገላ. 3፥1) ቅዱስ ጳውሎስ ለእውነት እንዳትታዘዙ ሲል የመስቀሉን ፍቅርን እውነት ብሎታል፣ ከዚህ ዓለም እውነት የተለየ ሰማያዊ እውነት በሆነው የመስቀል ፍቅር ስር እመቤታችን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ቆመው ነበር፣ እነዲሁም ከዘመናት በኋላ ቅድስት እሌኒ ከሮም ወደ ኢየሩሳሌም በመስቀሉ ፍቅር ተስባ ሄዳ ነበር፣ ብዙዎቹ ቅዱሳን ልባቸው ቀራንዮ ነበር፣ ኢትዮጵያውያን በኅሊና ብቻ ሳይሆን በብዙ መከራ ቀራንዮን ለማየት እንደአሁኑ የአየር መጓጓዣ ሳይኖር የመስቀሉ ፍቅር እየመራቸው ተጉዘው ስእለታቸውን እንደ ቅድስት እሌኒ ይፈጽሙ ነበር፡፡
ያልተቻላቸው እዚያው ከሩቅ በበዓታቸው ሆነው ነገር ግን በመንፈስ ተጉዘው ቀራንዮን ዳሰው እንደ እመቤታችንና እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ከእነርሱ ጋር እንዳሉ ሆነው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደተሰቀለ ሆኖ ተስሎ በኅሊና ያዩታል፤ አንቺ ሆይ ልጅሽ ይርዳሽ ያጽናናሽ እንደ አላት እንደ ሰሙ ሆነው በመንፈስ ይሰሙታል፡፡ ልጆችሽ ሲል ነውና በዮሐንስ ተገብተው እነሱን ለእርስዋ መስጠቱ ነውና እንደ ነበሩ ሆነው ቃሉን በመመርመር ያስተውሉታል፡፡ ደቀ መዝሙሩንም እነኋት እናትህ ታጽናህ እንደ አለው ሁሉ ለእነርሱም እናታችሁ ሲል በመሆኑ በተመስጦ እንደ ዮሐንስ አጠገብዋ እንዳሉ ሆነው እናቴ ሆይ ይሏታል፡፡ በዮሐንስ እርሷን ለእነርሱ ለእኛም መስጠቱ ነውና እኛም ልብ ልንለው ይገባናል፡፡ አዚምን መንጥቀው ጥለው ፍጹም ፍቅሩን የተረዱ ሁለት ሺውን ዘመን እደሌለ ሁሉ ወደ ኋላ ተጉዘው ከድንግል ጋር ዛሬም ቀራንዮ መስቀሉ ስር በመንፈስ አንድ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ዛሬም ትኩስ ፍቅሩን ለመጋራት በትኩስ እንባቸው ደመና ተመስጦ ወደ ቀራንዮ ተጉዘው እንደ ዮሐንስ ድንግል እመቤታችንን በእንባ የሃዘኗ ተካፋይ በመሆን እናትነትዋን ይጋሩታል፡፡
በዚህ በዓላችን እኛም እንደ ቅዱሳኑ በአካል ባይሆንልን በአንቃእድዎ ልቡና በሰቂለ ኅሊና ሆነን ሁለት ሺህ ዘመን ወደ ኋላ ተጉዘን፣ ርቀቱን በተመስጦ አቅርበነው ከድንግል ጋር እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ቀራንዮ በመንፈስ እንሆን ዘንድ ልብ ልንለው ይገባል፡፡ በዘመኑ ባንኖርም በመልካም ምኞታችን እንደ ኖርን ይቆጠርልን ዘንድ፣ ተጉዘን ቀራንዮ ባንገኝ፣ ርቀት ቢወስነንም ስለመሻታችን እንደተጓዝን ይደረግልን ዘንድ፣ አንድም ባለንበት አምነን ስላከበርነው በረከቱን ያድለን ዘንድ፡፡ ኑ ቀራንዮ እንሂድ በእግራችን አይደለም በመንፈስ እንጂ፣ ኑ በበዓላችን ቀን መስቀሉን እንዳሰው በእደ ሥጋ አይደለም በዕደ ኅሊና እንጂ፣ የመስቀሉ ፍቅር ምሥጢር ቀራንዮ እንዲገኝ ዛሬም ያዘጋጀነው ይህ የመስቀል በዓል የቀራንዮ አካል ነው፡፡ አንድም ግሸን ደብረ ከርቤ እንሂድ የእውነተኛው መስቀል አካል ከእኛው ዘንድ አለና፡፡ ክርስቶስ ተሰቅሎ ዓለምን ያዳነበት፣ ደሙ የነጠበበት እውነተኛው መስቀል ለዓለም ብርሃኑን ያበራበትን የምናከብርበት ይህ ቀን ነውና፡፡ ምክንያቱም፡-
-
መስቀል የፍቅር ዙፋን ነውና፤ ቅዱስ ዮሐንስ ጌታ በመስቀል ላይ ሳለ እስከመጨረሻው ሳይለይ የፍቅሩን መጠን ተረድተዋል፡፡ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ የጌታን ሕማሙን በዚያች ሌሊት የአዳሩንና የውሎውን ለሰው ልጆች ፍቅር ሲል በሰው ልጆች እጅ የተቀበለውን ጽኑ መከራውን አይተዋልና፤ በመልእክቱም ”ፍቅርም እንደዚህ ነው፣ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደወደደን ስለ ኀጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደላከ እንጂ እኛ እግዝአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም” (1ዮሐ. 4: 10) ያለው፡፡ የሰቀሉትን እንኳ ወደዳቸው፣ ይቅርም አላቸው፡፡ በመስቀሉ ዙፋን በፍቅሩም ድነዋልና ”አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ” እንዲል፡፡
-
መስቀል የጥበብ ቤት ነውና፤ ጠቢቡ ሰሎሞን ” ጥበብ ቤትዋን ሠራች ... ፍሪዳዋን አረደች ... ማድጋዋን አዘጋጀች ... ሁሉን ጠራች ... ኑ እንጀራዬን ብሉ ... አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፣ በማስተዋል መንገድ ሂዱ ... ”(ምሳሌ 9፥ 1-10) ሲል፤ በቅዳሴ መጽሐፍ ላይ ጥበብ መድኀኒታችን ነው በማለት የሚሥጢሩን ባለቤትን ያመሠጥራል፤ በመስቀል ላይ ጥበብ የተባለ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወት እንጀራ ሆኖ ዓለም ሁሉ ተመግቦት ድኖአልና፡፡ ለእኛ በመስቀል ጥበብ ቤት ላይ የተሰቀለው ጥበብ መድኀኔዓለም በዛሬው በምናከብረው የጥበብ ምሥጢር መገኛ በሆነው የመስቀል በዓል ራስ እርሱ ክርስቶስ ነው፡፡ በዚህም እርሱን የዓለምን መድኅን እንሰብክበታለንና፡፡ ”አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ፣ የግሪክ ሰዎች ጥበብን ይሻሉ፣ እኛ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” (1ቆሮ. 1፥22-23) እንዲል፡፡
-
መስቀል የክርስቲያኖች ሁሉ አርማ ነውና፤ በምድራውያን ልማድ የሀገር ነጻነት በሰንደቅ ዓላማ አርማነት መውለብለብ እንዲታወቅ ሁሉ፣ ዛሬ የሰማያውያን ተስፋና የሕይወት አርማ በዓለም ላሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ መውጣት በክርስቶስ የታወጀበት ሰንደቅ ዓላማ መስቀል ነው፡፡ በሀገራችን ከአደይ አበባ ውበት ጋር አንድ ሆኖ የሚውለበለብበት መስከረም 16ና 17 ልዩ ክብረ በዓሉ ነው፡፡ ልዩ የሚያደርገው ከአርማ ጋር የእግዚአብሔር ኀይል መሆኑ ነው፡፡ ቅዱስ መስቀል ምንኛ ድንቅ ነው? ዕፅነት/መስቀሉ የተቀረጸበት እንጨት/ ከመለኮት ኀይል ጋር አንድነት፣ ድንቅ ተዋሕዶ፣ አጋንንት የሚርዱለት የክርስቲያኖች ቤዛ ልዩ ምልክት፣ ለመረጣቸው ብቻ ኀይልን ያደርጉበት ዘንድ የታደሉት ግርማ ሞገስ ቅዱስ መስቀል ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ”የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ነው፣ ለእኛ ለምንድነው ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው (1ቆሮ 1፥18) እንዲል፡፡
የመስቀል ፍቅር ሰው፣ ልዩ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ”ወሶበ ርእዮሙ እግዚእ ኢየሱስ ለእሙ ወለረድኡ ዘያፈቅር ይቀውሙ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወደውን ደቀ መዝሙርና እመቤታችንን ከእግረ መስቀል ቁመው ባያቸው ጊዜ ሲል፣ ድንግል ልብዋ በሀዘን ጦር ተወግቶ የልጅዋን መከራ መቻል ጭንቅ በሆነባት ጊዜ ልጅዋ መሪር ሃዘንዋን ተመለከተ፤ እንዲሁም ከአጠገቧ ካሉት በእንባ ከሚራጩት የኢየሩሳሌም ሴቶች ጋር ከወንድ ወገን የሚያጽናናት አንድ ሰው ቅዱስ ዮሐንስን አየው፡፡ ወይቤላ ለእሙ ኦ ብእሲቶ ነዋ ወልድኪ፤ አንች ሆይ ልጅሽ ይርዳሽ ያጽናናሽ አላት፡፡ ውሉድኪ ሲል ነው በዮሐንስ እኛን ለእርስዋ መስጠቱ ነውና፡፡ ወይቤሎ ለውእቱኒ ረድ ነያ እምከ፣ ደቀ መዝሙሩንም እነኋት እናትህ ታጽናህ አለው እምክሙ ሲል ነው፡፡ በዮሐንስ እርስዋን ለእኛ መስጠቱ ነውና”፡፡ (ዮሐ.19፥26-27)ብሎዋል፡፡ እነሆ ተመልከቱ፣ ለቅዱስ ዮሐንስ የባሕሪያችን መመኪያ የሆነችውን የተወደደች ድንግል እመቤት እናት ትሆነው ዘንድ ከአምላኩ ፈጽሞ ተሰጠችው፡፡ ድንግልን ከመስቀሉ ፍቅር ለይቶ ማየት ከቶ አይቻልም፡፡
መስቀል ፍጹም ፍቅር፣ ርኅራሄ፣ የዋህነት እንደሆነ ሁሉ፣ ድንግልም እንዲሁ ፍጹም ፍቅርን የተሞላች የፍጡር ሁሉ ፍቅር ቢደመር የእርስዋን ፍቅር ይደርስ ዘንድ ሊታሰብ አይችልም፤ ርኅራሄዋ እንኳን ለሰው ልጅ ለፍጡር ሁሉ የምታዝን አዛኝት ናት እንጂ፤ በየዋህነትዋ የዋሂት ርግብ የተባለች ፍጹም ናት እንጂ፡፡ድንግል በዚህ ዓለም ሳለች ልጅዋ እንደተሰቀለ ሆኖ በኅሊናዋ ተስሎ፣ ልብዋ በሕማሙ ጦር ተወግቶ፣ ሃዘንዋ ጸንቶ፣ በሰቆቃ ተውጣ፣ እጅዋን ወደ ላይ ዘርግታ አንድም ስለልጅዋ ኀዘን እንባዋን ስታዘራ በሌላም ልጅዋ ይምረን ዘንድ ስለእኛ ስለ ሰው ልጆች ምልጃ ታደርግ ዘንድ ከቀራንዮ ከስቅለቱ ቦታ እንዲሁም ከመቃብሩ ጎልጎታ አንድም ቀን ተለይታ አታውቅም ነበር፡፡ ሕማሙን እንደ እርስዋ ማን ተረዳ? ድንግልን የመስቀሉ ፍቅር እንዲገባን አማልጂን ብለን እንማጸናት፣ በአምስቱ ኀዘናትሽ ቃል ኪዳን አስቢን እንላት ዘንድ የዚህ ዓለም ፈተና ግድ ይለናልና፡፡ ልጅዋን ወዳጅዋን፣ እስዋንም ደስ እናሰኝ ዘንድ ፍቅርዋን፣ ርኅራሄዋን፣ የዋህነትዋን እንምሰል፡፡ ወገኖቼ ቂም በቀል፣ ክፋት፣ተንኮል፣ ምቀኝነት፣ ዘረኝነት፣ወዘተ እንተው፣ ለዚህ ዓለምም ለወዲያኛውም አይጠቅሙምና፡፡
እኛም ዛሬ ቅዱስ ዮሐንስን የመስቀሉ ፍቅር አብነት እናድርገው፣ ይኸውም ልዩ የሚያደርገው መለኮታዊ ፍቅሩን መረዳቱ፣ የመስቀሉ ሥር የፍቅረ ሰው መሆኑ፣ የጌታን የሕማሙን ጥልቀት መጠን ማስተዋሉ፣ ሁል ጊዜ ነገረ መስቀሉን በማሰብ ቁጽረ ገጽ መሆኑ፡፡ ከዚህ ዓለም ልዩ በሆነ ፍቅር ጌታውን የመውደዱ፣ ”እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት አምላክ የሰው ልጅን ከመውደዱ ጋር ሰው ወንድሙን ቢጠላ እግዚአብሔርን እንዳያውቅ በሚለው ኀይለ ቃልና ረቂቅ ምሥጢር ከተግባራዊ ሕይወት ጋር አቅርቦቱን ልብ ልንለው ግድ ይለናል፡፡
በነገረ መስቀሉ አንጻር፣ የድንግል እመቤታችንና የቅዱስ ዮሐንስ ፍቅረ መለኮት ሕይወታቸው ቅድስናን አጎናጽፏቸው ተገኝቷል፡፡ እኛም ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ለሁላችንም ”ዓለምንና በዓለም ያሉትን አትውደዱ ... የአባት ፍቅር በውሰጡ የለም፣ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዓለም ይኖራል” (1ዮሐ. 2፥15.17) በማለት የሕይወቱን ተግባራዊ ትምህርት እንዳስተላለፈልን ሁሉ፤ በዚህ ዓለም ስንኖር ነፍስና ሥጋችንን በፍቅረ መለኮት ተጸምዶ፣ በሕማማተ መስቀል ውስጥ ተገብቶ በፍቅር ውስጥ መኖርን፣ መንፈሳዊ አገልግሎታችን በፍቅረ መስቀል አንጻር ብቻ ሆኖ መሰለፍን፣ መሰባሰባችን በፍቅረ እግዚአብሔር ግብዣ ማድረግን፣ ሥራችንን በፍቅር ውስጥ ማከናወንን ያመለክተናል፡፡ ትዳራችን የመስቀል ፍጹም ፍቅር፣ ርኅራሄ፣ የዋህነት የተሞላ ሁል ጊዜ ለይቅርታ ዝግጁ የሆነ በዘለዓለም ሕይወት ተስፋ የተሞላ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ባጠቃላይም ሕይወታችን በመንፈሳዊ ኅሊና የተዋበና የመስቀሉን ፍቅር የሚያዘክር ይሆን ዘንድ፣እግዚአብሔር እርሱን በመውደድና በማይዝል በመንፈሳዊ የፍቅር ወላፈን ይጸምደን ዘንድ ፈቃዱ ይሁን፡፡ አሜን!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር! አሜን!!!
Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1094-2012-09-25-09-24-02